‹‹የኢትዮጵያ ቱሪዝም አጀንዳ!!›› በሚል የተዘጋጀው የቀጣይ አስር ዓመቱ የቱሪዝም ዘርፍ ዕቅድ ለፌደራል ባለድርሻ አካላት ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል፡፡

በአራቱ የትኩረት መስኮች ማለትም በተወዳዳሪ ቱሪዝም፣ የቱሪዝም ማኅበረሰብ ትስስር ተጠቃሚነትና አጋርነት፣ በቱሪዝም መረጃ ስርዓት ልህቀት እና በተቋማዊ አቅም ግንባታ የተቃኘው መሪ ዕቅዱ ከዚህ በፊት ከተለያዩ አጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በተደጋጋሚ ለውይይት ቀርቦ ሀሳብና አስተያየቶች በግብዓትነት ተካተውበት ተሻሽሎና ዳብሮ የቀረበ ዕቅድ ነው፡፡
በመድረኩ የአስር ዓመቱ መሪ ዕቅድ እና የ2013ቱ በጀት ዓመት ዕቅድ ለአፈጻጸምና ለክትትል በሚያመች መልኩ በዝርዝር ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ በውይይት መድረኩ የተሳተፉ አካላትም ሀሳብ፣ አስተያየትና ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በሚኒስቴሩ አመራሮች በኩል ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ በመድረኩ ተገኝተው፡- ‹‹ዕቅዱን ተቀብለን ብንፈፅመው ከቱሪዝም ዘርፉ ችግር ተላቀን እድገት እንደምናስመዘግብ ሙሉ እምነት አለን ያሉ ሲሆን ነገር ግን አፈጻጸም ላይ ትልቅ ተግዳሮት ይገጥመናል የሚል ስጋት እንዳላቸውና ባለድርሻ አካላትን የሚያስፈልጉትም ዕቅዱን በብቸኝነት መስራትና ማሳካት ስለማይቻል ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ የባለድርሻ አካላት በዕቅዱ የተለየውን ድርሻችሁን ከኛ ጋር በመሆን ብትወጡልን መልካም ስኬት እናስመዘግባለን፡፡›› ብለዋል፡፡

ሌላው በመድረኩ የተገኙት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ተወካይ የተከበሩ አቶ ግርማ መላኩ በክትትልና ቁጥጥር ወቅት እየተፈጠረ ያለው ችግር በተማከለና በተቀናጀ መልኩ ካለመስራት የመነጨ ችግር ነው ብለዋል፡፡ የቱሪስት መዳረሻዎቻችንን በዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች እና በውጭ ቋንቋዎች በማስተዋወቅ ረገድ ብዙም የተሰራ ስራ የለም፡፡ እዚህ ላይ የተሳካ ስራ ለመስራት በተናጥል መሮጥ ሳይሆን በተቀናጄ መንገድ ተባብሮ መስራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡›› ብለዋል፡፡
በማጠቃለያውም የኢፌዲሪ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክብርት ወ/ሮ ቡዜና አልከድ የተሰጠንን ሀሳብና አስተያየት እንደ ግብዓት ወስደን በየጊዜው ዕቅዳችንን እየከለስን እንሰራለን ብለዋል፡፡ በሀገራችን በግልጽ ከታወቁ የቱሪስት መዳረሻዎች በተጨማሪ ሌሎች ያልተለዩ የቱሪስት መዳረሻዎች መኖራቸውን ጠቅሰው እነሱን ለይቶ ማስተዋወቅ በቀጣይ አንዱ ተግባራችን ነው ብለዋል፡፡ የፌደራል ባለድርሻ አካላት ጋር በሰው ሳይሆን በአሰራር ስርዓት መተሳሰርና በጋራ መስራት ያስፈልጋል ያሉት ዲኤታዋ የቱሪዝም ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የግሉ ዘርፍ የባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ሚና አለባቸው ነው ያሉት፡፡ በቱሪዝም ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የሰላም ጉዳይ አስተማማኝ መሆን እንዳለበትና ሆቴል እየተቃጠለ ሌላ ሆቴል መገንባት አይቻልም ብለዋል፡፡ ባለሀብቱ የሚተማመንበት ምቹ ሁኔታ ልንፈጥርለት ይገባል፡፡ ይሄ ደግሞ የኛን የጋራ ቅንጅት ይጠይቃል፡፡›› በማለት ተናግረዋል፡፡


News and Updates News and Updates