ስፖርት ለሰላም! በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡

ታህሳስ 03/2011 . በኢፌዴሪ የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴርና የሰላም ሚንስቴር አዘጋጅነት በተካሄደው የምክክር ስነ-ስርዐት ላይ ከሁሉም ክልሎች፣ ከስፖርት ፌደሬሽኖች፣ ማህበራት፣ ባለሙያዎች፣ ደጋፊዎችና ስፖርተኞች ተሳትፈዋል። በመድረኩ ላይ በዋናነት በተለያዩ ቦታዎች የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮች፣ የቡድን መሪዎችና አመራሮች ህግና መመሪያዎችን በአግባቡ ባለመተግበር በሚፈጥሯቸው ችግሮች የስፖርት ማህበረሰቡ እየተረበሸ መሆኑ ተነስቷል። በሀገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዘርና በሰፈር በመከፋፈል የሚታየው ሁከትና አፀያፊ ተግባር በመራቅ ስፖርትን ለአንድነት ለሰላምና የተጀመረውን ለውጥ ማጠናከር እንጠቀምበት የሚሉ ሀሳቦች ቀርበዋል። ሁለቱ ሚንስቴር /ቤቶች ይህን መድረክ በማዘጋጀታቸው በስፖርት ዘርፍ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት በጋራ የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል በማለት ቀጣይነት ያለው መድረክ እንዲመቻች ተሳታፊዎች አንስተዋል። የሰላም የፍቅር ዋንጫ በሚል ውድድር ቢደረግ የሚል ሀሳብም ቀርቧል። በጸጥታ ሀይሎች እንመታለን ከደጋፊነት የፀዳ ፖሊስ ያስፈልጋል። በጥሩ ስሜት ስንደግፍ ይመቱናል ይህ ደግሞ ወደ ብጥብጥ ይገፋፋናል ሲሉ ደጋፊዎች ገልፀዋል። 


ደጋፊወች ወንድምና እህቶች ነን አንጣላም ወደክልል ስንንቀሳቀስ ግን ተመተን እንመጣለን። ስለዚህ ፌደሬሽኖች ሊፈተሹ ይገባል፤ ብዙ የቤት ስራ አለበት ተብሏል። መንግስት የሚሯሯጠው ብዙ ችግሮች ከተፈጠረ በኋላ ስለሆነ አሁን ምን አቅዳችኋል የሚል ጥያቄ ቀርቧል። ስፖርት ለሰላም! ሰላምም ለስፖርት! የማይነጣጠሉ ተመጋጋቢዎች በመሆናቸው ሁላችንም ለሰላም ዘብ መቆም ያስፈልጋል። የተለያዩ መፍትሄዎችን በእጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ በሚል ሰርተን ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባናል በማለት ተሳታፊዎች ገልፀዋል። በክልሎች መካከል ያሉ ችግሮችን መፍታት ስለሚገባ መንግስት ዝም ማለት የለበትም ተብሏል። መንግስት በጨዋነት መሳተፍ ለማይችል ክለብ በጀት እስከማንሳት መድረስ ይገባዋል የሚሉ ጠንካራ ሃሳቦችም ተንሸራሽረዋል።


News and Updates News and Updates