በቱሪዝም ልማት ዘርፍ ለተሰማሩ ሴቶች ሲሰጥ የቆየው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተጠናቀቀ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ከኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር “የባህልና ቱሪዝም ሃብቶቻችንን እንወቃቸው አውቀን እንጠቀምባቸው!!! ”  በሚል መሪ ቃል በቱሪዝም ልማት ዘርፍ ለተሰማሩ ሴቶች በዘርፉ ያላቸውን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ለማጎልበት  ከሚያዚያ 12 እስከ ሚያዚያ 17/ 2010 ዓ.ም ድረስ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እና የጉብኝት መርሐግብር ተጠናቀቀ፡፡

በመርሃ ግብሩ መሠረት የባሌ ጎባን ከተማ ማዕከል በማድረግ በተለያዩ ፕሮግራሞች ታጅቦ የተከናወነ ሲሆን ከፕሮግራሞቹም መካከል ጉብኝቶች፣ ባዛርና እና ሲምፖዚየም፣ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች እና የፓናል ውይይቶች ተካሂዷል፡፡ በተለይም ሲንቄ እና በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ የአቴቴና ሴቶች በማህበራዊ አኗኗር ሂደት ውስጥ ያላቸው ድርሻ፣ በመጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ የተጠና ሀገር አቀፍ ጥናት፣ ሴቶችና ቱሪዝም፣ ራስን ማብቃት፣ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻዎች፣ ሴቶችና የገጽታ ግንባታ የተሰኙ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸው ጥልቅ ግንዛቤ  የተወሰደበት ነበር፡፡

በቀጣይነትም የጉባኤው ተሳታፊዎች በክልሉ ከሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል በዋናነት የቱሉ ጎዶ፣ ሲምቦ ሎጆ፣ አብያታና ሻላ፣ ጥቁር ውሃ እንዲሁም በባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ ብርቅዬ የዱር እንስሳቶችና በኢትዮጵያ ከራስ ደጀን ቀጥሎ በርዝመቱ  2ኛ የሆነውንና 4377 ሜትር ርዝመት ያለው የቱሉ ዲምቱ (ሳነቴ) ተራራ ጭምሮ ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻዎችን ጉብኝት አድርገዋል፡፡

 

የመርሃ ግብሩን መዘጋጀት አስመልክቶ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ወይንሸት ኃይለማሪያም እንገለጹት ከተለያዩ የግል እና የመንግስት ሚዲያዎች ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ፕሮግራሙ ከአራት ዓመት በፊት የተጀመረና በዓመት ውስጥ አንድ ጊዜ የሚከናወን መሆኑንና ወደፊትም የበለጠ ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ዋና ዓላማውም በቱሪዝም በዘርፉ የተሰማሩ ሴቶችን የማሰፈጸምና የመፈጸም አቅም በማጎልበት ሴቶች ዘርፉ ላይ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማሳደግ እንዲሁም የሴቶች ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከር ምርጥ ተሞክሮዎችንም እንዲለዋወጡ አጋጣሚዎችን ለመፍጠርም ጭምር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም ለፕሮግራሙ ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽ ያደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት ሽልማት የተሰጣቸው ሲሆን የፕሮግራሙ ተሳታፊ የነበሩ ሴቶች በሰጡት አስተያየት እንደዚህ ዓይነት ጉብኝቶችና ስልጠናዎች ስራቸውን በእውቀት ላይ ተመስርተው እንዲሰሩ በማስቻል ለዘርፉ የተሻለ አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሚያስችላቸው የገለጹ ሲሆን ቀጣዩን ተረኛ አሰተናጋጅ ክልል ደግሞ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መሆኑ ታውቋል፡፡


News and Updates News and Updates