የመጀመሪያ ጥናትና ምርምር ጉባኤ በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ ተካሄደ

Newsበባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬትና በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም በክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ትብብር ከሚያዝያ 18-21/2009 ዓ.ም የዘርፉ የመጀመሪያ የጥናትና ምርምር ጉባኤ በጎንደር ከተማ ተካሄደ ፡፡
 
አውደ ጥናቱን በንግግር የከፈቱት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ሂሩት ወ/ማርያም እንደገለፁት ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪካዊ፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቅርሶች ባለቤት ናት። ከቱሪዝም የሚገኘውን ሃብት ለማሳደግ ቀደም ሲል በተሰሩ ስራዎች የሃገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሃገራት ቱሪስቶች እንቅስቃሴ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ካለው ያልተነካ የቱሪስት መስህብ ሃብት ጋር ሲነፃፀር ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በመደገፍ ደረጃ ከዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ገልፀዋል። "በየዓመቱ በዓለም ላይ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ቱሪስት ለጉብኝት የሚንቀሳቀስ ሲሆን ኢትዮጵያን የሚጎበኟት አንድ ሚሊዮን እንኳ አይደርሱም" ብለዋል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የመስህብ ሃብቶችን በአግባቡ ቆጥሮ የመለየት፣ የማልማት፣ የመንከባከብ፣ የመጠበቅና በእውቀት ላይ ተመስርቶ ሰፊ የሆነ የማስተዋወቅ ስራ አለመከናወኑ እንደሆነም ተናግረዋል።

እንዲሁም በውጭ ሃገራት ቀደም ሲል ስለ ሃገራችን ገፅታ ያለው የተሳሳተ ግንዛቤና በዘርፉ የሚተገበሩ የልማት ስራዎችም በጥናትና ምርምር የታገዙ እንዳልነበሩም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት የተመዘገቡ 28 የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች እንዳሏትና ከእነዚሁ ውስጥም 12ቱ ጥንታዊ ፅሁፎች መሆናቸውን አመልክተው እነዚህንና ሌሎች ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ የተፈጠሮ ሃብቶችን በመለየትና በማልማት ለአለም ህዝብ ማስተዋወቅና ከቱሪዝም ሃብቱ ተጠቃሚ ለመሆን ተቀናጅቶ መስራት ይገባል። በተለይም አትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ የምድረ ቀደምት ታሪክ ባለቤት መሆኗን አውቆ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የማስተዋወቅና ገፅታዋን የመገንባት ስራ የሁሉም ዜጋ ድርሻ መሆን እንዳለበት አብራርተዋል።

"የጥናትና ምርምር ጉባኤውም ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ማደግ የሚያግዙ አዳዲስ የምርምር ውጤቶችንና ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት የሚሆን ሃሳብ ይገኝበታል" ብለዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን በበኩላቸው "የቱሪዝም ዘርፉ ባለፉት 10 ዓመታት የተሻለ ለውጥ ተመዝግቦበታል "ብለዋል። ዩኒቨርሲቲውም በቱሪዝም ዘርፉ የሚስተዋለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ችግር ለመፍታት በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የባህል ማዕከል በማቋቋም ተማሪዎች የባህል ልውውጥ እንዲያደርጉና ባህላቸውን አውቀው እንዲያድጉ የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

"በየዓመቱም የቱሪዝም ሳምንትን በማክበር የጎንደር ከተማ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲያድግ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተከናወነ ነው በሃገር ዓቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የቱሪዝም ጥናትና ምርምር ጉባኤም አዳዲስ ምክረ ሃሳቦችን ለማፍለቅ ያግዛል" ብለዋል።

ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት የመጀመሪያው የባህልና ቱሪዝም ጥናትና ምርምር ጉባኤ ላይ በተለያዩ ምሁራን የተጠኑ 13 ምርምሮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
 
Newsበጉባኤው የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባና የሃገሪቱን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማሳደግና አዳዲስ መዳረሻዎችን ለማልማት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ምሁራን የገለጹ ሲሆን የቱሪዝም እንቅስቃሴው ከጎረቤት ሃገራት በተቀራራቢ እንዲለማና ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆንም ምሁራን፣ ህዝቡና መንግስት ተቀናጀቶና ተናቦ በጋራ መስራት እንደሚገባ አብራርተዋል።

በቱሪዝም ልማቱ ባለሃብቱ በብዛት በዘርፉ እንዲሳተፍም መንግስት አስፈላጊውን ግፊት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ህብረተሰቡ የቱሪዝም ሀብቶችን ጠንቅቆ በማወቅ ለቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መሰራት እንዳለበት ምሁራኑ በሰጡት አስተያየት ጠቁመዋል።

የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ምርምሮች እየተከናወኑ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በሚኒስቴሩ የሴክተር ልማት ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ተክሉ ናቸው።

እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትም የባህል እሴቶችንና ቅርሶችን የሚመለከቱ ጥልቀት ያላቸው 15 ጥናትና ምርምሮችን ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

"በተለያዩ ምሁራን የሚከናወኑ ጥናቶች ወደ ሚመለከታቸው ተቋማት ሄደው ወደ ትግባራ እንዲገቡ ተገቢው ክትትል ይደረጋል" ብለዋል።

በመጨረሻም አቶ ልዑል ዩሃንስ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊና አቶ ተፈሪ ተክሉ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሴክተር ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቅራቢነት በዘርፉ አቅም ግንባታና ዩኒቨርሲቲዎች ከግልና የመንግስት ተቋማት ጋር በጋራ መስራት የሚችሉበትን መንገድና በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮና በክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረሙን ለማጠናከር መከናወን ስላለባቸው ጉዳዮች  ምክክር በማድረግ ተጠናቋል ፡፡


News and Updates News and Updates