በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ታሪክ ላይ በተሠሩ ጥናቶች ዙሪያ አውደ ጥናት ተካሄደ፣

ኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ታሪክ  ላይ በተሠሩ ጥናቶች ዙሪያ አውደ ጥናት ተካሄደ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር  በኢትዮጵያ የፊልም ዕድገት ላይ በተሠሩ ጥናቶች "ፊልማችን ለባህል ኢንዱስትሪ  ዕድገታችን!" በሚል መሪ ቃል ለፊልም ባለሙያዎች፣ ለዘርፉ በጎ ተፅዕኖ ፈጣሪ የድምፅ፣ የምስል፣ የህትመትና የማህበራዊ ሚዲያ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ተቋማት እንዲሁም የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ጋር ለማወያየት ህዳር 14/2010ዓ.ም. በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ የተዘጋጀው አውደ ጥናት ተካሄደ፡፡

በአውደ ጥናቱ በ5 ርዕሰ ጉዳዮች ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን፣ እነዚህም የኢትዮጵያ ፊልሞች ተግዳሮቶችና ዕድሎች(በዶ/ር ወንድሙ ለገሠ)፣ የአማርኛ ፊልሞች መስተዎት ወይስ መጋረጃ (በአቶ ምስጋናው ዓለሙ)፣ እኛ ወዲህ ፊልሞቻችን ወዲያ(በአቶ ስመኘው ሽፋራው)፣ የኢትዮጵያ ፊልሞች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችና የመፍትሔ ሀሳቦች(በአቶ ሄኖክ አየለ)፣ የፊልም ሙዚቃ ምንነትና ታሪካዊ መሠረት፣ በኢትዮጵያ ፊልሞች ውስጥ ያለው ስዕለ-ሂሊናና ትግበራ ምጥን ምልከታ( በአቶ ሠርፀ ፍሬሰንበት) የጥናቶቻቸውን መነሻ ሀሳብ የተደረሱባቸውን ግኝቶች በተሰጣቸው ጊዜ በቅደም ተከተል ለተሳተፊዎች ገለፃ አድርገዋል፡፡

 

በእያንዳንዱ ርዕስ  ጉዳይ ላይ አንዳንድ ተሳታፊዎች  ያላቸውን አስተያየት ሰጥዋል፡፡  የዚህ ዓይነት  መድረኮች  በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መዘጋጀቱና  እንድንሳተፍ መደረጉ በጣም ያስደሰተን ነው፡፡ በተለይ የፊልም ፖሊሲያችን መጽደቁ ለፊልሙ ኢንዱስትሪ ትልቅ አቅም ነውና ሥራዎቻችንን ይበልጥ  እያጠናከርን የምንሄድበት ዕውቀት ያገኘንበት ነው በማለት በአድናቆት ገልጸዋል፡፡  የኢትዮጵያ ፊልም  የደረሰበት ደረጃ በጥራትም ሆነ  በመጠን ሲታይ በቂ ነው ባይባልም ጅምሮቹ መልካም መሆናቸውንና በተደራጀ መልኩ በመንቀሳቀስና ያሉትን አቅሞች በመጠቀም ወደ ላቀ ደረጃ ለመድረስ አሁንም ቢሆን የመንግስት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ጠይቀዋል፡፡

በመጨረሻም መድረኩን ያጠቃለሉት አቶ ደስታ ካሳ የባህል ኢንዱስትሪ ልማትና ትብብር ዳይሬክቶሬት  ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ በዕለቱ ያስተላለፉት መልዕክት "የፊልም ኢንዱስትሪውን በተሻለ መንገድ ለማልማት ለተያያዝነዉ የልማት አቅጣጫ ከቀረጥ ነፃ ከውጭ የሚገቡ የፊልም መሣሪያዎች በሚመለከት ንግድ ኮድ የሚገባበት ሁኔታ እያመቻቸን ሲሆን፣ የባህል ኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማነት የዕውቀት፣ የክህሎትና የአመለካከት ለውጥ ሊኖር ይገባል፡፡ የሌሎች አገሮችን ልምድ ስናይ ለምሳሌ የናይጀሪያን የፊልም ኢንዱስትሪ በቀን አዳዲስ ፊልሞችን እስከ 50  ለተመልካች ያቀርባል፡፡ የእኛን አገር ስናይ ደግሞ የብዛሃ ባህል ሀገር ሆነን ፊልሞቻችን በጥራትም ሆነ በብዛት እየወጡ አይደሉም፡፡ ይህ የሚሆንበት ዘርፉ የባለሙያ እጥረት ያለበት መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም በአሁኑ ወቅት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ለፊልም ኢንዱስትሪው የሚያግዝ ትምህርት ስርዓተ ትምህርት ተቀርፆ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የፊልም ትምህር እንዲጀመር ተደርጓል በማለት ተሳታፊዎችን በማስገንዘብ የእለቱ መድረክ  ተዘግቷል፡  

 


News and Updates News and Updates