የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር በዛሬው እለት ለኮቪድ -19 መከላከል ስራ የሚውል የግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አበረከተ፡፡

የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ቢኒያም ብስራት በሰላም ሚኒስቴር በመገኘት የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ክብርት ወ/ሮ ቡዜና አልከድር በተገኙበት ስጦታውን አበርክተዋል፡፡
አቶ ቢኒያም ማህበሩን ወክለው ስጦታውን ባበረከቱበት ወቅት እንደተናሩት የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር አሁን ካበረከተው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ቫይረሱ በሀገራችን ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የማህበሩ አባላት ሆቴሎቻቸውን መንግስት በለይቶ ማቆያነት እንዲጠቀምባቸው መፍቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሆቴሎቹ ከ15 ሺህ በላይ ሰራኞቻቸውን ሳይበትኑ ደመወዛቸውን እየከፈሉ መቀጠላቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታዋ ክብርት ወ/ሮ ቡዜና አልከድር በበኩላቸው የዛሬው ድጋፍ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይደለም ያሉ ሲሆን ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚደረገው ርብርብ አጋር አካላትን በማስተባበር የሚያደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፅዋል፡፡
ስጦታውን የተረከበው የኮቪድ-19 መከላከል ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በበኩላቸው ተቋማቱ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከመንግስት ጎን በመቆም በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በስራቸው ያሉ ሰራተኞችንና በየአካባቢው ያሉ ድጋፍ ፈላጊ ወገኖችን በመታደግ ለሚያደርጉት የማይተካ ሚና ምስጋና አቅርበዋል፡፡

News and Updates News and Updates