በተደራጀ የወጣቶች ተሳትፎ ለባህል እና ቱሪዝም ልማት ወሳኝ ነው፤
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት “በተደራጀ የወጣቶች ተሳትፎ ለባህልና ቱሪዝም ልማት" በሚል መሪ ቃል ከደቡብ ብ/ብ/ሕ/ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመቀናጀት በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ለሚገኙ ከ9ኙ ብሔራዊ ክልሎች እና የሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የወጣት አደረጃጀቶች በአሉታዊ መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በዜጎች ላይ እያስከተሉት ያለው አሉታዊ ገጽታዎች እንዲሁም በማህበራዊ ድረ-ገጾች የሀገራቸውን ባህልና የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን የማስተዋወቅ ያላቸው ሚናና ተደራሽነት ዙሪያ ከግንቦት 25-28 /2010 ዓ.ም ድረስ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዊ በሐዋሳ ከተማ ኬር አውድ ሆቴል ተካሄደ፡፡
የስልጠናው መክፈቻ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችው መልዕክት ያስተላለፉት አቶ አቡቶ አኒቶ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የባህል ልማትና ጥናት ዋና ሥራ ሂደት ባለቤት እና አቶ ገዛኸኝ ሜጎ የደቡብ ክልል ወጣቶች ፌዴሬሽን ም/ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ መክፈቻውንም ለማድመቅ የክልሉ የባህል ቡድን ልዩ ልዩ ብሔረሰብ ባህላዊ ሙዚቃ፣ ከማራኪ ውዝዋዜና ዳንስ ጋር በማቅረብ ታዳሚውን በማስደሰት አድናቆትን አትርፈዋል፡፡
በመቀጠልም ወ/ሮ ወይንሸት ኃይለማርያም ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለጉባኤው ተሳታፊ የሆኑ ወጣቶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ የግንዛቤ ማስጨበጫውን ዋና ዓላማና አስፈላጊነትን በማስመልከት ወጣቶች የሀገራቸውን ባህላዊ፤ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ እሴቶችን በማልማት በመጠበቅና በማሳደግ ዘላቂ የቱሪዝም ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ኃይል መሆናቸውን በመጠቆም በመርሀግብሩ የራሳቸውን አቅም በመገንባት የዘርፉን የልማት የተሳታፊነት ሚናቸው በዘላቂነት ለማስቀጠል በተደራጀ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል እንደሆነ በመግለጽ የዕለቱን ክብር እንግዳ ወደ መድረክ ጋብዘዋል፡፡
በክብር እንግዳነት የተገኙት ክብርት ወ/ሮ ቡዜና አልከድር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሲሆኑ፣ በጉባኤው መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት “በአሁን ወቅት በአገራችን የምናያቸው አዳዲስ የመሰረተ-ልማት ዝርጋታዎች/ መንገድ፣ መብራት፣ ውሃ፣ የባቡር ሀዲድ፣ የአውሮፕላን ወዘተርፈ.. ለባህልና ቱሪዝም ዘርፉ ልማትና ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም ወጣቶች ከባለድርሻ አካላት ጋራ በመቀናጀት እነዚህን ልማቶች በባለቤትነት በእንክብካቤ ልንጠብቃቸው ይገባል፡፡ ያለንን የመከባበር፣ የመቻቻልና የአብሮነት ባህላችን እንዲሁም በስራ እድል ፈጠራ፣ በሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴ በመሳተፍና ለልማቱ የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይገባል” ብለዋል፡፡
ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም በተለይ የወጣቶች ዕምቅ ዕውቀትና ለቴክኖሎጂ ያላቸው ቀረቤታ በተግባርም በማሳየት በማህበራዊ ሚዲያዎች መስህቦቻችንን በማስተዋወቅ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው አለመሆኑን በመረዳት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ያለንን ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ ሀብቶችን በማልማትና በመንከባከብ፣ ለባህልና ቱሪዝም ዕድገት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ተልዕኮን ለማሳካት የሚኖራቸው ተሳትፎ ለጋራ ስራችን መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ነው ሲሉ በማስገንዘብ፤ መርሐግብሩ በይፋ መጀመሩን አብስረዋል፡፡
የጉዟቸው መነሻ ከአዲስ አበባ ያደረጉት ተሳታፊዎች የብሔራዊ ሙዚየም ጉብኝታቸው በመቀጠል የሀዋሳ ከተማ ውስጥ ለውስጥ ጉብኝትና የሀዋሳ ወልደ አማኑኤል ዱባለ ሀንካርሶ ሐውልት አካባቢ ጽዳት የተደረጉ ሲሆን፣ የሀዋሳ ታቦር ተራራን፣ የፍቅር ሐይቅን፣ የኢንዱስትሪያል ፓርክንና የወንዶ ገነት ፍልውሀዎችና ተፈጥሯዊ መስህቦቿ የተጎበኙ የውብቷ ኢትዮጵያ የደቡብ ክልል ቱሪስት መዳረሻዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫው ዋና ዓላማ ወጣቶች ለባህልና ቱሪዝም ልማት እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ ከፌዴራል ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ በክልሉ ቢሮና መንግስታዊ ድርጅት ካልሆነ የተውጣጡ ባለሙያዎች ተመቻችቶ በአራት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ተከፋፍሎ ትምህርታዊ ገለፃዎች የተሰጡ ሲሆን፣ በተቀመጠው መርሀግብር መሠረት በቀዳሚነት በደቡብ ክልል ያሉ ዕምቅ የቱሪዝም አቅምና ተግዳሮቶች፣ በወጣቶች የለውጥ ፓኬጅና የትግበራ ዋና ዋና ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች፣ በአሉታዊ መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና የማምከኛ ዘዴ እና በወጣቶች ራዕይ ቀረፃ በሚሉ ርዕሶች በፓዎርፖይት ገለፃዎች ከተደረጉ በኋላ በየርዕሰ ጉዳዮቹ በተሳታፊዎች የማጠናከሪያ ሀሳቦችን በማንሳት ጥልቅ ውይይቶች ተካሂዷል፡፡ በእያንዳንዱ ርዕሰ ጉዳዮችም ጎልተው የወጡ ግኝቶች፣ ለችግሮቹ መፍትሔ ጠቋሚ ምክረ-ሀሳቦች ላይ የጋራ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡
በመጨረሻም መድረኩን ያጠቃለሉት ክብርት ወ/ሮ ብዙነሽ መሰረት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሲሆኑ፣ በአወያይነት በመምራት መድረኩን ክፍት በማድረግ ተሳታፊዎች ማንሳት አለብን የሚሉት ጥያቄ፣ ሀሳብና አስተያየት እንዲያቀርቡ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ከዚህ አንጻር ተሳታፊዎች በቆይታቸው ሀዋሳን በደንብ ማወቅ መቻላቸውን፣ በቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች በጣም ጥሩ እንደነበሩ፤ በብሔራዊ የዱር እንስሳት ፓርኮች ያሉ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው፣ የባህል ምርቶችን ገበያ የሚያቀጭጩ ከውጭ አስመስለው አምርተው የሚያስገቡትንእንዴት መገታት እንዳለባቸው፣ በባህል ዘርፍ የተቀርፁ ስትራቴጂዎች ሼልፍ ላይ ከማስቀመጥ ፈጥነን ወደ ትግበራ የምንገባበት ሁኔታ ሊኖር ይገባል የሚሉ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን አንስተዋል፡፡
ከአወያዮችም በሠልጣኖች በተነሱ ጥያቄዎችና ሀሳቦች ላይ ማብራሪያዎች የተሰጡ ሲሆን፣ በተለይ የሀገራችን ባህል አልባሳት ዲዛይን በመውሰድ በውጭ አገር አስመስሎ በማምረት ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡትን በጥናት አስደግፎ ለመለየትና ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የምንሠራበት ሁኔታ እንፈጥራለን፡፡ ሁላችንም የቤት ሥራችን ይዘን የምንሄድበትና በ2011 ዕቅዳችን ጋር አስተሳስረን የምናይበት ዕቅድ እናዘጋጃለን፣ በአሉታዊ መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በመከላከል ረገድ ወጣቱ የራሱን ድርሻ መውሰድ አለበት፡፡ ወጣቶች እምቅ ኃይል ናቸውና የመጣውን ሁሉ ከመውሰድ ይልቅ ድርጊቱን በመኮነን፤ በመጸየፍና በመራቅ ራሱን በማየት ይኖርበታል፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለው የንባብ ባህልን ለማሳደግ በማንበብ፣ በማጥናት፣ አብሮ በመኖር፤ በሀገርን እንወቅ ክበባት፣ በማህበራት ተሳትፎ በማድረግ ሀገራቸውን በማወቅ ጠቃሚ የሆኑትን መውሰድና መጠቀም ይኖርበታል፡፡ ወጣቶች ሀገራቸውን ለማወቅ በቅድሚያ የጉብኝት ባህል እንዲኖራቸው የመደገፍ ሥራ ከመንግስትም ሆነ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የሚሠራበት አሠራር ሊኖር እንደሚገባ ተጠቁሞ ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ለስልጠናው ተሳታፊዎች የሀዋሳን ውበት ለመጠበቅ ስትሉ ጽዳት በማድረጋችሁ እንደ ክልሉ ተወላጅም ሆኜ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በራሴ ስም ላመስግናችሁ እወዳለሁ ሲሉ ካስገነዘቡ በኋላ የነበረው መድረክ ተጠናቋል፡፡
News and Updates
- The Geda Panel discussion held on the 4th anniversary of the Geda system recorded in the world heritage
- በአንኮበር ወረዳ በጎረቤላ ከተማ ተገንብቶ ለተመረቀው የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ሙዚየም የተለያዩ ጥንታዊ ቅርሶች ተበረከቱለት
- ለመዲናችን ልዩ ድምቀት!
- ኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ሰራተኞች ጋር ውይይት አደረጉ፡፡
- የሩሲያ ፌደሬሽን ለኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ እርስቱ ይርዳው የዲፕሎማና የሜዳልያ ሽልማት ሰጠች፡፡
- ኢትዮጵያ እና የሩሲያ ፌደሬሽን በባህል፣ በቱሪዝም እና ስፖርት ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ውይይት አካሄዱ፡፡
- የኢፌዴሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዶክተር ሂሩት ካሣው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ጋር ውይይት አደረጉ፡፡
- ስፖርት ለሰላም! በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡
- ዶክተር ሂሩት ካሳው በኢትዮጵያ የኳታር አምባሳደር ሀማድ አልዶሳሪን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
- የአዲስዓለም አድባራት ወገዳማት ደብረጽዮን ማርያም ሙዚየም በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ፡፡