የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከቱሪዝም ዘርፍ የህዝብ ክንፍ ጋር ግንቦት 12 ቀን 2010 ዓ.ም የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከቱሪዝም ዘርፍ የህዝብ ክንፍ ጋር ለመተዋወቅ እና በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመለየትና አቅጣጫ ለማስቀመጥ ግንቦት 12 ቀን 2010ዓ.ም በጌትፋም ኢንተርናሽናል ሆቴል የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡

የምክክር መድረኩን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ክብርት ወ/ሮ ፎዚያ አሚን በንግግር የከፈቱ ሲሆን በፌዴራል ደረጃ ተደራጅተው ከሚንቀሳቀሱ የህዝብ ክንፍ ጋር በጋራ ተሳስሮ የተሻለ ስራ ለማከናወን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ የአሰራር እና የመመሪያ ክፍተቶች ላይ በመመካከር ችግሮችን የጋራ በማድረግና በመግባባት ለቀጣይ ስራ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ወደ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ተመድበን የመጣን አመራሮች ከቱሪዝም ባለድርሻ አካላት ጋር ተዋውቀን በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ በፌደራል ደረጃ ተደራጅተው ከሚንቀሳቀሱ ማህበራት ጋር በጋራ የዘርፉን ተጠቃሚነት እና ውጤታማነት እንዲሁም እያጋጠሙ ላሉ ችግሮችና ተግዳሮቶች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን አስመልክተው በሚኒስቴር መ/ቤቱ የቱሪስት አገልግሎት ብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው እንደገለጹት፡-

አስጎብኝ ድርጅቶችን በሚመለከት

 • አስጎብኝ ድርጅቶች የሚሰጡት አገልግሎቶች ከዓለም አቀፍ ስታንዳርድ አንፃር ያላቸዉ ተወዳዳሪነት ዝቅተኛ መሆን
 • ለአገር ዉስጥ ቱሪዝም ልማት ተገቢዉን ትኩረት አለመስጠት
 • ከልማዳዊ የገበያና ማስተዋወቅ ዘዴዎች አለመላቀቅ በተለይም የዲጂታል ማርኬቲንግ ዘዴዎችን በተሟላ መልክ አለመጠቀም
 • ጠንካራ የገበያና ፕሮሞሽን ስትራቴጅዎችን ነድፎ ተግባራዊ አለማድረግ
 • የአገራችንን ገፅታ ለመገንባትና የቱሪዝም ሀብቶቻችንን ለማስተዋወቅ በሚደረጉ የቱሪዝም ንግድ ትርኢቶች/ሁነቶችን ከታለመላቸዉ ዓላማዎች ዉጭ የመጠቀም አዝማሚያዎች መኖራቸዉ
 • ድርጅቶች በተገቢዉ የሰለጠነ የሰዉ ሀይል ከማደራጀትና ከመምራት አንፃር ክፍተቶች መታየታቸዉ በኩል የሚስተዋሉ እጥረቶች
 • በቱሪዝም ኢንዱስትሪ እሴት ሰንሰለት ዉስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶች ቀልጣፋ፣ ጥራታቸዉ የተጠበቀና ተወዳዳሪ አለመሆናቸዉ
 • አስጎብኚ ድርጅቶች የሚሰጡት አገልግሎቶች ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን የሚየስችል ስታንዳርድ (ደረጃ) አለመዘጋጀትና ተግባራዊ አለመደረጉ
 • በአስጎብኚነት ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶችና ባለሙያዎች ብቃት ማረጋገጫ ስርዓት ውሱንነት ያለበት መሆኑ
 • በሆቴሎችና መሰል ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶች ጥራት ዝቅተኛ መሆንና ጎብኝዎች ለሚከፍሉት ዋጋ ተመጣጣኝ አለመሆኑ
 • የቱሪስት መዳረሻዎች በሚፈለገዉ መጠን አለመልማታቸዉ
 • በአንዳንድ የፌዴራል አስጎብኝዎችና በበርካታ የአካባቢ አስጎብኝ ባለሙያዎች የእዉቀት፣ ክህሎትና ስነ-ምግባር ክፍተቶች መኖራቸዉ
 • ከኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ስርዓቶች ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮች ከተጠቀሱት ተግዳሮቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በዘርፉ ችግሮች ላይ ተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶች ያቀረቡ ሲሆን በዋነት የቀረቡት ችሮግች ሚ/ር መ/ቤቱ በትክክል አደራጅቶ ችግሮቹን ያቀረበ ስለሆነ ወደ ተግባር መቀየር እደሚገባቸው አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ክብርት ሚኒስትሯ መድረኩን ሲያጠቃልሉ የቱሪዝም ዘርፍ በርካታ ማነቆዎች ያሉበት ነው፡፡ አሁን ካለው ያዘገመ ጉዞ ወጥተን በፍጥነት ለውጥ ማምጣት የሚቻለው ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት መስራት ሲችል እና ያሉንን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች ወደ ገንዘብ በመቀየር ለአገራችን ተገቢውን አስተዋጽዖ ማበርከት ስንችል ነው፡፡ ይሄ የሚሆነው ዘርፉን በሰለጠነ የሠው ኃይል መምራት ሲቻል ነው፡፡ በቅርቡም የቱሪዝም ዘርፉን በዕውቀት የሚያግዙ ቲንክ ታንክ ቡድን በማቋቋም ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴም እንገባለን በማለት መድረኩ ተጠናቋል፡፡


News and Updates News and Updates