በመጀመሪያው ሩብ ዓመት አገራችንን የጎበኙ የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር መጨመሩ ታወቀ፤

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት አገራችንን የጎበኙ የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር መጨመሩ ታወቀ፤

ህዳር 08 /2010 ዓ.ም ሕዝቦች እርስ በርሳቸው እንዲተዋወቁ፣ እንዲቀራረቡና እንዲከባበሩ፣ በአገሮች መካከል የጋራ ትብብር እንዲፈጠር በተለይም  ዓለም አቀፋዊ መግባባት እንዲኖር አንዱ የሌላውን ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስ እንዲሁም የኔ የሚሏቸውን ትውፊቶች እንዲያውቁ ከማድረግ ረገድ የባህልና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡

በተለይእንደኢትዮጵያ የራሳቸው ባህል፣ ወግ፣ ሥርዓት፣ እምነት፣ ማንነት፣ ቋንቋና ታሪክ፣  ሌሎችም መገለጫዎች ያላቸው አገራት ያላቸውን እምቅ ሀብት ከዘርፉ ተዋንያን ጋር ተቀናጅቶ በመስራትና በመምራት ለህብረተሰብ ተጠቃሚነት እንዲሁም ለምጣኔ ሀብት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ለማጉላት ብዙ መስራት ይጠይቃል፡፡

የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በዘርፉ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ከዘርፉ ባለድረሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በርካታ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል፡፡ በ2017 ከመጀመሪያዎቹ 5 በአፍሪካ አገራት አንዷ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻዎች ለማድረግ ራዕይ ሰንቆ መንቀሳቀስ ከጀመረ ወዲህ በርካታ አበረታች የሆኑ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

ይሁንና ስለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ሲነሳ ከምንም በላይ ከሰላም ጋር የተያያዘ ነውና ባለፉት ሁለት ዓመታት በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው አለመግባባትና ግጭቶች በቱሪዝም ፍሰቱ ላይ በተለይ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚመጡ ጎብኝዎች ላይ የፈጠረው ተፅእኖ በጎብኝዎች አጠቃላይ ቁጥር ላይ ተፅእኖ አሳድሮ ነበር፡፡

መንግስትና ህብረተሰቡ በሰሩት የተቀናጀ ስራ ችግሩ በመቀረፍ ላይ በመሆኑ እንቅስቃሴው ወደ ነበረበት መመለስ ችሏል፡፡ በዚህም በዘንድሮ በጀት ዓመት የመጀመሪያ ምዕራፍ ከውጭ ወደ ውስጥ የገቡ ቱሪስቶች ቁጥር 256,154 ሆኗል፡፡ ይህ አሃዝ ካለፈው 2009 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር ለውጡን በግልፅ የሚያመላክት ነው፡፡ ለንፅፅር ያህል  በ2009 የመጀመሪያው 3 ወራት ውስጥ 233,032,ጎብኝዎች ወደ ሀገራችን  የገቡ ሲሆን በዚህም ከጎብኝዎች የተገኘ የገቢ መጠንም  872,471,808 የአሜሪካን ዶላር  ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም ተመሳሳይ ጊዜ አገራችን ውስጥ የገቡ ቱሪስቶች ቁጥር 235,011 ነበር 879881184 ዶላር ገቢም ተገኝቷል፡፡ በያዝነው 2010 የመጀመሪያው 3 ወራት ውስጥ ከ256,154 ጎብኝዎች የተገኘ የገቢ መጠንም  959,040,576የአሜሪካን ዶላር  ደርሷል ፡፡ ይህ አሃዝ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር በጎብኝዎች ቁጥር ላይ የታየው ልዩነት የ23122 ቱሪስት ($86,568,768) +9.92 % እንዲሁም ከ2008 ዓ.ም ጋር ሲነጻፀር ደግሞ የ21143 ቱሪስት ($79,159,392) የ8.99% ብልጫ ያለው መሆኑን ደግሞ ያሳያል፡፡

ይህን የቱሪስት ቁጥር ከስራ እድል ፈጠራ ጋር ብናስተሳስረው በአለም ተቀባይነት ባለው ጥናት መሰረት አንድ ቱሪስት በአማካኝ ለ9 ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል ይህ ማለት በዚህ ሩብ አመት ለ2,305,386 ሰዎች የስራ እድል ፈጥሯል ማለት ነው፡፡ እነዚህ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች ከጉልበት ሰራተኞች እስከ ባለሃብቱ ከተራ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እስከ አየር መንገድ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ የቱሪዝም የእዝ ሰንሰለት ረዥምና ድንበር ተሻጋሪ ነው፡፡   

ይህ አሁን የተመዘገበው ለውጥ በዘላቂነት ለማስቀጠልና አገራችን ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስገኘት በዘርፉ የተሰማሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸውን ማላቅ በተለይ የቱሪዝም ዘርፍ መሰረቱ ሰላም ነውና የአገራችን ህዝብ የሰላም ባለቤት በመሆን ጉልህ ድርሻውን በመወጣት ለምንወዳት አገራችን መስራት እንደሚጠበቅብን መልዕክታችንን እናስተላልፋለን::

 


News and Updates News and Updates