የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ዙሪያ እያዝናና ግንዛቤ የሚያስጨብጥ የኪነ ጥበብ ዝግጅት በአዲስ አበባ አንድነት ፓርክ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

በጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ስር በተዋቀረውና በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ብሔራዊ የሚዲያ እና ኪነ ጥበባት ግብረ ሃይል ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ የኪነ ጥበብ ዝግጅት በቤት ውስጥ ለተቀመጠው ህዝብ እያዝናኑ የሚያስተምሩ ስራዎችን በቀጥታ በማስተላለፍ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት የታቀደ ነው፡፡
በዛሬው እለት በዝግጅቱ መክፈቻ ላይ በርካታ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ሚኒስትሮች፣ እውቅ የኪነ-ጥበብ ሙያተኞችና የመገናኛ ብዙሃን ታድመዋል፡፡ በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረጉት የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ካሳው ዝግጅቱን እውን ለማድረግ አስተዋፅኦ ያደረጉትን አካላት በሙሉ አመስግነዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚልና የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ የኪነ ጥበብ ሙያኞች እያደረጉ ላሉት ግንዛቤን የማስጨበጥ እንቅስቃሴ ያላቸውን አድናቆት የገለፁ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስቴር የፕሬስ ሲክሪታሪያት ሃላፊው አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው ኪነ ጥበብ ህዝብ ሲደናገጥ የምትደነግጥ አይደለችም፡፡ ይልቁንም የፈራን የምታረጋጋ እንደመሆኗ ለዚህ አላማ ማዋላችሁ የሚበረታታ ነውና ሁሉም አልፎ በዚሁ መድረክ ለመመሰጋገን ያብቃን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም በበኩላቸው ፖለቲካም ሆነ ሌላው ስራ የሚኖረው ሀገር እና ህዝብ ሲኖር ነውና ሙሉ ትኩረታችንን የቫይረሱን ስርጭት በመግታት ላይ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
ከታዋቂ የጥበብ ሰዎች መካከል አርቲስት ሙሉአለም ታደሰ፣ አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ፣ አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ፣ አርቲስት እመቤት ወ/ገብርኤል፣ አርቲስት ሃናን ታሪክ፣ አርቲስት እፅ ህይወት አበበና አርቲስት ቴድሮስ ሞሲሳ ቫይረሱን በመከላከል ዙሪያ የየራሳቸውን መልዕክቶች አስተላልፈዋል፡፡
በመቀጠል ልዩ ልዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎች በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭቶች ለህዝብ በመቅረብ ላይ ናቸው፡፡

News and Updates News and Updates