የ2009 ዓ.ም የዓለም ቱሪዝም ቀን የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ (Guidebook) የተጽዕኖ ጥናት

 • 2009 ዓ.ም የዓለም ቱሪዝም ቀን የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ (Guidebook) የተጽዕኖ ጥናት

በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ

  የጥናት ቡድኑ አባላት፡-

 • ዶ/ር ፍጹም አባተ (የጥናቱ መሪ)
 • ወ/ሮ የሺወርቅ አበበ (አባል)
 • አቶ ደስታ ምትኩ (አባል)
 • አቶ ብርቅነህ በቀለ (አባል)
 • ወ/ሮ መስከረም ባዩ (አባል)
 • አቶ ጸጋዬ ዘመዴ (አባል)
 • አቶ ሳምሶን አየናቸው (አባል)
 • አቶ ዳኘው ተፈራ (አባል)
 • አቶ ዋናው ኃ/ማርያም (አባል)

አሕፅሮተ ጥናት (Abstract)

ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ በዋናነት መሰረት ያደረገው ሁለት ጥቅል ዓላማዎችን (General objectives) ነው፡፡ እነዚህም፣ 1ኛ/ የ2009 ዓ.ም የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ ይዘትንና ዲዛየንን ማሻሻል፣ 2ኛ/ የ2009 ዓ.ም የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ ለአዲስ አበባ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ያለውን አወንታዊ ሚና ማሳዳግ የሚሉ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ሶስት ዝርዝር ዓላማዎችን (Specific objectives) ታሳቢ በማድረግ ጥናቱ ተካሂዷል፡፡ እነዚህም፣ 1ኛ/ የ2009 ዓ.ም የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ ይዘትንና ዲዛየንን ከማሻሻል አንጻር በመጽሐፉ ውስጥ አሁን የሚታዩ ጠንካራ ጎኖችን እና ክፍተቶችን/ደካማ ጎኖችን በዝርዝር መረጃዎች መሰረት መተንተን፣ 2ኛ/ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የ2009 ዓ.ም የዓለም ቱሪዝም ቀን የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ ለአዲስ አበባ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ያለውን አወንታዊ ሚና ከማሳዳግ አንጻር በጥናቱ የተገኙ መረጃዎችን ውጤታማነት ማጎልበት፣ 3ኛ/ የጥናቱን ውጤቶች መነሻ በማድረግ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የ2009 ዓ.ም የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ በተሻለ መልኩ የሚዘጋጅባቸውን አማራጮች ማመላከት ናቸው፡፡

ለጥናቱ ሶስት የመረጃ ማሰባሰቢያ ዘዴዎች ተዘጋጅተው ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ እነዚህም፣ 1ኛ/ የሰነዶች ዳሰሳ ማለትም የተለያዩ የአገር ውጭ እና የአገር ውስጥ የቱሪስት መመሪያዎች /Guidebooks/ የይዘትና የዲዛየን ቅኝት፣ 2ኛ/ ከቢሮ ሃላፊዎችና ከተመረጡ የቢሮው ሙያተኞች ጋር የተደረጉ ሶስት ኢ-መደበኛ ውይይቶች፣ በግንቦት 9/2009 ዓ.ም ለአንድ ሰዓት ያክል በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ከሁለት ሙያተኞች ጋር /የቢሮውን የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ የሕትመት ሥራ ጥራት ደረጃን በተመለከተ/ የተደረጉ መደበኛ ውይይቶች፣ 3ኛ/ በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በማዕከል፣ በክፍለከተሞችና በወረዳዎች ደረጃ ለሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት እና ለሌሎች የሴክተር መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ለቢሮው ባለድርሻ አካላት፣ ከ2009 ዓ.ም የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ ጋር፣ በፖስታ የቀረበ የጽሑፍ መጠይቅ ናቸው፡፡

በዚህ ጥናት የመረጃ ማሰባሰቢያ መሳሪያዎች ከተዘጋጁ በኋላ በታለመ /Purposive Sampling/ የናሙና አወሳሰድ የመረጃ ሰጪዎች መረጣ ተካሂዷል፡፡ ይኼውም የመረጃ ሰጪዎችን ለጥናቱ ባላቸው የሥራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት መሰረት በጥናት ቡድኑ ውሳኔ መምረጥ የተቻለበት እንዲሁም መላሾቹ በተመቻቸው ጊዜና ቦታ በሁለት ወር አማካይ የጊዜ ገደብ ውስጥ ተረጋግተው የቱሪስት መመሪያውን /Guidebook/ በጥልቅ በማንበብ ለጥናቱ መረጃ እንዲሰጡ የማድረግ ዕድልን የሰጣቸው አሰራር ነው፡፡ ይህም ሰፊ፣ የተሟላና በቂ መረጃ ለጥናቱ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ከሚመለከታቸው አካላት ለማግኘት ረድቷል፡፡ በመሰረቱ የጽሁፍ መጠይቅ እና የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ/ጋይድ ቡክ/ የወሰዱ መላሾች /Respondents/ ብዛት 187 ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 145ቱ በአግባቡ ሞልተውና ለጥናት ቡድኑ መጠይቁን መልሰው ለጥናታዊ ሥራው መጠይቁ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ 

በመጨረሻም፣ በመረጃ ትንተና የቀረቡ ዝርዝር ማሳያዎችን መሰረት በማድረግ መጽሐፉ ምንም እንኳን የተወሰኑ ጉድለቶች ቢኖሩትም በተጠቃሚዎቹ ላይ ሊያሳድር የሚችለው /በዋናነት የአዲስ አበባን የቱሪዝም ሀብቶች የማሳወቅ አቅም/ ተጽዕኖ አወንታዊ መሆኑ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የ2009 ዓ.ም የዓለም ቱሪዝም ቀን የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ ለአዲስ አበባ ዘላቂ (Sustainable) የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ያለውን አወንታዊ ሚና ከማሳዳግ አንጻር በጥናቱ የተገኙ መረጃዎችን ውጤታማነት ለማጎልበት እና የጥናቱን ግኝቶች መነሻ በማድረግ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መጽሐፉን በተሻለ መልኩ የሚዘጋጅባቸውን አማራጮች ከማመላከት አኳያ ጠቃሚ ምክረሃሳቦች (recommendations) ከጥናቱ ተገኝተዋል፡፡ ለምሳሌ፣ በዋናነት የመጽሐፉን መጠን የማሳነስ፣ ዲዛየኑን፣ የፊደላት መጠንና ፎቶዎችን የማሻሻል ሥራ /እንደ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ካሉ አታሚ ድርጅቶች ጋር በሕግ አግባብ በመስራት/ እንዲሁም አዳዲስ ጥናቶችን በማካሄድ የከተማዋን ዋሻዎች፣ የስፖርት ቱሪዝም አማራጮችና የመሳሰሉትን የቱሪስት መስህቦች በመጽሐፉ አካትቶ እንዲሁም በአማርኛና እንደፈረንሳይኛ፣ ቻይንኛና ጀርመንኛ ባሉ በተለያዩ ቋንቋዎች መጽሐፉ ተተርጉሞ አሁን ከሚታየው በተሻለ መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጉባኤዎች፣ በበዓላትና በተለያዩ መድረኮች ለጎብኚዎች በብዛትና በቋሚነት መሰራጨት እንዳለበት በጥናቱ ተመልክቷል፡፡  

 1. መግቢያ (Introduction)
  1. ዳራ (Background of the study)

ቱሪዝም ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን የያዘ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያው በአንድ ሀገር ውስጥ ባህላዊ፣ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ የሆኑ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሀብቶችን በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች አማካይነት ለሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ለሚመጡ ጎብኚዎች በማቅረብ በተለይ ለሀገር ልማት ዕድገት ያለው ፋይዳ ቱሪዝምን እጅግ ተመራጭ አድርጎታል፡፡ በቅርቡ በዓለም የጉዞና ቱሪዝም ምክር ቤት (ቀ.አ.$i) እንደተገለጸው “የጉዞና ቱሪዝም ሴክተር/ዘርፍ ዕድገት በ2015 (2.8%) እ.ኤ.አ. የዓለምን የኢኮኖሚ ዕድገት (2.3%) እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርትና ሽያጭ ዕድገትን መብለጡ፣ 7.2 ትሪሊየን ዶላር (ማለትም 9.8% ያህል የዓለም አቀፍ ጂዲፒ መጠን ማለት ነው) ከዘርፉ መገኘቱ፣ 284 ሚሊየን  (ማለትም በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ከአሥራ አንድ የሥራ ዕድሎች አንዱ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ የተፈጠረ ነው) የሥራ ዕድሎችን መፍጠሩ፣ ይህም ዕድገት እያደገ ሄዶ በ2026 እ.ኤ.አ. 370 ሚሊየን የሥራ ዕድሎችን መፍጠር እንደሚችል የተገመተለት መሆኑም ቱሪዝም በመላው ዓለም ያለውን አወንታዊ ሚና በጉልህ ያሳያል፡፡ አይን፣ ኤኔዳ፣ ሀናህና ለውሴ (ቀ.አ.$i) እንደሚያስረዱት ደግሞ ቱሪዝም በአፍሪካ ለተለያዩ ሀገሮች ኢኮኖሚ ማበብ ምክንያት ከመሆኑም ባሻገር ከዕለት ተዕለት የኑሮ መደጎሚያነት አንስቶ እስከ ኤክስፖርት አቅምነት የደረሰ፣ ለምሳሌ፣ ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገሮች በ2012 እ.ኤ.አ. ከ36 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ያስገኘ ወሳኝ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ከዚህም መገመት እንደሚቻለው ኢንዱስትሪው ባህላዊ፣ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ የሆኑ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሀብቶችን በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች አማካይነት የማጥናት፣ የማልማት፣ የማስተዋወቅና ለገበያ የማቅረብ እንቅስቃሴዎችን ስለያዘ ለሀገሮች ልማት ቀጣይነት ያለው ከፍተኛ አስተዋዕጾ በማድረግ ላይ ያለ ኢንዱስትሪ መሆኑን ነው፡፡       

በተለያዩ ሀገሮች ከቱሪዝም ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ተቋማት የቱሪዝም አቅም ጥናቶችን መሰረት በማድረግ የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ በማዘጋጀትና የቱሪስት መስህቦችን በየሀገሩ በማስተዋወቅ ለሀገር ዕድገት ከፍተኛ አወንታዊ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም በመጀመሪያ ደረጃ ሀገሮች ለቱሪስቶች/ለጎብኚዎች ምቹ የሆኑ ባህላዊ፣ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ የሆኑ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሀብቶቻቸውን በሙያተኞች ያስጠናሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃም በተለያዩ የሕትመት ውጤቶች የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ በየቋንቋው በሙያተኞች አማካይነት ያዘጋጃሉ፡፡ ቀጥሎም በኦንላየንና በኦፍላየን ልዩልዩ አማራጮች የመጽሐፉን ቅጂዎች ለጎብኚዎች በክፍያ ወይም በነፃ በማሰራጨት ጎብኚዎች ወደ ቱሪስት መስህቦች እየጎረፉ የሀገርን ዘርፈብዙ የልማት እንቅስቃሴዎች የሚደግፉ /የውጭ ምንዛሪ ገቢና የገጽታ ግንባታን የመሳሰሉ ጥቅሞችን ለማሳካት/ ሥራዎች በተለያዩ ሀገሮች ይሰራሉ፡፡ በመጨረሻም በየወቅቱ መጽሐፉ እየታደሰ ይበልጥ ተደራሽና ተነባቢ እየሆነ ልማታዊ ሚናውን በየሀገሩ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ልዩልዩ ዘርፎች ሲጫወት ይታያል፡፡ ለዚህም በርካታ የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍትን /Guidebooks/ ከየሀገሩ ከኢንተርኔት በማውረድ ማንበብና ከሞላ ጎደል ይህን ሃቅ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡                  

ቱሪዝም ለዕድገታቸው ወሳኝ በሆነባቸው ሀገሮች ሁሉ እንደተለመደው በኢትዮጵያ የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍትን /Guidebooks/ ለጎብኚዎችና የንባብ ፍለጎቱ ላላቸው ሁሉ በተለያዩ ጊዜያት ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም ሁሉም መጽሐፍት የጎብኚዎችን ወቅታዊ የመረጃ ጥያቄ በመመለስ ፍጹም ስላልሆኑ በገበያና በአብያተ መጽሐፍት ከሚገኙ ወይም ለጎብኚዎች በነፃ ከሚታደሉ የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍት ይዘት መረዳት እንደሚቻለው ከጊዜ ወደ ጊዜ በሀገሪቱ ውስጥ የሚታዩ ዘርፈብዙ ለውጦችን መሰረት በማድረግ መጽሐፍቱ መዘጋጀታቸውን ነው፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ በአጠቃላይና የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ካፒታል በሆነችው በአዲስ አበባ በተለይ ባህላዊ፣ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ የሆኑ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሀብቶችን በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች አማካይነት ለሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ለሚመጡ ጎብኚዎች በማቅረብ የሀገር ልማትንና ዕድገትን ከማፋጠን አኳያ የቱሪዝምን ልዩልዩ ዘርፎች አወንታዊ ሚና ለማጎልበት የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ ማዘጋጀት፣ ለአንባብያን ተደራሽ ማድረግና የመጽሐፉን ተጽዕኖ /ማለትም አወንታዊና አሉታዊ ጎኖች ከነመገለጫዎቻቸው ጋር/ በሳይንሳዊ መንገድ ማጥናት ሊበረታታ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡      

 1. የመረጃ ማሰባሰቢያ መሳሪያዎች ዝግጅት
  1. የጥናትና ምርምሩ ዘዴ (Methods of the study)

 

ለጥናቱ ሶስት የመረጃ ማሰባሰቢያ ዘዴዎች ተዘጋጅተው ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ እነዚህም የሰነዶች ዳሰሳ ማለትም የተለያዩ የአገር ውጭ እና የአገር ውስጥ የቱሪስት መመሪያዎች /Guidebooks/ የይዘትና የዲዛየን ቅኝት (ክፍል 2.2.1ን ይመልከቱ)፣ ከቢሮ ሃላፊዎችና ከተመረጡ የቢሮው ሙያተኞች ጋር የተደረጉ ሶስት ኢ-መደበኛ ውይይቶች፣ በግንቦት 9/2009 ዓ.ም ለአንድ ሰዓት ያክል በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ከሁለት ሙያተኞች ጋር /የቢሮውን የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ የሕትመት ሥራ ጥራት ደረጃን በተመለከተ/ የተደረጉ መደበኛ ውይይቶች እንዲሁም በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በማዕከል፣ በክፍለከተሞችና በወረዳዎች ደረጃ ለሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት እና ለሌሎች የሴክተር መስሪያ ቤቶች እንዲሁም የቢሮው ባለድርሻ አካላት የቀረበ የጽሑፍ መጠይቅ ናቸው፡፡ የሁሉም የመረጃ ማሰባሰቢያ መሳሪያዎች ዋንኛ ይዘት በአባሪ 1 የሚገኘው የጽሑፍ መጠይቅ ይዘት ነው፡፡

 1. የመረጃ ሰጪዎች መረጣ /ናሙና አወሳሰድ/

   በዚህ ጥናት የመረጃ ማሰባሰቢያ መሳሪያዎች ከተዘጋጁ በኋላ በታለመ /Purposive Sampling/ የናሙና አወሳሰድ የመረጃ ሰጪዎች መረጣ /ናሙና አወሳሰድ/ ተካሂዷል፡፡ ይኼውም የመረጃ ሰጪዎችን ለጥናቱ ባላቸው የሥራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት መሰረት በጥናት ቡድኑ ውሳኔ መምረጥ የተቻለበት እንዲሁም መላሾቹ በተመቻቸው ጊዜና ቦታ በሁለት ወር አማካይ የጊዜ ገደብ ውስጥ ተረጋግተው የቱሪስት መመሪያውን /Guidebook/ በጥልቅ በማንበብ ለጥናቱ መረጃ እንዲሰጡ የማድረግ ዕድልን የሰጣቸው አሰራር ነው (ኮትሃሪ፣ 2004 እ.አ.አ.፤ ፔተን፣ 1990 እ.ኤ.አ.)፡፡ ይህም ሰፊ፣ የተሟላና በቂ መረጃ ለጥናቱ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ከሚመለከታቸው አካላት ለማግኘት ረድቷል፡፡

 1. የመረጃ ምንጭና አሰባሰብ (Data source and collection)

ከሕዳር 21/2009 ዓ.ም ጀምሮ በሁለት ወር ውስጥ የመረጃ ማሰባሰቢያ መሳሪያዎችን የጥናት ቡድኑ አባላት ተጠቅመው (ማለትም አንድ የቱሪስት መመሪያ /Guidebook/፣ የጽሑፍ መጠይቁን ኮፒ በአንድ ፖስታ ውስጥ አድርገው፣ የሰነዶች ዳሰሳና ውይይቶችን በማካሄድ) በአዲስ አበባ ተዘዋውረው መረጃ እንደሚያሰባስቡ በዕቅድ ተይዞ ሥራው ቢጀመርም በሁለት ምክንያቶች መጠነኛ የጊዜ ማሻሻያ (ማለትም በተለያዩ ምክንያቶች መጠይቁን ሞልተው ማስረከብ ላልቻሉ እስከ መጋቢት ወር መጨረሻ መጠይቁ ተሞልቶ እንዲመለስ ማድረግ) አስፈላጊ ሆኗል፡፡ የመጀመሪያው በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ ምክንያት በአዲስ አበባ ለዚህ ጥናት ምላሽ መስጠት የነበረባቸው መላሾች የሚሰሩባቸው ተቋማት ዝግ ሆነው መቆየታቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የቂርቆስ ክፍለከተማ አመራር አካላት መጠይቁን ከየወረዳው አሰባስበው ለማምጣት ሳይችሉ መቅረታቸው ነው፡፡ ለዚህም ዋንኛ ምክንያታቸው መጠይቁን የወሰዱት ወረዳዎች መጠይቁን በአግባቡ አለመያዛቸው ነው፡፡ ሆኖም ለዚህ ጥናት ከባለድርሻ አካላትም ሆነ ከማዕከልና ከክፍለከተሞች የተሰበሰበው መረጃ፣ ከዚህ በታች በሠንጠረዥ 1 እንደተመለከተው፣ የጽሁፍ መጠይቁን እንዲሞሉ መጠይቁ ከተሰጣቸው 187 መላሾች ውስጥ ከግማሽ በላይ (ማለትም 145) መላሾች በአግባቡ ሞልተው ስለመለሱ በአግባቡ ሞልተው ያልመለሱ መላሾች ድክመት በጥናቱ ውጤት ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ ዝቅተኛ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡         

በመሰረቱ ከላይ እንደተገለጸው የጽሁፍ መጠይቅ እና የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ/ጋይድ ቡክ/ የወሰዱ መላሾች /Respondents/ ብዛት 187 ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 145ቱ በአግባቡ ተሞልተውና ለጥናት ቡድኑ ተመልሰው ለጥናታዊ ሥራው ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

 

 1. የጥናቱ ግኝቶች ትንተና (Results and discussions)[1]
  1. በመጽሐፉ ውስጥ አሁን የሚታዩ ጠንካራ ጎኖችን በተመለከተ[2]
   1. ከአዲስ አበባ ተፈጥሮአዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ

ከላይ የቀረበው ዝርዝር መረጃ እንደሚያመለክተው ከአዲስ አበባ ተፈጥሮአዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ መጽሐፉ ያሉትን ጠንካራ ጎኖች በተመለከተ 82 ጥቆማዎች ከመላሾቹ ቀርበዋል፡፡

ከአብዛኛዎቹ (60% በላይ) አስተያየቶች መገንዘብ እንደሚቻለው መጽሐፉ አዲስ አበባ ያሏትን ተፈጥሮአዊ የቱሪስት መስህቦች በቂ በሚባል ደረጃ ማስተዋወቅ ችሏል፡፡ እነዚህም ተፈጥሮአዊ /መልክዓምድራዊ/ አቀማመጥዋ፣ የአየር ንብረቷ፣ መናፈሻዎችዋና ዋሻዎችዋ /ለምሳሌ፣ እንጦጦ ተራራ፣ ጉለሌ እፅዋት ማእከል እነ ዋሻ ሚካኤል፣ የቦሌ ክፍለከተማ ዋሻዎች፣ ፍል ውሀ፣ፒኮክ መናፈሻ፣ ሐምሌ19 መናፈሻ፣ የአዕዋፍ መገኛ ስፍራዎች  የመሳሰሉት/ መጠቀሳቸው በጥንካሬ ማሳየነት ተገልጸዋል፡፡ በመሰረቱ ከቢሮ ሃላፊዎችና ከተመረጡ የቢሮው ሙያተኞች ጋር የተደረጉ ሶስት ኢ-መደበኛ ውይይቶች፣ በግንቦት 9/2009 ዓ.ም ለአንድ ሰዓት ያክል በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ከሁለት ሙያተኞች ጋር /የቢሮውን የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ የሕትመት ሥራ ጥራት ደረጃን በተመለከተ/ የተደረገ ውይይት ይህንኑ መረጃ ያረጋግጣሉ፡፡ በተጨማሪም ከላይ በተገለጹት አስተያየቶች አንዳንድ መላሾች የገለጹት ሃሳብ አትኩሮት የሚገባው ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የሚከተሉትን አሰተያየቶች ቁጥሮቻቸውን /ኮዶቻቸውን/ መሰረት በማድረግ ማየት ይቻላል፡፡

 • ከሞላ ጎደል የተፈጥሯዊ ቦታዎችን ለማሟላት ተችሏል፡፡ ነገር ግን እንደ ዋሻ እና የመሳሰሉት ላይም ጥናት ቢደረግና ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ቢሰጠው የተሻለ መረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡ (63)
 • ከሞላ ጎደል የተፈጥሯዊ ቦታዎችን ለማሟላት ተችሏል፡፡ ነገር ግን እንደ ዋሻ እና የመሳሰሉት ላይም ጥናት ቢደረግና ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ቢሰጠው የተሻለ መረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡ (75)
 • በዙሪያችን ይኖራሉ ብለን የማናስባቸውን መስህቦች የያዘ ጋይድ ቡክ ነው ፡፡ (82)

 

በጥቅሉ፣ ጥቂት እርስበርስ ተቃራኒ የሆኑ ሃሳቦችን/ጥቆማዎችን በመተው፣ ከላይ ከቀረቡት አብዛኛዎቹ ጥቆማዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ በቂ በሆነ ደረጃ፣ መጽሐፉ የአዲስ አበባን ተፈጥሮአዊ የቱሪስት መስህቦች ለቱሪስቶች/ጎብኚዎች ከማስተዋወቅ አኳያ፣ ሳቢ በሆነ /ስዕላዊ/ መንገድና ግልጽ ዓለማቀፋዊ ቋንቋ መረጃ ማቅረብ የተቻለበት ቢሆንም ከምሉዕነት አንጻር ግን /በተለይ ዋሻዎችን በዝርዝር መረጃ አስደግፎ በማቅረብ ረገድ/ ውስንነቶች ያሉበት መሆኑን ነው፡፡  

 1. ከአዲስ አበባ ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ

ከአዲስ አበባ ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ ከላይ የተዘረዘሩትን 96 ነጥቦች መሰረት በማድረግ በአብዛኛው (ከ70% በላይ) ከመጽሐፉ ጠንካራ ጎን አንጻር ከቀረቡት ጥቆማዎች/አስተያየቶች መገንዘብ የሚቻለው፣ አንዳንድ መስህቦች ባይካተቱበትም፣ በቂ በሆነ ደረጃ በመጽሐፉ የአዲስ አበባ ከተማ ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች በጥሩ አገላለፅና በዝርዝር መቀረባቸውን ነው፡፡ ከቢሮ ሃላፊዎችና ከተመረጡ የቢሮው ሙያተኞች ጋር የተደረጉ ሶስት ኢ-መደበኛ ውይይቶች፣ በግንቦት 9/2009 ዓ.ም ለአንድ ሰዓት ያክል በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ከሁለት ሙያተኞች ጋር /የቢሮውን የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ የሕትመት ሥራ ጥራት ደረጃን በተመለከተ/ የተደረገ ውይይት ይህንኑ መረጃ ያረጋግጣሉ፡፡     

 1. ከአዲስ አበባ ባህላዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ
 2. አበባ ባህላዊ የቱሪስት መስህቦች አንጻር የመጽሐፉን ጥንካሬ በመተቸት ከቀረቡ 85 ዋንኛ አስተያየቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ (ከ80%) የሚበልጡት ጥቆማዎች የባህላዊ መስህቦችን ከታሪካዊ ዳራቸው ጋር /በአመዛኙ ከበቂ ማሳያዎቻቸው ጋር/ አበረታች በሆነ መልኩ ሙሉ በሙሉ ባይባልም /ለምሳሌ፣ ሁሉም ታዋቂ የባህል ምግብ ቤቶች ባይጠቀሱም/ በመጽሐፉ ማካተት መቻሉን ያመላክታሉ፡፡ ሆኖም መጽሐፉን በሚገባ ከአለማንበብ ጋር ተያይዞ የተሰጡ አስተያየቶችም ከአስተያየቶቹ መካከል ተገኝተዋል፡፡ ለምሳሌ፣ የሚከተለውን መሰረተ-ቢስ አስተያየት መጽሐፉን ከገጽ 18 እስከ 21 በሚገባ የአነበበ እና የመስቀል ደመራና የጥምቀት በዓል በሚገባ በመጽሐፉ ውስጥ መገለጻቸውን ያየ ሰው አይቀበለውም፡፡
 • የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ኢሬቻ ፕሮሞት  በመደረጉ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ነገር ግን ከመስቀል ደመራ ያልተናነሰ እና እምቅ ታሪክ ያለው የጥምቀት በዓል ዓለምን ትኩረት እንዲሰጠው እና በዩኔስኮ ቅርስነት እንዲመዘገብ በዚህ መፅሀፍ እንኳን ፕሮሞት ሲደረግ አላየሁም፡፡ (78)

በተቃራኒው ደግሞ የሚከተለውን አስተያየት ማየት ይቻላል፡፡ 

 • ጥምቀትና መስቀልን የመሳሰሉ ሃይማኖታዊ በዓላት በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ የተገለጸበት ሁኔታና የተሰጡት ማብራሪያዎች ጥሩ ናቸው:: (53) 

ከዚሁ ጋር ተያይዞም የሚከተለው አስተያየት መረጃና ማስረጃን በሚገባ ከአለማገናኘት ችግር ወይም መጽሐፉን በሚገባ ከአለማንበብ ጋር የተያያዘ ችግር ውጤት መሆኑን የመጽሐፉን የተለያዩ ገጾች /ገጽ 7 እስከ 21/ በመመልከት ብቻ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

 • ዲስ አበባ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያ ከተማ እንደመሆኑ መጠን ይህን የሚገልፅ ህብረ ብሄራዊነትን የሚያንፀባርቅ እሴት እንደ ባህላዊ መስህብ አልተካተተም፡፡ ይህ ቢስተካከከል ጥሩ ነው፡፡ (77) 

   በአጭሩ፣ በማሳያነት በቁጥር 77 እና 78 ከተገለጹት አስተያየቶች መረዳት እንደሚቻለው አንዳንድ መረጃ ሰጪዎች በሚገባቸው ልክ በቁርጠኝነት መረጃ የመስጠት ኃላፊነታቸውን አለመወጣቸውን ጥናቱ ያመላክታል፡፡ ይሁን እንጂ ከአዲስ አበባ ባህላዊ የቱሪስት መስህቦች አንጻር መጽሐፉ አዲስ አበባን ለሚጎበኙ ሁሉ በበቂ ደረጃ፣ ከበቂ ማስረጃና ፎቶግራፍዎች ጋር፣ መረጃ መያዙን አብዛኛዎቹ አስተያየቶች መጠቆማቸውን ማየት ይቻላል፡፡ ከዚህ አኳያ ከቢሮ ሃላፊዎችና ከተመረጡ የቢሮው ሙያተኞች ጋር የተደረጉ ሶስት ኢ-መደበኛ ውይይቶች፣ በግንቦት 9/2009 ዓ.ም ለአንድ ሰዓት ያክል በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ከሁለት ሙያተኞች ጋር /የቢሮውን የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ የሕትመት ሥራ ጥራት ደረጃን በተመለከተ/ የተደረገ ውይይት ይህንኑ በጠንካራ ጎን የተገለጸ መረጃ ያረጋግጣሉ፡፡       

 1. የፎቶዎችና የሰንጠረዦች ጥራትንና አጠቃላይ የመጽሐፉ ዲዛየንን በተመለከተ

         በመጽሐፉ የፎቶዎች፣ የፊደላት መጠን/ፎንትና የሰንጠረዦች ጥራትን እንዲሁም የመጽሐፉ ዲዛየንን በተመለከተ ከአብዛኛዎቹ አስተያየቶች መገንዘብ እንደተቻለው በከፍተኛ ደረጃ የማሻሻያ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ፣ ሆኖም አሁን በመጽሐፉ የሚታየው ጠንካራ ጎን የፎቶዎች ብዛትና ተዛማጅነት ጥሩ መሆኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ነገር መላሾች የሰጡት አስተያየት ሁሉ ተቀባይነት እንዳሌለው ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የግል እንጂ ሳይንሳዊ ያልሆነ ፍላጎት የማይታይበትን plate ከማለት ይልቅ picture ቢባል በሚል ከቋት አንድ መረጃ ሰጪዎች መካከል በቁጥር 4 የተመለከተው አስተያየት መቅረቡ ትክክል አይደለም፡፡ ሳይንሳዊ ትርጉምንና አሰራርን መሰረት ያደረገው ቃል “Plate” ነው፡፡ ለቱሪስት መመሪያ መጽሐፉ ይመጥናል፡፡ ትርጉሙም በእንግሊዝኛ መዝገበቃላት “illustration or photograph in a book, especially on glossy or coated paper” /በሚያንጸባርቅ፣ በተለበደ ወይም ግሎሲ ወረቀት ላይ ያለ መግለጫ ወይም ፎቶ/ ማለት ነው፡፡ በተቃራኒው “picture” ማለት “photograph or something drawn or painted” /ፎቶ ወይም የተሳለ ነገር/ ነው፡፡ አሻሚ ከመሆኑም በላይ ለቱሪስት መመሪያ መጽሐፉ ፎቶዎች የሚመጥንና የተለመደ አጠቃቀም እንዳልሆነ መገመት ይቻላል፡፡ በጥቅሉ፣ በመጽሐፉ የፎቶዎች፣ የፊደላት መጠን/ፎንትና የሰንጠረዦች ጥራትን እንዲሁም የመጽሐፉ ዲዛየንን በተመለከተ በአብዛኛዎቹ አስተያየቶች መሰረት መጽሐፉ ከጥንካሬው ይልቅ ጉድለቱ ጎልቶበት የታየ ስለሆነ በከፍተኛ ደረጃ የማሻሻያ ሥራ የሚያሻው መጽሐፍ ነው፡፡  

 1. የቋንቋ ግልጽነት እና የይዘት የአመክንዮ ፍሰት /logical flow of issues/

የቋንቋ ግልጽነት እና የይዘት የአመክንዮ ፍሰት /logical flow of issues/ ዝርዝር ጉዳዮችንና መገለጫቸውን በተመለከተ ከላይ የቀረቡት 72 አስተያየቶች ከመረጃ ሰጭዎች ተገኝተዋል፡፡ አብዛኛዎቹ (85% በላይ) አስተያየቶች በመጽሐፉ ውስጥ የቋንቋ ግልጽነት እና የይዘት የአመክንዮ ፍሰት ማሳያዎች በጥሩ ሁኔታ መቅረባቸውን ያመለክታሉ፡፡ በተለይ የሚከተሉት ጥቆማዎች ልዩ ትኩረት ይሻሉ፡፡

 • [መጽሐፉ] ቋንቋዉ በአማርኛ ቢሆን ለአገር ዉስጥ ሰዎች ጥሩ ነዉ:: (27)
  • [በመጽሐፉ ውስጥ] የአዲስ አበባ ነዋሪ ቁጥር 3.2 የሚለው አሁን የሚገመተው ከ5 ሚሊዎን በላይ ነው፡፡ (42)
  • [በመጽሐፉ] ለአገር ውስጥ ቱሪዝም በአማርኛ ቋንቋ መዘጋጀት ቢችል ጥሩ ነው፡፡ (43)
   1. የአዲስ አበባን የልማት፣ የሰላምና የዲሞክራሲ ገጽታዎች በተመለከተ
 • አበባን የልማት፣ የሰላምና የዲሞክራሲ ገጽታዎችን በተመለከተ የመጽሐፉ ይዘት በአብዛኛው ጠንካራ ጎን እንዳለው አብዛኛዎች (ከ85% በላይ) አስተያየቶች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር በተለይ ተቻችሎ በከተማዋ የመኖር ባህልን እና ተያያዥ የአዲስ አበባን የልማት፣ የሰላምና የዲሞክራሲ ግብአቶችን ተንከባክቦ በመጠበቅ ለከተማዋ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ አወንታዊ ሚና እንዳለው አስተያየቶቹ ያመለክታሉ፡፡
  1. በመጽሐፉ ውስጥ አሁን የሚታዩ ክፍተቶችን/ደካማ ጎኖችን በተመለከተ
   1. ከአዲስ አበባ ተፈጥሮአዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ
 • አበባ ተፈጥሮአዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ ከመረጃ ሰጪዎች ከተገኙት የመጽሐፉን ጉድለቶች የሚመለከቱ 76 ጥቆማዎች መረዳ የሚቻለው ጉድለቶቹ በዋናነት የመረጃ ምሉዕነት /በቂ አለመሆን/፣ ዝርዝርነት /ለምሳሌ፣ አዕዋፋትንና ጅብን የማድነቅ ቱሪዝም መረጃ በዝርዝር አለመቅረብ/ በተመለከተ፣ ሳቢነት /መስህቦቱን ጥራት ባላቸው ፎቶዎች የማስደገፍ ጥረት አናሳነት/ ላይ እንዲሁም ማሳሰቢያዎችን /ለምሳሌ፣ ከቋት 8 ጥቆማዎች ጋር በተያያዘ መገመት እንደሚቻለው/ በማስተላለፍ ላይ ትኩረት ያረጉ ናቸው፡፡ ሁሉም አስተያየቶች ለቀጣይ የመጽሐፉ ሕትመት ሥራ መልካም ግብዓቶች ቢሆኑም ሁሉንም እንዳሉ ወስዶ መጠቀም ግን አይቻልም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በዋናነት የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ ስለሁሉም የአንድ ከተማ /አገር/ የቱሪስት መስህቦች ዝርዝር /ሰፊ/ መረጃ የሚሰጥበት ሳይሆን አንድን ቱሪስት እያጓጓ ስቦ ወደ መስህቦች በመውሰድ ዝርዝር መረጃዎችን ከየመስህቡ ሥፍራ እንዲያገኝ የሚያስችል መሳሪያ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ሀቅ ታሳቢ በማድረግ ከመላሾች የተሰጡ አስተያየቶችን /በልካቸው እየተሰፈሩ/ በቀጣይ መጠቀም ያሻል፡፡ ለአብነት ያክል በቅድሚያ ሊወሰዱ ከሚገባቸው አስተያየቶች መካከል የሚከተሉትን አስተያየቶች በቀጣይ ማካተት ይቻላል፡፡
 • በአዲስ አበባ ያሉ የአእዋፍ  ዝረያዎች እንዴት እንደሚጉበኙ አልተጠቆመም፡፡ ነገር ግን እነዚህ በአንድ አካባቢ በተለይም በእንጦጦና በጉለሌ የእፅዋት ማዕከል የሚገኙ በመሆኑ ማስተዋወቅ ይቻል ነበር፡፡ (2)
 • ጅብን የማድነቅ /hyena watching/ ቱሪዝም እንጦጦ አካባቢ ማሳየት ይቻላል፡፡      (24)
 • የፓርኮች አገልግሎት ቢጠቀስ፡፡ (25)
 • ቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 12 ያለ ገዳም መካተት ነበረበት፡፡ (30)
 • የጉለሌ እጽዋእት ማእከል አልተገለጸም፡፡ (44)
 • የፓርኮች አገልግሎት አልተጠቀሰም፡፡ (47)
 • በመፅሀፉ በአብዛኛው ከተፈጥሮአዊ ይልቅ በሰው ሰራሽ ላይ የተኮረ መሆኑ በድክመት

    የሚታይ ነው፡፡ (60)

 • በተለይ በየቦታው ያሉት የመናፈሻ ፓርኮች የጫት መቃሚያና የሲጋራ ማጨሻ ስፍራነት ተለውጠዋል፡፡በተለይ ሀምሌ 19 ከመናፈሻነት እየወጣ ይገኛል፡፡ስለሆነም ጥብቅ ቁጠጠር ቢደረግ፡፡ (63)
 •  የከተማዋን ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦችን በየክፍለ ከተማዎች በንፅፅር ማስቀመጥ     

   አለመቻሉ፤ (75)

 1. ከአዲስ አበባ ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ

ከስምንቱም ቋቶች የተገኙት አብዛኛዎቹ መረጃዎች ከአዲስ አበባ ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ የሚያመላክቱት የመጽሐፉ ጉድለት ማሳያዎች የመረጃዎች ዝርዝር አለመሆንን፣ ሁሉን አቀፍ አለመሆንንና ተገቢና ሳቢ በሆኑ ፎቶዎች አለመደገፍን ያሳያሉ፡፡ ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ አሰተያየቶችና ምክረሃሳቦች ለመጽሐፉ ቀጣይ የሕትመት ሥራ ጥሩ ግብዓቶች ቢሆኑም አንዳንድ አስተያየቶች ግን መጽሐፉን በሚገባ ከአለማንበብና የአዲስ አበባን የቱሪስት መስህቦች ብቻ መጽሐፉ ማሳየት አለበት ከሚል ተቀባይነት ያሌለው /የከተማዋን ዋና ከተማነትና ወደ ሌሎች የቱሪስት መስህቦች ለሚሄዱ ቱሪስቶች የምትጫወተውን ቱሪስቶችን በቅድሚያ የመቀበልና የማስተናገድ ሚና ያላገናዘበ/ አስተያየት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም መሰረተ ቢስ ጥቆማዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፣ የሚከተሉትን አስተያየቶች በተመለከተ መጽሐፉን በሚገባ ያነበበ ሰው በቂና ዝርዝር መረጃዎችን በገጽ 17 ፎቶ 13 /የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን ቪላ አልፋ ፎቶ ያየ/፣ በገጽ 95 አዲስ አበባ በዩኔስኮ የተመዘገቡ መስህቦች መግቢያ በር በሚል ርዕስ የተጠቀሰውን መረጃ የተገነዘበ አንባቢ/ ስለሚያገኝ ሊቀበላቸው አይገባም፡፡   

 • የሜ/አ/አፈወርቅ ተክሌ ቤት ቢካተት፡፡ (26)
 • ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች ተብለው መፅሀፉ ላይ የተገለፁት በአብዛኛው አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ብቻ መሆናቸው፡፡ ለምሳሌ ሶፍ ኡመር ዋሻ መፅሀፉ ውስጥ ቢካተት እናም ሌሎች፡፡ (66)
 • መጽሃፉ በሽፋኑ የተሰጠው ስያሜና በውስጡ ስለ ጎንደር ሀረርና አክሱም ይዘረዝራል ይህ ደግሞ ትክክል አይደለም፡፡ (60)
  1. ከአዲስ አበባ ባህላዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ

     ከላይ በዝርዝር በቀረቡት ነጥቦች /በአብዛኛው የተጠቀሱ ነጥቦች/ መሰረት ከአዲስ አበባ ባህላዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ በመጀመሪያ ደረጃ መፍትሄ የሚያሻቸው ጉዳዮች/ከፍተቶች የመስህቦች ተሟልቶ አለመጠቀስና ዝርዝር መግለጫዎች አለመቅረባቸው ናቸው፡፡ በምሳሌነት የተጠቀሱት የብሔር ብሔረሰቦች የተለያዩ ልማዶች ወጉችና ባህሎች የሚያስተዋውቅ ጠለቅ ያለ ማብራሪያ፣ ስለ ኢትዮጽያ ካላንደር ታሪካዊ ሁኔታየየብሄረሰቦቹ ባህላዊ እሴቶችን የሚገልጹ ባህላዊ ትውፊቶች ስርኣቶች ቅርሶች ጌጣጌጦች ባህላዊ እቃዎች፣ታዋቂ የባህል ምግብ ቤቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህንና ሌሎችንም ጉዳዮች በመጽሐፉ ቀጣይ የሕትመት ሥራ በማካተት ከፍተኛ የማሻሻያ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ አብዛኛዎቹ አስተያየቶች ጠቁመዋል፡፡    

 1. የፎቶዎችና የሰንጠረዦች ጥራትንና አጠቃላይ የመጽሐፉ ዲዛየንን በተመለከተ

የፎቶዎችና የሰንጠረዦች ጥራትንና አጠቃላይ የመጽሐፉ ዲዛየንን በተመለከተ በአመዛኙ ጉድለቶች እንዳሉ ከቀረቡት 76 አስተያየቶች መረዳት ተችሏል፡፡ ከቢሮ ሃላፊዎችና ከተመረጡ የቢሮው ሙያተኞች ጋር የተደረጉ ሶስት ኢ-መደበኛ ውይይቶች፣ በግንቦት 9/2009 ዓ.ም ለአንድ ሰዓት ያክል በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ከሁለት ሙያተኞች ጋር /የቢሮውን የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ የሕትመት ሥራ ጥራት ደረጃን በተመለከተ/ የተደረገ ውይይት ይህንኑ ጉድለት አመላክቷል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የመጽሐፉ ገጾች በቀላሉ የሚገነጠሉ መሆናቸው፣ የፅሁፎቹ መጠን አናሳ መሆንና የመጽሐፉ መጠን ትንሽ አለመሆን በዋናነት ተጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪ ማስታወሻነት የተጠቀሱት የሚከተሉት ነጥቦችም ልዩ ትኩረት ይገባቸዋል፡፡

 • የሰማዕታት ሀውልት 6ኪሎ እንደሚገኝ ቢገለፅ? ሀውልቱ ለምንድነው ባለ ሦስት ጉን የሆነው?   ቢገለፅ /ይመስለኛል የ3 ቀን ጭፍጨፋውን ለመግለፅ ነው ይባላል፡፡/
 • አብነ ጰጥሮስ መታሰቢያ ሃውልት የበባቡር ግንባታው ከተጠናቀቀ በኃላ መቼ ነው እንደገና የቆመው? 
 • የድል ሃውልት ለምንድነው መግቢያ በሮች ያሉት?
 • የአበበ ቢቂላ እና የማሞ ወልዴ ሀውልት መቼ ቆመ?
 • የቦብ መርሌይ ሃውልት መቼ ቆመ? የመቆሙ ፋይዳ ምንድን ነው?
 • የካልሄን በህሞ ሃውልት መቼ ቆመ?
  1. የቋንቋ ግልጽነት እና የይዘት የአመክንዮ ፍሰት /logical flow of issues/

በዝርዝር ከቀረቡት 57 ጥቆማዎች በአብዛኛው በመጽሐፉ የሚታየው የቋንቋ አጠቃቀም ግልጽና እንግሊዝኛ ተናጋሪ ለሆኑ ቱሪስቶች ምቹ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም ቢታዩ በሚል ከተጠቀሱት አንዳንድ ነጥቦች (ለምሳሌ፣ቋንቋው የበለጠ ቀለል ባለ መልኩ መቅረብ ቢችል) ባሻገር በፈረንሳይና በሌሎችም የውጭ ቋንቋዎች እንዲሁም በአማርኛም ጭምር ሊዘጋጅ የሚገባው መሆኑም መገለጹ ትኩረት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ከቢሮ ሃላፊዎችና ከተመረጡ የቢሮው ሙያተኞች ጋር የተደረጉ ሶስት ኢ-መደበኛ ውይይቶች፣ በግንቦት 9/2009 ዓ.ም ለአንድ ሰዓት ያክል በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ከሁለት ሙያተኞች ጋር /የቢሮውን የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ የሕትመት ሥራ ጥራት ደረጃን በተመለከተ/ የተደረገ ውይይት ይኼው አስተያየት ተገኝቷል፡፡

 1. የአዲስ አበባን የልማት፣ የሰላምና የዲሞክራሲ ገጽታዎች በተመለከተ

     ከጉድለት አንጻር የአዲስ አበባን የልማት፣ የሰላምና የዲሞክራሲ ገጽታዎች በተመለከተ ከቀረቡት 42 ነጥቦች በአብዛኛው መገንዘብ የተቻለው መጽሐፉ ጥሩ መረጃ የያዘ ቢሆንም አንዳንድ ግነቶችን በማውጣትና ማብራሪያዎችንም በመጨመር ሊታይ እንደሚገባው ነው፡፡ ለዚህም የሚከተሉትን ነጥቦች በምሳሌነት ማየት ይቻላል፡፡ 

 • አዲስ አበባ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ፈርሳ እየተገነባች ያለች ከተማ በመሆኑ ምክንያት ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሀይማኖታዊና ተፈጥሯዊ መስህቦቻችንን የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ልማቱን ማስቀጠልና እስካሁንም ላከናወናቸው የሰላምና ዴሞክራሲ ተግባራቶች ሊመሰገን ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን ከዚህ አሁን ካለንበት በበለጠ መሰራት ይጠበቅበታል፡፡ ብዙ ብዙ ያልተሰሩ ሥራዎች እንዳሉ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ አመላካች መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ (11) 
 • ያልተሰሩ ስራዎችን እንደተሰሩ አድርጎ ማስቀመጥ ስራውን ያወርደዋል፡፡ ለምሳሌ የኢ/ያ ንግድ ባንክ ህንጻ፤ (28)
 • በሃገር ውስጥ የነበረው አለመረጋጋት የመንግስትም ለዘርፉና ለወቅታዊ ችግሮቹ አፋጣኝ መፍትሄ አለመስጠቱ በመጽሃፉ አልተዳሰሰም፡፡ (29)
 • የልማት የሰላምና ዲሞክራሲ ገፅታዎችን [በተመለከተ] ያለው ጉድለት የአዲስ አበባን ከተማ ብቻ መግለፅና በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙትን ያላካተተ መሆን፡፡ (43)
 1. የማጠቃለያና የመፍትሄ ሃሳቦች (Conclusions and recommendations)

የዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ በዋናነት መሰረት ያደረገው ሁለት ጥቅል ዓላማዎችን (General objectives) ነው፡፡ እነዚህም፣ 1ኛ/ የ2009 ዓ.ም የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ ይዘትንና ዲዛየንን ማሻሻል፣ 2ኛ/ 2009 ዓ.ም የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ ለአዲስ አበባ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ያለውን አወንታዊ ሚና ማሳዳግ የሚሉ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ሶስት ዝርዝር ዓላማዎችን (Specific objectives) ታሳቢ በማድረግ ጥናቱ ተካሂዷል፡፡ እነዚህም፣ 1ኛ/ 2009 ዓ.ም የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ ይዘትንና ዲዛየንን ከማሻሻል አንጻር በመጽሐፉ ውስጥ አሁን የሚታዩ ጠንካራ ጎኖችን እና ክፍተቶችን/ደካማ ጎኖችን በዝርዝር መረጃዎች መሰረት መተንተን፣ 2ኛ/ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የ2009 ዓ.ም የዓለም ቱሪዝም ቀን የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ ለአዲስ አበባ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ያለውን አወንታዊ ሚና ከማሳዳግ አንጻር በጥናቱ የተገኙ መረጃዎችን ውጤታማነት ማጎልበት3ኛ/ የጥናቱን ውጤቶች መነሻ በማድረግ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የ2009 ዓ.ም የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ በተሻለ መልኩ የሚዘጋጅባቸውን አማራጮች ማመላከት ናቸው፡፡

ከዚህ በታች የጥናቱን ጥቅልና ዝርዝር ዓላማዎችን መሰረት በማድረግ የማጠቃለያና የመፍትሄ ሃሳቦች (Conclusions and recommendations) በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

 1. የማጠቃለያ ሃሳቦች (Conclusions)

ከላይ በመረጃ ትንታኔ ክፍል በተጠቀሱት አብዛኛዎቹ ዝርዝር ማሳያዎች መሰረት መጽሐፉ ምንም እንኳን የተወሰኑ ጉድለቶች ቢኖሩትም በተጠቃሚዎቹ ላይ ሊያሳድር የሚችለው /የአዲስ አበባን የቱሪዝም ሀብቶች የማሳወቅ አቅም/ ተጽዕኖ አወንታዊ ነው፡፡ ይህም በአጭሩ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

 1. በመጽሐፉ ውስጥ አሁን የሚታዩ ጠንካራ ጎኖችን በተመለከተ
  1. ከአዲስ አበባ ተፈጥሮአዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ
 • 82 ጥቆማዎች ከመላሾቹ ቀርበዋል፡፡
 • ከአብዛኛዎቹ (60% በላይ) አስተያየቶች መገንዘብ እንደሚቻለው መጽሐፉ አዲስ አበባ ያሏትን ተፈጥሮአዊ የቱሪስት መስህቦች በቂ በሚባል ደረጃ ማስተዋወቅ ችሏል፡፡ እነዚህም ተፈጥሮአዊ /መልክዓምድራዊ/ አቀማመጥዋ፣ የአየር ንብረቷ፣ መናፈሻዎችዋና ዋሻዎችዋ /ለምሳሌ፣ እንጦጦ ተራራ፣ ጉለሌ እፅዋት ማዕከል እና ዋሻ ሚካኤል፣ የቦሌ ክፍለከተማ ዋሻዎች፣ ፍል ውሀ፣ፒኮክ መናፈሻ፣ ሐምሌ19 መናፈሻ፣ የአዕዋፍ መገኛ ስፍራዎች የመሳሰሉት/ መጠቀሳቸው በጥንካሬ ማሳየነት ተገልጸዋል፡፡
 • ከሞላ ጎደል የተፈጥሯዊ ቦታዎችን ለማሟላት ተችሏል፡፡ ነገር ግን እንደ ዋሻ እና የመሳሰሉት ላይም ጥናት ቢደረግና ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ቢሰጠው የተሻለ መረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡
 • በአዲስ አበባ ይኖራሉ በሚል ያልታሰቡ አዳዲስ መረጃዎችን ተፈጥሮአዊ መስህቦችን በተመለከተ የያዘ ጋይድ ቡክ ነው፡፡ 
 • በቂ በሆነ ደረጃ፣ መጽሐፉ የአዲስ አበባን ተፈጥሮአዊ የቱሪስት መስህቦች ለቱሪስቶች/ጎብኚዎች ከማስተዋወቅ አኳያ፣ ሳቢ በሆነ /ስዕላዊ/ መንገድና ግልጽ ዓለማቀፋዊ ቋንቋ መረጃ ማቅረብ የተቻለበት ቢሆንም ከምሉዕነት አንጻር ግን /በተለይ ዋሻዎችን በዝርዝር መረጃ አስደግፎ በማቅረብ ረገድ/ ውስንነቶች ያሉበት መሆኑን ነው፡፡  
  1. ከአዲስ አበባ ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ
 • 96 ጥቆማዎች ከመላሾች ቀርበዋል፡፡
 • አንዳንድ መስህቦች ባይካተቱበትም፣ መስህቦች በቂ በሆነ ደረጃ፣ በጥሩ አገላለፅና በዝርዝር ቀርበዋል፡፡     
  1. ከአዲስ አበባ ባህላዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ
 • 85 ጥቆማዎች ከመላሾች ቀርበዋል፡፡
 • አብዛኛዎቹ (ከ80% የሚበልጡት) ጥቆማዎች የባህላዊ መስህቦችን ከታሪካዊ ዳራቸው ጋር /በአመዛኙ ከበቂ ማሳያዎቻቸው ጋር/ አበረታች በሆነ መልኩ ሙሉ በሙሉ ባይባልም /ለምሳሌ፣ ሁሉም ታዋቂ የባህል ምግብ ቤቶች ባይጠቀሱም/ በመጽሐፉ ማካተት መቻሉን ያመላክታሉ፡፡ ሆኖም መጽሐፉን በሚገባ ከአለማንበብ ጋር ተያይዞ የተሰጡ አስተያየቶችም ከአስተያየቶቹ መካከል ተገኝተዋል፡፡ ለምሳሌ፣ የሚከተለውን መሰረተ-ቢስ አስተያየት መጽሐፉን ከገጽ 18 እስከ 21 በሚገባ የአነበበ እና የመስቀል ደመራና የጥምቀት በዓል በሚገባ በመጽሐፉ ውስጥ መገለጻቸውን ያየ ሰው አይቀበለውም፡፡ ይኼውም፣ 1ኛ/ የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ኢሬቻ ፕሮሞት  በመደረጉ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ነገር ግን ከመስቀል ደመራ ያልተናነሰ እና እምቅ ታሪክ ያለው የጥምቀት በዓል ዓለምን ትኩረት እንዲሰጠው እና በዩኔስኮ ቅርስነት እንዲመዘገብ በዚህ መፅሀፍ እንኳን ፕሮሞት ሲደረግ አላየሁም የሚል ጥቆማ ነው፡፡ (78) በተቃራኒው ደግሞ የሚከተለውን አስተያየት ማየት ይቻላል፡፡ 2ኛ/ ጥምቀትና መስቀልን የመሳሰሉ ሃይማኖታዊ በኣላት በዩኔስኮ እንደተመዘገቡ የተገለጸበት ሁኔታና የተሰጡት ማብራሪያዎች ጥሩ ናቸው:: (53) [3] ከዚሁ ጋር ተያይዞም የሚከተለው አስተያየት መረጃና ማስረጃን በሚገባ ከአለማገናኘት ችግር ወይም መጽሐፉን በሚገባ ከአለማንበብ ጋር የተያያዘ ችግር ውጤት መሆኑን የመጽሐፉን የተለያዩ ገጾች /ገጽ 7 እስከ 21/ በመመልከት ብቻ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይኼውም፣ 3ኛ/ ዲስ አበባ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያ ከተማ እንደመሆኑ መጠን ይህን የሚገልፅ ህብረ ብሄራዊነትን የሚያንፀባርቅ እሴት እንደ ባህላዊ መስህብ አልተካተተም፡፡ ይህ ቢስተካከከል ጥሩ ነው በሚል የተገለጸ ነው፡፡ (77)
 • በማሳያነት በቁጥር/ኮድ 77 እና 78 ከተገለጹት አስተያየቶች መረዳት እንደሚቻለው አንዳንድ መረጃ ሰጪዎች በሚገባቸው ልክ በቁርጠኝነት መረጃ የመስጠት ኃላፊነታቸውን አለመወጣቸውን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከአዲስ አበባ ባህላዊ የቱሪስት መስህቦች አንጻር መጽሐፉ አዲስ አበባን ለሚጎበኙ ሁሉ በበቂ ደረጃ፣ ከበቂ ማስረጃና ፎቶግራፍዎች ጋር፣ መረጃ መያዙን አብዛኛዎቹ አስተያየቶች አመላክተዋል፡፡ 
  1. የፎቶዎችና የሰንጠረዦች ጥራትንና አጠቃላይ የመጽሐፉ ዲዛየንን በተመለከተ
 • 82 ጥቆማዎች ከመላሾች ቀርበዋል፡፡
 • በመጽሐፉ የፎቶዎች፣ የፊደላት መጠን/ፎንትና የሰንጠረዦች ጥራትን እንዲሁም የመጽሐፉ ዲዛየንን በተመለከተ ከአብዛኛዎቹ አስተያየቶች መገንዘብ እንደተቻለው በከፍተኛ ደረጃ የማሻሻያ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ፣ ሆኖም አሁን በመጽሐፉ የሚታየው ጠንካራ ጎን የፎቶዎች ብዛትና ተዛማጅነት ጥሩ መሆኑ ነው፡፡
 • የፎቶዎችና የሰንጠረዦች ጥራትንና አጠቃላይ የመጽሐፉ ዲዛየንን የማይመለከት ነገር ግን ተቀባይነት የሌለው አስተያየት ከቋንቋ ጋር በተያያዘ በመላሾች መቅረቡ ስለአንዳንድ መላሾች የጥንቃቄ ማነስ አመላካች ነው፡፡ ይኼውም፣ plate ከማለት ይልቅ picture ቢባል በሚል ከቋት አንድ መረጃ ሰጪዎች መካከል በቁጥር 4 የተመለከተው አስተያየት ያለቦታውም ቢሆን መቅረቡ ትክክል አለመሆኑ ነው፡፡ ሳይንሳዊ ትርጉምንና አሰራርን መሰረት ያደረገው ቃል “Plate” ነው፡፡ ትርጉሙም በእንግሊዝኛ መዝገበቃላት “illustration or photograph in a book, especially on glossy or coated paper” /በሚያንጸባርቅ፣ በተለበደ ወይም ግሎሲ ወረቀት ላይ ያለ መግለጫ ወይም ፎቶ/ ማለት ነው፡፡ በተቃራኒው “picture” ማለት “photograph or something drawn or painted” /ፎቶ ወይም የተሳለ ነገር/ ነው፡፡ ለቱሪስት መመሪያ መጽሐፉ ፎቶዎች የሚመጥንና የተለመደ አጠቃቀም እንዳልሆነ መገመት ይቻላል፡፡
 • ይሁን እንጂ፣ በጥቅሉ ሲታይ፣ በመጽሐፉ የፎቶዎች፣ የፊደላት መጠን/ፎንትና የሰንጠረዦች ጥራትን እንዲሁም የመጽሐፉ ዲዛየንን በተመለከተ በአብዛኛዎቹ አስተያየቶች መሰረት መጽሐፉ ከጥንካሬው ይልቅ ጉድለቱ ጎልቶበት የታየ ስለሆነ በከፍተኛ ደረጃ የማሻሻያ ሥራ የሚያሻው መጽሐፍ ነው፡፡  
  1. የቋንቋ ግልጽነት እና የይዘት የአመክንዮ ፍሰት /logical flow of issues/
 • 72 ጥቆማዎች ከመላሾች ቀርበዋል፡፡
 • አብዛኛዎቹ (85% በላይ) አስተያየቶች በመጽሐፉ ውስጥ የቋንቋ ግልጽነት እና የይዘት የአመክንዮ ፍሰት ማሳያዎች በጥሩ ሁኔታ መቅረባቸውን ያመለክታሉ፡፡ በተለይ የሚከተሉት ጥቆማዎች ልዩ ትኩረት ይሻሉ፡፡

1ኛ/ [መጽሐፉ] ቋንቋዉ በአማርኛ ቢሆን ለአገር ዉስጥ ሰዎች ጥሩ ነዉ:: 

    (27)

2ኛ/ [በመጽሐፉ ውስጥ] የአዲስ አበባ ነዋሪ ቁጥር 3.2 የሚለው አሁን የሚገመተው ከ5 ሚሊዎን በላይ ነው፡፡ (42)

3ኛ/ [በመጽሐፉ] ለአገር ውስጥ ቱሪዝም በአማርኛ ቋንቋ መዘጋጀት ቢችል ጥሩ ነው፡፡ (43)

 1. የአዲስ አበባን የልማት፣ የሰላምና የዲሞክራሲ ገጽታዎች በተመለከተ
 • 66 ጥቆማዎች ከመላሾች ቀርበዋል፡፡
 • የመጽሐፉ ይዘት በአብዛኛው ጠንካራ ጎን እንዳለው አብዛኛዎች (ከ85% በላይ) አስተያየቶች ይጠቁማሉ፡፡ ይኼውም ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር በተለይ ተቻችሎ በከተማዋ የመኖር ባህልን እና ተያያዥ የአዲስ አበባን የልማት፣ የሰላምና የዲሞክራሲ ግብአቶችን ተንከባክቦ በመጠበቅ ለከተማዋ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ አወንታዊ ሚና እንዳለው አስተያየቶቹ ያመለክታሉ፡፡
  1. በመጽሐፉ ውስጥ አሁን የሚታዩ ክፍተቶች/ደካማ ጎኖችን በተመለከተ
   1. ከአዲስ አበባ ተፈጥሮአዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ
 • 76 ጥቆማዎች ከመላሾች ቀርበዋል፡፡
 • በዋናነት የመረጃ ምሉዕነት /በቂ አለመሆን/፣ ዝርዝርነት /ለምሳሌ፣ አዕዋፋትንና ጅብን የማድነቅ ቱሪዝም መረጃ በዝርዝር አለመቅረብ/ በተመለከተ፣ ሳቢነት /መስህቦቱን ጥራት ባላቸው ፎቶዎች የማስደገፍ ጥረት አናሳነት/ ላይ እንዲሁም ማሳሰቢያዎችን /ለምሳሌ፣ ከቋት 8 ጥቆማዎች ጋር በተያያዘ መገመት እንደሚቻለው/ በማስተላለፍ ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥቆማዎች ናቸው፡፡ ሁሉም አስተያየቶች ለቀጣይ የመጽሐፉ ሕትመት ሥራ መልካም ግብዓቶች ቢሆኑም ሁሉንም እንዳሉ ወስዶ መጠቀም ግን አይቻልም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በዋናነት የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ ስለሁሉም የአንድ ከተማ /አገር/ የቱሪስት መስህቦች ዝርዝር /ሰፊ/ መረጃ የሚሰጥበት ሳይሆን አንድን ቱሪስት በተመረጡ ውስን ማሳያዎች እያጓጓ ስቦ ወደ መስህቦች በመውሰድ ዝርዝር መረጃዎችን ከየመስህቡ ሥፍራ እንዲያገኝ የሚያስችል መሳሪያ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ሀቅ ታሳቢ በማድረግ ከመላሾች የተሰጡ አስተያየቶችን /በልካቸው እየተሰፈሩ/ በቀጣይ መጠቀም ያሻል፡፡ ለአብነት ያክል በቅድሚያ ሊወሰዱ ከሚገባቸው አስተያየቶች መካከል የሚከተሉትን አስተያየቶች በቀጣይ ማካተት ይቻላል፡፡
 • በአዲስ አበባ ያሉ የአእዋፍ  ዝረያዎች እንዴት እንደሚጉበኙ አልተጠቆመም፡፡ ነገር ግን እነዚህ በአንድ አካባቢ በተለይም በእንጦጦና በጉለሌ የእፅዋት ማዕከል የሚገኙ በመሆኑ ማስተዋወቅ ይቻል ነበር፡፡ (2)
 • ጅብን የማድነቅ /hyena watching/ ቱሪዝም እንጦጦ አካባቢ ማሳየት ይቻላል፡፡      (24)
 • የፓርኮች አገልግሎት ቢጠቀስ፡፡ (25)
 • ቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 12 ያለ ገዳም መካተት ነበረበት፡፡ (30)
 • የጉለሌ እጽዋእት ማእከል አልተገለጸም፡፡ (44)
 • የፓርኮች አገልግሎት አልተጠቀሰም፡፡ (47)
 • በመፅሀፉ በአብዛኛው ከተፈጥሮአዊ ይልቅ በሰው ሰራሽ ላይ የተኮረ መሆኑ በድክመት

    የሚታይ ነው፡፡ (60)

 • በተለይ በየቦታው ያሉት የመናፈሻ ፓርኮች የጫት መቃሚያና የሲጋራ ማጨሻ ስፍራነት ተለውጠዋል፡፡በተለይ ሀምሌ 19 ከመናፈሻነት እየወጣ ይገኛል፡፡ስለሆነም ጥብቅ ቁጠጠር ቢደረግ፡፡ (63)
 •  የከተማዋን ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦችን በየክፍለ ከተማዎች በንፅፅር ማስቀመጥ     

   አለመቻሉ፤ (75)

 1. ከአዲስ አበባ ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ
 • 79 ጥቆማዎች ከመላሾች ቀርበዋል፡፡
 • የመረጃዎች ዝርዝር አለመሆንን፣ ሁሉን አቀፍ አለመሆንንና ተገቢና ሳቢ በሆኑ ፎቶዎች አለመደገፍን ያሳያሉ፡፡ ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ አስተያየቶችና ምክረሃሳቦች ለመጽሐፉ ቀጣይ የሕትመት ሥራ ጥሩ ግብዓቶች ቢሆኑም አንዳንድ አስተያየቶች ግን መጽሐፉን በሚገባ ከአለማንበብና የአዲስ አበባን የቱሪስት መስህቦች ብቻ መጽሐፉ ማሳየት አለበት ከሚል ተቀባይነት ያሌለው /የከተማዋን ዋና ከተማነትና ወደ ሌሎች የቱሪስት መስህቦች ለሚሄዱ ቱሪስቶች የምትጫወተውን ቱሪስቶችን በቅድሚያ የመቀበልና የማስተናገድ ሚና ያላገናዘበ/ አስተያየት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም መሰረተ ቢስ ጥቆማዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፣ የሚከተሉትን አስተያየቶች በተመለከተ መጽሐፉን በሚገባ ያነበበ ሰው በቂና ዝርዝር መረጃዎችን በገጽ 17 ፎቶ 13 /የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን ቪላ አልፋ ፎቶ ያየ/፣ በገጽ 95 አዲስ አበባ በዩኔስኮ የተመዘገቡ መስህቦች መግቢያ በር በሚል ርዕስ የተጠቀሰውን መረጃ የተገነዘበ አንባቢ/ ስለሚያገኝ ሊቀበላቸው አይገባም፡፡ 1ኛ/ የሜ/አ/አፈወርቅ ተክሌ ቤት ቢካተት፡፡ (26)፣ 2ኛ/ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች ተብለው መፅሀፉ ላይ የተገለፁት በአብዛኛው አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ብቻ መሆናቸው፡፡ ለምሳሌ ሶፍ ኡመር ዋሻ መፅሀፉ ውስጥ ቢካተት እናም ሌሎች፡፡ (66)፣ 3ኛ/መጽሃፉ በሽፋኑ የተሰጠው ስያሜና በውስጡ ስለ ጎንደር ሀረርና አክሱም ይዘረዝራል፡፡ ይህ ደግሞ ትክክል አይደለም፡፡ (60)
  1. ከአዲስ አበባ ባህላዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ
 • 68 ጥቆማዎች ከመላሾች ቀርበዋል፡፡
 • በአብዛኛው የተጠቀሱ ነጥቦች መሰረት ከአዲስ አበባ ባህላዊ የቱሪስት መስህቦች አኳያ በመጀመሪያ ደረጃ መፍትሄ የሚያሻቸው ጉዳዮች/ከፍተቶች የመስህቦች ተሟልቶ አለመጠቀስና ዝርዝር መግለጫዎች አለመቅረባቸው ናቸው፡፡ በምሳሌነት የተጠቀሱት የብሔር ብሔረሰቦች የተለያዩ ልማዶችን፣ ወጉችንና ባህሎችን የሚያስተዋውቅ ጠለቅ ያለ ማብራሪያ፣ ስለ ኢትዮጽያ ካላንደር ታሪካዊ ሁኔታየየብሄረሰቦቹ ባህላዊ እሴቶችን የሚገልጹ ባህላዊ ትውፊቶች ስርኣቶች ቅርሶች ጌጣጌጦች ባህላዊ እቃዎች፣ታዋቂ የባህል ምግብ ቤቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህንና ሌሎችንም ጉዳዮች በመጽሐፉ ቀጣይ የሕትመት ሥራ በማካተት ከፍተኛ የማሻሻያ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ አብዛኛዎቹ አስተያየቶች ጠቁመዋል፡፡    
  1. የፎቶዎችና የሰንጠረዦች ጥራትንና አጠቃላይ የመጽሐፉ ዲዛየንን በተመለከተ
 • 76 ጥቆማዎች ከመላሾች ቀርበዋል፡፡
 • በአመዛኙ ጉድለቶች እንዳሉ ከቀረቡት 76 አስተያየቶች መረዳት ተችሏል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የመጽሐፉ ገጾች በቀላሉ የሚገነጠሉ መሆናቸው፣ የፅሁፎቹ መጠን አናሳ መሆንና የመጽሐፉ መጠን ትንሽ አለመሆን በዋናነት ተጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪ ማስታወሻነት የተጠቀሱት የሚከተሉት ነጥቦችም ልዩ ትኩረት ይገባቸዋል፡፡

1ኛ/ የሠማዕታት ሀውልት 6ኪሎ እንደሚገኝ ቢገለፅ? (ይህ አስተያየት በመጽሐፉ ከገጽ 54-55 ያለውን መረጃ ያለማንበብ ችግር ውጤት ነው፡፡)

2ኛ/ ሀውልቱ ለምንድነው ባለ ሦስት ጉን የሆነው? ቢገለፅ፡፡ ይመስለኛል የ3 ቀን ጭፍጨፋውን ለመግለፅ ነው ይባላል፡፡ (ይህ መረጃ ተጣርቶ በመጽሀፉ ሊካተት ይችላል፡፡)

3ኛ/ የአቡነ ጰጥሮስ መታሰቢያ ሃውልት የባቡር ግንባታው ከተጠናቀቀ በኃላ መቼ ነው እንደገና የቆመው? (ይህ መረጃ ተጣርቶ በመጽሀፉ ሊካተት ይችላል፡፡) 

4ኛ/ የድል ሃውልት ለምንድነው መግቢያ በሮች ያሉት? (ይህ አስተያየት በመጽሐፉ ከገጽ 55-56 ያለውን መረጃ ያለማንበብ ችግር ውጤት ነው፡፡) 

5ኛ/ የአበበ ቢቂላ እና የማሞ ወልዴ ሀውልት መቼ ቆመ? (ይህ መረጃ ተጣርቶ በመጽሀፉ ሊካተት ይችላል፡፡)  

6ኛ/ የቦብ መርሌይ ሃውልት መቼ ቆመ? የመቆሙ ፋይዳ ምንድን ነው? (ይህ መረጃ ተጣርቶ በመጽሀፉ ሊካተት ይችላል፡፡) 

7ኛ/ የካልሄን በህሞ ሃውልት መቼ ቆመ?(ይህ መረጃ ተጣርቶ በመጽሀፉ ሊካተት ይችላል፡፡)  

 1. የቋንቋ ግልጽነት እና የይዘት የአመክንዮ ፍሰት /logical flow of issues/
 • 57 ጥቆማዎች ከመላሾች ቀርበዋል፡፡
 • በአብዛኛው በመጽሐፉ የሚታየው የቋንቋ አጠቃቀም ግልጽና እንግሊዝኛ ተናጋሪ ለሆኑ ቱሪስቶች ምቹ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም ቢታዩ በሚል ከተጠቀሱት አንዳንድ ነጥቦች (ለምሳሌ፣ቋንቋው የበለጠ ቀለል ባለ መልኩ መቅረብ ቢችል) ባሻገር በፈረንሳይና በሌሎችም የውጭ ቋንቋዎች እንዲሁም በአማርኛም ጭምር ሊዘጋጅ የሚገባው መሆኑም መገለጹ ትኩረት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡
  1. የአዲስ አበባን የልማት፣ የሰላምና የዲሞክራሲ ገጽታዎች በተመለከተ
 • 42 ጥቆማዎች ከመላሾች ቀርበዋል፡፡
 • በአብዛኛው መገንዘብ የተቻለው መጽሐፉ ጥሩ መረጃ የያዘ ቢሆንም አንዳንድ ግነቶችን በማውጣትና ማብራሪያዎችንም በመጨመር ሊታይ እንደሚገባው ነው፡፡ ለዚህም በመላሾች የተጠቆሙ የሚከተሉትን ነጥቦች በምሳሌነት ማየት ይቻላል፡፡ 

1ኛ/ አዲስ አበባ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ፈርሳ እየተገነባች ያለች ከተማ በመሆኑ ምክንያት ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሀይማኖታዊና ተፈጥሯዊ መስህቦቻችንን የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ልማቱን ማስቀጠልና እስካሁንም ላከናወናቸው የሰላምና ዴሞክራሲ ተግባራቶች ሊመሰገን ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን ከዚህ አሁን ካለንበት በበለጠ መሰራት ይጠበቅበታል፡፡ ብዙ ብዙ ያልተሰሩ ሥራዎች እንዳሉ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ አመላካች መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ (11) 

2ኛ/ ያልተሰሩ ስራዎችን እንደተሰሩ አድርጎ ማስቀመጥ ስራውን ያወርደዋል፡፡ ለምሳሌ የኢ/ያ ንግድ ባንክ ህንጻ፤ (28)

3ኛ/ በሃገር ውስጥ የነበረው አለመረጋጋት የመንግስትም ለዘርፉና ለወቅታዊ ችግሮቹ አፋጣኝ መፍትሄ አለመስጠቱ በመጽሃፉ አልተዳሰሰም፡፡ (29)

4ኛ/ የልማት የሰላምና ዲሞክራሲ ገፅታዎችን [በተመለከተ] ያለው ጉድለት የአዲስ አበባን ከተማ ብቻ መግለፅና በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙትን ያላካተተ መሆን፡፡ (43)

 1. የመፍትሄ ሃሳቦች (Recommendations)

የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የ2009 ዓ.ም የዓለም ቱሪዝም ቀን የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ ለአዲስ አበባ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ያለውን አወንታዊ ሚና ከማሳዳግ አንጻር በጥናቱ የተገኙ መረጃዎችን ተደራሽነት ለማስፋት እንዲሁም የጥናቱን ውጤቶች መነሻ በማድረግ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የ2009 ዓ.ም የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ በተሻለ መልኩ የሚዘጋጅባቸውን አማራጮች ለማመላከት እንዲረዳ የሚከተሉት የመፍትሄ ሃሰቦች (Recommendations) ልዩ ትኩረት ያሻቸዋል፡፡

 1. በቀጣይ ሊተገበሩ የሚገባቸው ተግባራት በቅደም ተከተል
 2. ለአዲስ አበባ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የ2009 ዓ.ም የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ /Guidebook/ ያለውን አወንታዊ ሚና ከማሳዳግ አንጻር በጥናቱ የተገኙ መረጃዎችን ውጤታማነት ለማጎልበትቢሮው መረጃ በመስጠት ለተባበሩ የጥናቱ አካላት እና በጥናቱ ላልተሳተፉ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የራሱን የኤፍ ኤም 96.3 የቱሪዝም የሬድዮ ክፍለ-ጊዜ ወይም መድረክ በመጠቀም ከላይ የተገለጹትን ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ከዝርዝር ማሳያዎቻቸው ጋር (አባሪ 2ን ይመልከቱ) ተደራሽ ማድረግ አለበት፡፡ ከዚህም ባሻገር በዚሁ የሬድዮ ክፍለጊዜ /በአማርኛ ተተርጉሞ/ በቋሚነት መጽሐፉን የማስተዋወቅ ሥራ ሊሰራና ለተጠቃሚዎች መጠኑ አነስ ብሎ፣ የፊደላቱ መጠን/ፎንቱ ከፍ ብሎ፣ ፎቶዎቹ በአዲስ መልክ ተዘጋጅተውና በተሻለ ዲዛየን እንዲሁም አዳዲስ የቱሪስት መስህቦች ተጨምረውበት በሰፊው ታትሞ ቢሮው ባለው አደረጃጀት ከማዕከል እስከ ወረዳ እንዲሁም የአዲስ አበባን ፎረሞች /አስተባባሪዎችን/፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በመጠቀምና በፒዲኤፍ ፎርማት በቢሮው ድረገጽ በነፃ ሊሰራጭ ይገባል፡፡ ከአገር ውጭም በውጭ ጉዳይና በቆንስላ ጽ/ቤቶች በኩል እንዲሁም በተለያዩ ቢሮው በሚወከልባቸው ጉባኤዎችና በዓላት ሁሉ /በቅርቡ በመካከለኛው ምስራቅና በአውሮፓ እንደተደረገው የቢሮው ተወካዮች ያደረጉት ጥረት ዓይነት/ መጽሐፉን በሰፊው በማሰራጨት በአገር ውስጥም /ለምሳሌ፣ በታላቁ ሩጫ፣ በሕዝብ በዓላት፣ በጉባኤዎች/ ሆነ በዓለም አቀፍ ቱሪዝም የቱሪስት ፍሰትን/ቁጥርን በአዲስ አበባም ሆነ በኢትዮጵያ ለማሳደግ መጽሐፉ የሚኖረውን አወንታዊ ሚና/ተጽዕኖ ማጉላት ይቻላል፡፡    
 3. የጥናቱን ውጤቶች መነሻ በማድረግ መጽሐፉ በተሻለ መልኩ የሚዘጋጅባቸውን አማራጮች በተመለከተ በዚህ ሰነድ በምዕራፍ ሁለት /አጭር የሰነዶች ዳሰሳ (Review of related literature)/  በቀረቡት ምርጥ ተሞክሮዎች መሰረት እና ከላይ የተገለጹትን ጠንካራና የደካማ ጎኖችን ከዝርዝር ማሳያዎቻቸው ጋር ታሳቢ ባደረገ አግባብ መጽሐፉ በተሻለ መልኩ ወደፊት እንዲዘጋጅ የሚሰራ ቡድን/ኮሚቴ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በፕሮሰስ ካውንስል ደረጃ ወሰኖ ማቋቋም እና ኮሚቴው ዕቅድ አውጥቶ እንዲሰራ በጥብቅ ክትትል፣ ድጋፍና ቁጥጥር አግባብ ማስቻል ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ፣ ከመጽሐፉ ዲዛየንና ፎቶዎች እንዲሁም የሕትመት አማራጮች /ገጾች ሳይነቀሉ ከመስራት/ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ውስጥ ወይም ከኢትዮጵያ ውጭ ተገቢ ሥራዎችን የተሻለ ዝና/ዕውቅና ባለው አታሚ ድርጅት /ለምሳሌ፣እንደ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ካሉ አታሚ ድርጅቶች ጋር በሕግ አግባብ በመስራት/ ኮሚቴው እንዲሰራ ማስቻል ይገባል፡፡
 4. የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መጽሐፉ በተሻለ መልኩ የሚዘጋጅባቸውን አማራጮች ከማስፋት አኳያ የከተማዋን የቱሪስት መስህቦችን/ ለምሳሌ፣ ዋሻዎችን፣ የስፖርታዊ ቱሪዝም አማራጮችን፣ የአዕዋፍ ማድነቅ ቱሪዝም/ ከዚህ ቀደም በቢሮው በተዘጋጀው የጥናት ቼክሊስት መሰረት በባለሙያዎቹና በውጭ ባለሙያዎች ማስጠናት አለበት፡፡ አዳዲስ ጥናቶችን በማካሄድም የከተማዋን ቱሪዝም የማስተዋወቅ አማራጮችን የማስፋትና አዳዲስ የቱሪስት መስህቦችን በማልማት በመጽሐፉ አካትቶ እንዲሁም በአማርኛና እንደፈረንሳይኛ፣ ቻይንኛና ጀርመንኛ ባሉ በተለያዩ ቋንቋዎች መጽሐፉ ተተርጉሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራት ባለው ሕትመት አሁን ከሚታየው (አባሪ 2ን ይመልከቱ) በተሻለ መንገድ መጽሐፉን በማዘጋጀት ለቱሪስቶች/ለጎብኚዎች ቢሮው ማስተዋወቅ እንደሚገባው ጥናቱ ያመላክታል፡፡     
 5. በጥናቱ ወቅት የታዩና ትምህርት ሊወሰድባቸው የሚገቡ ጉዳዮች
 • አንዳንድ ምላሾች እንዳመላከቱት ጥቂት መላሾች የጽሁፍ መጠይቁን በጥንቃቄ ያለመያዝ /የመጣል/ ችግር እንዲሁም ትክክለኛ (በቂ፣ ተአማኒና ዝርዝር) መረጃ /በተለያዩ ምክንያቶች/ በሚገባቸው ልክ መጽሐፉን አንብበው አለመስጠታቸው ከሚመለከታቸው የበላይ አካላት ምክር ሊሰጣቸው እንደሚገባ ያሳያል፡፡
 • በተለያዩ ከፕሮግራም አስቸጋሪነት ጋር በተያያዙ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው የጽሁፍ መጠይቁን በጥንቃቄ ይዘውና ሞልተው በወቅቱ ለጥናት ቡድኑ አባላት ገቢ ላደረጉ ሁሉ ምላሽ/መረጃ ሰጪዎች አርአያነት ያለው ሥራ አድናቆት ሊቸረው ይገባል፡፡   

ዋቢዎች (References)

አባቱቢ (የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ) (2008 ዓ.ም)፤ ሁለተኛው (2008-2012)      የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እስትራተጂክ ዕቅድ ያልታተመ ሰነድ፤ አዲስ አበባ፣አባቱቢ፡፡ 

 

Harris, Robert. (2001). Dictionary of Travel, Tourism and Hospitality Terms. Melbourne: Global Books & Sbscription services.

 

Hornby, AS. (1999). Oxford Advanced Learner’s Dictionary of Current English. Oxford: Oxford University Press.

 

Iain Christie, Eneida Fernandes, Hannah Messerli, and Louise Twining - Ward (n.d)      Overview-Tourism in Africa: Harnessing Tourism for Growth and Improved      Livelihoods. Washington, DC, 20433: The World Bank

 

Kothari C. R. (2004). Research Methodology - Methods and Techniques (Second Revised Edition). New Delhi: New Age International (P)Ltd.

 

Krejcie Robert V. and Morgan Daryle W. (1970). Determining Sample Size for Research Activities. Educational and Pyschological Meaurement. 30, 607 – 610.

 

Patton, M.Q.(1990). Qualitative evaluation and research methods. SAGE Publications. Newbury Park London New Delhi.

 

World Travel and Tourism Council (n.d) Travel and Tourism Economic Impact2016 Ethiopia. Retrieved on September 18/2016 from www.wttc.org.

 

 

[1]  የመረጃ ትንታኔው ከመረጃ ሰጭዎች/ግለሰቦች ብዛት ይልቅ በመረጃዎች ዓይነትና ብዛት ላይ ያተኮረበት ዋንኛው ምክንያት መላሾች በቁጥር አንድ ግለሰብ ወይም ከአንድ በላይ ግለሰብ ያላቸው ቡድኖች ሆነው፣ የዕውቀት ልዩነታቸውን ታሳቢ ባደረገ መንገድ፣ መረጃ እንዲሰጡ ጥናቱ ዕድል ስለሰጣቸው እና ጥናቱ ከግለሰቦች ብዛት /ቁጥር/ ጥናት ይልቅ ለሃሳቦች/ጥቆማዎች የአመክንዮ ትስስር /Logical relationship/ ዓይነትና ብዛት ጥናት የበለጠ ዋጋ የሚሰጥ ይዘት-ተኮር /Qualitative/ ጥናት ስለሆነ ነው፡፡ 

[2] በዚህና በሌሎችም ክፍሎች ውስጥ የመረጃ ይዘት ለውጥ እንዳይከሰት በሚል ከመላሾች የተገኘው የአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም መሰረታዊ ለውጥ አልተደረገበትም፡፡

[3]  በመረጃ ትንተና ክፍል በተገለጸው መሰረት ይህንንና ሌሎችንም ቁጥሮች/ኮዶች በመጠቀም ዝርዝር መረጃዎችን ማየት ይቻላል፡፡ 


Tourism Studies and research Tourism Studies and research