አትሌት አሰለፈች መርጋ ሆቴልና ስፓ ዛሬ በይፋ ተመርቆ ስራ ጀመረ፡፡

በአዲስ አበባ ወሰን አካባቢ ግንባው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው ሆቴሉ ከ40 በላይ እንግዳ ማረፊ ክፍሎችን፣ የስብሰባ አዳራሽ ሪስቶራንትና ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠት የሚችል ነው፡፡


የሆቴሉ ባለቤት ከሀገራችን ጀግኖች አትሌቶች አንዷ የሆነችው አትሌት አሰለፈች መርጋ እና ባለቤቷ አትሌት ኪዳኔ ባልቻ ናቸው፡፡


በሆቴል ምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ እና ሌሎችም ታድመዋል፡፡


ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ሀብታሙ ሲሳይ ባስተላለፉት መልዕክት አትሌቷ በአለም አደባባይ ኢትዮጵያን እንዳኮራችው ሁሉ አሁን ደግሞ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ መሰማራቷ ለሌሎች ከታች ለሚመጡ አትሌቶችም አርዓያ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡
ይህ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ በይፋ የሚመረቀው የአሰለፈች መርጋ ሆቴልና ስፓም በኢትዮጵያዊ መልካም መስተንግዶ አገልግሎቱን እንደሚሰጥ እተማመናለሁ ያሉት አቶ ሀብታሙ በሚኒስቴር መ/ቤቱ በኩልም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ጀግኖች አትሌቶቻችን ከሁሉ በፊት ኢትዮጵያ ዳግም መነሳት እንደምትችል በተግባር ማሳየት የቻሉ ናቸው ያሉ ሲሆን ከነዚህ ጀግኖች አንዷ አትሌት አሰለፈች መርጋ እና ባለቤቷ መሆናቸውን አንስተው ዛሬ ደግሞ ለዚህ በመብቃታቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች እና ጀግናው አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገ/ስላሴም እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕታቸውን አስተላልፈዋል፡፡


News and Updates News and Updates