የዓለም ቱሪዝም ቀን በኢትዮጵያ የቱሪዝም አባት በአቶ ኃብተስላሴ ታፈሰ መታሰቢያነት ይከበራል

ኢዲስ አበባ መስከረም 11/2010 የዘንድሮ የዓለም ቱሪዝም ቀን በኢትዮጵያ የቱሪዝም አባት በመባል በሚታወቁት በአቶ ኃብተስላሴ ታፈሰ መታሰቢያነት በኦሮሚያ ክልል ይከበራል።

በኢትዮጵያ 30 ጊዜ የሚከበረው በዓሉ "ቱሪዝም ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች በኦሮሚያ ክልል ይከበራል።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር  የቱሪዝም ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ መዓዛ ገብረመድህን ዛሬ በዓሉን አስመልክቶ በኦሮሞ ባህል ማዕከል በተካሄደው ሲምፖዚየም ላይ እንደተናገሩት የዘንድሮውን በዓል ሁለት ገጽታዎች ልዩ ያደርጉታል።

የመጀመሪያው የኦሮሞ ህዝብ መገለጫ የሆነው የገዳ ስርዓት በዓለም ወካይ ቅርስነት በዩኔስኮ ቋሚ ቅርስነት መመዝገቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ ከልጅነት እስከ እውቀት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያገለገሉት የአቶ ኃብተስላሴ ታፈሰን ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ተከትሎ በዓሉ በእርሳቸው ስም እንዲሰየም መደረጉ ደግሞ ሌላው ልዩ ገጽታ ነው ብለዋል።

በመሪ ሃሳቡ መልዕክት መሰረትም በዘርፉ የተቀናጀ አሰራር በመፍጠር ለዜጎች ዘላቂ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ለማድረግ በተጀመረው ጉዞ "የምንሰራበት ዓመት ነው" ብለዋል።

በዓሉ የዜጎችን የጉብኝት ባህል ለማሳደግ፣ የቱሪዝም መስህቦችን ለማስተዋወቅና የማንነት መገለጫ የሆኑትን ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ አሻራዎች ለአገር መልካም ገጽታ በማዋል አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት የጎብኚዎች ቁጥር መቀነሱን በመጥቀስም ዘንድሮ ችግሩ በመቀረፉ የዘርፉ ዕቅድ የሚሳካበት ዓመት እንዲሆን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የቱሪዝም ቀኑ ሲከበር በስፋት ያልተዋወቁ የቱሪዝም መዳረሻዎች በሚገኙባቸው የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ትኩረት መደረጉንም አውስተዋል።

ቱሪዝም ለዜጎች ከሚፈጥረው የስራ ዕድል ባሻገር ከሌሎች አገራት ጋር ጠንካራ ትስስር በመፍጠር ግኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያስችልም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቅሰዋል።

ምንጭ፡- ኢዜአ


News and Updates News and Updates