በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሙዝየም በ1936 ዓ.ም የብሔራዊ ቤተ መፅሐፍት አካል ሆኖ ተከፍቷል፡፡ በዚህም ከነገስታቱ ቤተሰቦችና ባለሟሎቻቸው በስጦታ መልክ የተበረከቱ ጥቂት የክብርና የማዕረግ መግለጫ ቅርሶች ለመጀመሪያ ግዜ በአውደ ርዕይ መልክ ቀርበዋል፡፡


ከዚህ ጋር ተያይዞ በአርኪዮሎጂ ኢንስቲቲዩት በ1946 ዓ.ም መመሰረት ለሙዚየም እድገት ከፍተኛ አስተዋጾኦ አበርክቷል፡፡ ይህም በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል የፈረንሳይ አርኪዮሎጂስቶች ተልኮ ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን ጠቃሚ ታሪካዊና የአርኪዮሎጂ ግኝት ለማግኘት አስችሏል፡፡ በቀጣይነትም ሙዚየሙ የተዛዋወረ በአሁኑ ሰዓት የብሔራዊ ባንክ ሠራተኞች ክበብ ሆኖ ወደሚያገለግለው እንፃ ሲሆን ቀስ በቀስም በ1958 ዓ.ም ወደ አሁኑ ይዞታው መጥቷል፡፡

በ1947 ዓ.ም የተቋቋመው የአርኪዮሎጂ ሙዚየም ስራውን የጀመረው ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተገኙ የአርኪዮሎጂ ውጤቶችን ለእይታ በማቅረብ ነበር፡፡ በ1958 ዓ.ም ብሔራዊ ሙዚየም የማቋቋም ሀሳብና የኢትዮጵያ የጥንታዊና ታሪካዊ ቅርስ አስተዳደር መመስረት መንግስት ለጉዳዮ ትኩረትና ድጋፍ እንዲሰጥ አድርጎታል፡፡


በመቀጠልም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዝየም በአዋጅ ስራውን የጀመረ ሲሆን ይህም ለጥንታዊ ቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ህጋዊ ከለላ በማግኘት የሀገሪቱን አርኬዎሎጂካዊና ፓሊዮንፐሎጂካዊ መገኛዎች እንዲሁም የጥንታዊ ህንፃዎችንና ሀውልቶችን የመጠበቅና የማቆየት ስልጣን አግኘቷል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሙዚየሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው አሮጌው ህንፃ የተገነባው 1928 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ  ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ሲሆን፣ የተገነባውም በወቅቱ ከፋሺስት ኢጣሊያ የጦር መሪዎች ለሆነው እና አዲስ አበባን ሲያስተዳደር ለነበረው መኖሪያ ቤት እንዲሆን ነበር፡፡ የፋሽት ኢጣሊያ የወረራ ዘመን ካበቃ በኃላ ህንጻው ለቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ልጅ ለልዑል መኮንን በመኖሪያነት ሲያገለግል ቆይቶ በመቀጠልም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተሰጠ፡፡ በመጨረሻም በ1957 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሁን ወደሚገኘበት ቦታ ሲዛወር ህንፃው ለሙዚየም አገልግሎት እንዲውል ተደረገ፡፡ 

አዲሱ ቋሚ የትርኢት አዳራሽ ወይም የሙዚየም ህንጻ የተገነባው በዩ.ኤስ.ኤይድ ድጋፍና በግንባታ ሚኒስቴር ተቆጣጣሪነት እ.ኤ.አ ከ1978 እስከ 1981 ነው፡፡ በህንፃው ግንባታ ወቅት የዩኔስኮ አማካሪዎች በኢግዝቢሽን አደረጃጀትና በትርእይት አቀራረብ ከፍተኛ የማማከር ስራ ሰርተዋል፡፡ 

ይህ ህንፃ በአሁኑ ወቅት ቋሚ የትርዒት አዳራሽ በመሆነው እያገለገለ ይገኛል፡፡ በውስጡም በርካታ ቅርሶች ሲኖሩ ከእነዚህም መካከል በአብዛኛ የአርኪዮሎጂካዊ ግኝቶች በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በአሁኑ ጊዜ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ስር ካሉት ዓላማ አስፈጻሚ ዳይሬክቶሬቶች አንዱ፣ ሲሆን፣ የሚገኘውም በአዲስ አበባ ከተማ 5ኪሎ አካባቢ ከቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን አጠገብ ነው፡፡ በ1992 ዓ.ም የሙዚየሙ ቋሚ ትርኢት ከአሮጌው ህንፃ ወደ አዲሱ ህንፃ ተዘዋውሮ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በአሁኑ ጊዜ አራት ዋና ዋና የትርእይት ማሳያ ክፍሎች ሲኖሩት በነዚህም የተለያዩ ቅርሶች ለጎብኚዎች ቀርበዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ለመጥቀስ ያህል የሰው ዘርን ታሪካዊና ባህላዊ አመጣጥ በቁፋሮ የተገኙ የጥንት መገልገያ መሳሪያዎች፣ ከተለያየ የሀገረቱ ክፍል የተገኙ የሰው ልጅ እና የእንሰሳት ቅርቶች ታሪካዊ ስብስቦች፣ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህላዊ ቅርሶች እንዲሁም ጥንጣዊና ዘመናዊ የሰነ-ጥበብ ስራዎች የሚቀርቡበት ከፍሎች ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት ግዚያዊ ኢግዚብሽኖችን በተመረጡ ዕርሶች ላይ ከስብስቦች መካከል በመምረጥ ከአጋር ድርጅቶች፣ ከግል አቅራቢዎችና ከክልል ሙዚየሞች ጋር በመተባበር ያቀርባል፡፡ በተለያዩ የዶክመንተሪ ፊልሞች በመታገዝም ገለጻ ይደረጋል፡፡

Pages: 1  2