የከፋ የባዮስፌር አለም አቀፍ ጥብቅ አካባቢ የሀገር በቀል እዉቀትና የኢኮ ቱሪዝም ልማት ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት

 

 

 

 

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሴክተር ልማት፣ጥናትና

 

ምርምር ዳይሬክቶሬት

 

 

 

 

የከፋ የባዮስፌር አለም አቀፍ ጥብቅ አካባቢ የሀገር በቀል እዉቀትና

የኢኮ ቱሪዝም ልማት ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት

 

 

 

 

                                   ጥር 30 ቀን 2009/ዓ.ም

Sprit of forest                          

 

                           ማውጫ

   ርዕስ                                                                ገፅ

1.መግቢያ----------------------------------------------------------------------------------------------1

2.የጥናቱ መነሻሀሳብ---------------------------------------------------------------------------------1

2.የጥናቱ አስፈላጊነት--------------------------------------------------------------------------------2

3.የጥናቱ ዋና አላማ----------------------------------------------------------------------------------2

4.የጥናቱ ዘዴ------------------------------------------------------------------------------------------2

5.የጥናቱ ማዕቀፍ(ወሰን)------------------------------------------------------------------------------2

6.የከፋ ዞን ጥቅል ገጽታ እና የከፊቾ ብሄረሰብ ታሪካዊ አመታጥ------------------------------3

7.የከፊቾ ብሄረሰብ ታሪካዊ አመጣጥ----------------------------------------------------------------3

7.የከፋ ዞን ስነ ምህዳር--------------------------------------------------------------------------------4

8.የከፋ ዞን የደን ሽፋን እና የብዝሃ ህይወት ጥብቅ ደን ገጽታ----------------------------------6

9.የከፋ ዞን የደን ሽፋን--------------------------------------------------------------------------------6

9.የከፋየብዝሃ ህይወት ጥብቅ ቦታወይም ባዮሰፌር ገጽታ----------------------------------------7

10.የመረጃ ትንተና እና የጥናቱ ግኝቶች------------------------------------------------------------8

11.ለባዮስፌር ጥብቅ ቦታ ዘላቂነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሀገር በቀል እውቀቶች------------8

12.የከፊቾ ብሄረሰብ ጉዶ ዲጆ አምልኮአዊ ስርአት------------------------------------------------9

13. .የከፋ ባህላዊ አስተዳደርና መዋቅር------------------------------------------------------------11

14.የኮቦ የከፊቾ ብሄረሰብ የደን እንክብካቤ እና አጠባበቅ ስርአት-------------------------------14

15.ናሎ የከፋ ባህላዊ የፍትህ ስርአት---------------------------------------------------------------15

16.የከፊቾ ብሄረሰብ ማህበራዊ መዋቅርና አደረጃጀት---------------------------------------------16

17.የከፊቾ ብሄረሰብ ትውፊታዊ ትውን ጥበባት ለባዮስፌርጥብቅ ስፍራ ቀጣይነት ያለው አስተዋጽኦ-------------------------------------------------------------------------------------------------17

18 ክፍል ሁለት-የከፋ ባዮስፌር ጥብቅ አካባቢ የኢኮቱሪዝም ልማት ጥናት--------------------27

19 የከፋ ብዝሃ ህይወት ዓለም አቀፍ ጥብቅ ቦታና የኢኮቱሪዝም አቅም------------------------27

21 የከፋ አለም አቀፍ የባዮስፌር ጥብቅ ቦታ የቱሪዝም ሁኔታ መሠረተ ልማት--------------28

22.ሆቴልና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማት-------------------------------------------------------28

23.የቱሪዝም እንቅስቃሴውን የሚያግዙ ማህበራት-------------------------------------------------28

24.የከፋ ዓለም አቀፍ የባዮስፌር ጥብቅ ስፍራ የጉብኝት መስመሮች----------------------------29

24.በዚህ የዳሰሳ ጥናት በተመራማሪዎች የተጎበኙ መዳረሻዎች-----------------------------------32

25.ብሄራዊ የቡና ሙዚየም------------------------------------------------------------------------------32

26.ክፍት ሙዚየም ቦታ---------------------------- ----------------------------------------------------33

27.የቀርከሃ ጫካ------------------------------------------------------------------------------------------35

28.የአለም ጉኖ ውሃ አዘል ቦታ/አዕዋፋትን መመልከቻ ቦታ---------------------------------------35

29.ታትማራ የቡናና ማር አምራቾች ማህበር--------------------------------------------------------35

30.መሰረተ ልማትና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት---------------------------------------------------- 35

31.የማህበረሰብ ተጠቃሚነት----------------------------------------------------------------------------36

32.ማጠቃለያ----------------------------------------------------------------------------------------------36

33.የሚታዩ ተግዳሮቶች----------------------------------------------------------------------------------37

33.ዋቢ መጻህፍት----------------------------------------------------------------------------------------

34. Appedex-------------------------------------------------------------------------------------------

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

1.መግቢያ

የሴክተር ልማት ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት በ2009ዓ.ም ከታቀዱ የቅንጅት ጥናትና ምርምር ስራዎች ውስጥ ከሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት የሚሰራዉ የባዮስፌር ጥብቅ ቦታዎች የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ጥናቶች ናቸው፡፡ይህንኑ መነሻ በማድረግ በከፋ ባዮስፌር ጥብቅ አካባቢ ላይ ከጥር 7 እስከ 24 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ዳሰሳ ጥናት ተከሂዷል፡፡የሴክተር ልማት ጥናትና ምርምር የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ የጥናት ቡድን በከፋ ዞን ባካሄደዉ ዳሰሳዊ ጥናት ለባዮስፌር ጥብቅ ቦታዎች ዘላቂነት የሀገር በቀል እውቀት ያለዉን ድርሻ እንዲሁም የአካባቢዉ የኢኮ ቱሪዝም ልማት አቅጣጫዎችን፣ምቹ ሁኔትዎችንና ተግዳሮቶችን በተመለከተ አጥጋቢ መረጃዎችን አደራጅቶ ተመልሷል፡፡

የጥናት ቡድኑ በተዘዋወረባቸው ወረዳዎች፣የቱሪዝም መዳረሻዎችና የቦንጋ ከተማ አስተዳደር አካባቢ የከፊቾ ብሄረሰብ ባህላዊ ዕሴቶችና ስርዓቶችን፣የተፈጥሮ መስህቦችንና ሃብቶችን የባህልና ቱሪዝም ተቋማትንና የቡና እና የደን እርሻዎችን፣ማሳ፣ገበሬዎችንና ከባዮስፌሩ ጋር የተያያዙ ፐሮጀክቶችን ጎብኝቷል፣ቅኝትም አድርጓል፡፡

2 የጥናቱ መነሻ ሀሳብ

ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሀገር ከመሆኗም ባሻገር በርካታ ተፈጥሮአዊ፣ታሪካዊ ቅርሶችና ውብ ደኖች የተለያዩ ብዝሀ ህይወት፣ውብ መልካ ምድር ያላት ሀገር ናት፡፡በሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚንስቴር አስተባባሪነት ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያለው የሰውና የባዮስፌር ብሄራዊ ፕሮግራም ሀገራችን በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አቅድ ውስጥ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሰጠችውን ትኩረት የሚደገፍና ኢትዮጵያ ያጸደቀችውን አለም አቀፍ የዘላቂ ልማት ግቦች ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል ነው፡፡

የሰውና ባዮስፌር ፕሮግራም በኢትዮጵያ በተመዘገቡ አራት ጥብቅ የተፈጥሮ ሃብት ቦታዎች ላይ ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ እና በዓመት ከ6 መቶ ሺ ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ በላይ ከአየር ንብረቱ ለማስወጣት የሚችል ትልቅ ስልት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ይህንን ፕሮግራምና አካባቢውን በዘላቂነት ለመጠበቅና ለማልማት የማህበረሰቡ ባህላዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡በካፋ ባዮስፌር ጥብቅ አከባቢ ያለው ማህበረሰብ ተፈጥሮአዊ ደኖችን ለመጠበቅ ያዳበረውን ሀገር በቀል ዕውቀት አጥንቶና መዝግቦ መያዝ አካባቢውን ለኢኮ-ቱሪዝም በማዋል ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ትኩረት የሚሰጠው ጉደይ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የሴክተር ልማት ጥናትና ምርምር ቡድን ይህን ዳሰሳዊ ጥናት በከፋ ባዮስፌር ጥብቅ አካባቢ የሚኖረዉን የከፊቾ ብሄረሰብ ባህላዊ እውቀት በመተንተን ለአካባቢው ዘላቂ ልማት ያለውን አስተዋጽኦ ማሳየትና ማብራራት እንዲሁም በኢኮ-ቱሪዝም አካባቢውን ማልማት የሚቻልበት አቅጣጫ ገምግሟል፡፡  

3.የጥናቱ አስፈላጊነት

ይህ ጥናት ለባዮስፌር ጥብቅ ቦታዎች ዘላቂ ልማት አስፈላጊ ከመሆኑም ባሻገር በጥብቅ ቦታዎቹ አካባቢ የሚኖሩ የከፊቾ ብሄረሰብ ባህላዊ እውቀት ጠብቆ ለማቆየት እንዲሁም አካባቢው በዘላቂ የኢኮ ቱሪዝም ልማት እና አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ስልት ለመንደፍ ይረዳል፡፡

4.የጥናቱ ዋና ዓላማ

የሀገር በቀል እውቀት ለባዮስፌር ጥብቅ ቦታዎች ዘላቂ ልማት ያለውን አስተዋጽኦ እና የባዮስፌር ጥብቅ ቦታውን መሰረት አድርጎ የኢኮ ቱሪዝም ልማት አቅም በመገምገም ህብረተሰቡን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚኖረውን ፋይዳ ለመገንዘብ፣ለማብራራትና ለመተንተን ነው፡፡

5. የጥናቱ ዘዴ

ጥናቱ የከፍቾ ብሄረሰብ ባህላዊ እውቀትና ትውፊት በሚመለከት ስነ-ፅሁፋዊ ቅኝት ማካሄድ፤በመስክ የብሄረሰቡን አኗኗር፣ተፈጥሮ ጥበቃና ባህል ምልከታ ማድረግ፣የብሄረሰቡን ታሪክ አዋቂዎችና አዛዉንቶችን ቃለመጠይቅ ማካሄድ፣የምስልና የድምጽ መረጃ መውሰድ መረጃዎችን የማደራጀትና የመተንተን ስልት ጥናቱ ተከትሏል፡፡

6.የጥናቱ ማዕቀፍ (ወሰን)

የሀገር በቀል እዉቀት ለባዮስፌር ጥብቅ ቦታዎች ዘላቂ ልማት ያለውን አስተዋጽኦ እና የአካባቢውን ጥብቅ ቦታ መሰረት አድርጎ የኢኮ ቱሪዝም አቅም በመገምገም ለመተንተን ሆኖ ጥናቱ በዩኔስኮ በተመዘገበው የካፋ ጥብቅ አካባቢና ብሄረሰቦቹ ያተኩራል፡፡

 

 

 

1. የከፋ ዞን ጥቅል ገጽታ እና የከፊቾ ብሄረሰብ ታሪካዊ አመጣጥ

1.1 የከፍቾ ብሄረሰብ ታሪካዊ አመጣጥ

ከፋ የሚለው ስያሜ በደቡብ ኢትዮጵያ ከነበሩት የቀድሞ የቦንጋ ግዛት ውስጥ የሚካተቱ ሰፊ ህዝቦች ናቸው፡፡የጎንጋ ህዝቦች የሚባሉት የእናሪያ፣የቦሾ ወይም ጋሮ፣ከፋ፣ሸካ፣ሽናሻ ወይም ቦሮ-ሽናሻ እና አኒፊሎ ወይም ቡሽሽ ናቸው፡፡ የከፋ ህዝቦች አመጣጥ ከግብፅ  ነው የሚሉ ያሉ ሲሆን ሌሎች የጎንጋ ማህበረሰብ ቀደምት ግዛቶች አመጣጥ ትግረ እንዲሁም ከእስራኤልና የመን እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በሁለተኛው ሃሳብ የሚስማሙ ምሁራን እስራኤሎች በግብጹ ንጉስ ፈርኦን ቅኝ አገዛዝ ዘመን በነበረዉ ርሃብና ድርቅ ተሰደው የአባይን ወንዝ ተከትለው ለእርሻ ተስማሚ ወደ ሆነ ለም መሬት እንደተጓዙ ይህም ጉዞ ካፋ እንደተባለ ያብራራሉ፡፡ከፋ ማለት ከሞት ወደ ሕይወት ጉዞ እንደ ማለት ነው፡፡

የቀድሞና ያሁኑ የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚገልጹት የከፋ ግዛተ መንግስት የተቋቋመው በመካከለኛው ክፍለ ዘመን 500-1500 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ የከፋ ግዛት የራሱ የሆነ የአስተዳደር ስርአት ባለቤት ሆኖ በሶስት ስርወ መንግስታት ማለትም ማንጆ፤ማቱ እና ሚንጁ በሚባሉ የሚመራ እንደነበር ተመራማሪዎች ይገልጻሉ፡፡እነዚህም ከ13ኛ እስከ 19ኛመቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ጠንካራ እና እራሳቸውን የቻሉ ስርወ መንግስታት ነበሩ፡፡በዚህ መካከል ከ20 በላይ ነገስታት በከፋ ግዛት ተፈራርቀዋል፡፡የመጨረሻው የከፋ ስርወ መንግስት ሚንጆ ሲሆን ይህም ማዕከላዊ መንግስትና ታቶ በተባሉ መንፈሳዊ ንጉስ የሚመራ አምባገነን ስርአት እንደነበር ይነገራል፡፡ በ እ.ኤ.አ 1897 የመጨረሻው የከፋ ግዛት ንጉስ የነበሩት ታቶ ጋኪ ሽራቾ ተይዘው ስርአቱ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ከከፋ ግዛት ጋር አዋሳኛ የነበሩት አርባ ነገስታት ለከፋ ንጉስ ግብር ይገብሩ እንደነበር ይነገራል፡፡በ19ኛ ክፍለ ዘመን ከፋ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ከተቀላቀለች በኋላ እስከ 1991 ድረስ የአውራጃ ስያሜ ተሰጥቶ ጅማ ዋና ከተማ ነበረች፡፡

በአሁኑ ወቅት ከፋ ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መንግስት አንዱ ዞን ሆኖ በአስር ወረዳዎች የተከፋፈለ ነው፡፡በከፋ የሚኖሩ ሶስት ነባር ብሄረሰቦች ያሉ ሲሆን እነሱም ከፊቾ 80% ሌሎች ናኦ እና ጫራ ናቸው፡፡የከፊቾ ቋንቋ ከፊኖ በመባል ይታወቃል፡፡

 

 

1.2 የከፋ ዞን ስነ-ምህዳር

የከፋ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በ60 24እስከ 7070 ሰሜን እና 3569 እስከ 3678 ምስራቅ ላይ ይገኛል፡፡የከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ከአዲስ አበባ 460 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ከፋ ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መንግስት 13 ዞኖችና ስምንት ልዩ ወረዳዎች አንዱ ነው፡፡ የዞኑ የመሬት ስፋት ጠቅላላ 10,602.7 ኪ.ሜ ስኩዌር ሲሆን ከክልሉ 7.06% ስፋት ይሸፍናል፡፡ዞኑ በሰሜን ከኦሮሚያ እና ከሰሜን ምዕራበ በኮንታ ልዩ ወረዳ በምስራቅ በደቡብ ከደቡበ ኦሞ ጋር በቤንችማጅ ዞን በምዕራብ ከደቡብ ምዕራብ ከሸካ ዞን ጋር ይዋሰናል፡፡

የከፋ ዞን በአስር ወረዳዎች የተከፋፈለ ሲሆን እነዚህም አዲዮ፣ቢታ፣ጨና፣ጨታ፣ዴቻ፣ገዋታ፣ጌሻ፣ጊምቦ፣ሳይለም፣ ጠሎ እና ቦንጋ ከተማ አስተዳደር ናቸው፡፡

                                              Figure 1 የከፋ ዞን ካርታ

የከፋ ዞን የአረቢካ ቡና ዋና መገኛ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ቡና ምንጩና መገኛዉ በዴቻ ወረዳ ማኪራ በተባለ ቦታ እንደተገኘ ይነገራል፡፡በከፋ ዞን የሚገኘዉ የጥቅጥቅ ደን በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ጥቂት የቡና ደኖች ዉስጥ አንዱ ነው፡፡ ካፋ የኢትዮጵያ የቡና ዝርያ ምንጭ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ከፋ ሶስት የአየር ንብረት ዞኖች የሉት ሲሆን እነሱም ደጋ 2500-3000 ሜትር በላይ ወይና ደጋ 1500-2500 ሜትር እና ቆላ 500-1500 ሜትር ከፍታ ያለው ነው፡፡የከፋ ዞን ከ500 እስከ 3500ሜትር ከፍታ መካከል ይገኛል፡፡

የአካባቢው የሙቀት መጠን 17-20 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚደርስ ሲሆን የካቲት፣መጋቢት እና ሚያዚያ ሞቃታማ ወራት ናቸው፡፡የከፋ ተራራማ መሬቶች፣የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዝናብ ሰጭ አካባቢዎች ናቸው፡፡ይህም በመሆኑ ከዓመት ዓመት አረንጓዴ ደኖች እና ዛፎች የተከበበች ዞን እንድትሆን አድርጓታል፡፡የቦንጋና አካባቢው የዝናብ መጠን 1300-2000ሚ.ሜ ይደርሳል፡፡ ከፍተኛው የዝናብ መጠን በአካባቢው በግንቦትና መስከረም ቢሆንም በሁሉም ወራት መጠነኛ ዝናብ ይኖራሉ፡፡

በ1999 በስታቲስቲክ ባለስልጣን በወጣው ሪፖርት የከፋ ህዝብ ብዛት 880,251 ሲሆን ከዚህ ውስጥ 812,387 ወይም 92.3 ፐርሰንት በገጠር የሚኖሩ ሲሆን 67,864 ወይም 7.3 ፐርሰንት በከተማ የሚኖሩ ናቸው፡፡

ከዞኑ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት መረጃ እንደተገኘው በዞኑ ከ20 በላይ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሚኖሩ ሲሆን ከፊቾ ብሄረሰብ 71.8% ሸካ ብሄረሰብ 6.36% ቤንች 5.23% እና አማራ 6.86% ይገኛሉ፡፡ የቀረው ድርሻ ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች  የጫራ፣የዳውሮ፣ናኦ እና መአኒት እና ሌሎችም ብሄረሰቦች ናቸው፡፡በከፋ ዞን ካሉት ማህበረሰቦች ውስጥ ሚንጆ ማህበረሰብ ዝቅተኛ ማህበራዊ ደረጃ የተሰጣቸውና በልማድ የተገለሉ ናቸው፡፡ ሚንጆ ማህበረሰብ በተፈጥሮ ደን አካባቢ የሚኖሩና በአደን፣በከሰል፣እንጨትና ሌሎች የባህላዊ ዕደጥበብ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡የማንጆ ማህበረሰብ መገለል እንደ ማህበረሰቡ ልማዳዊ ዕይታ በማንጆ የአመጋገብ ስርአታቸው የሞቱና የዱር እንስሳትን የሚመገቡ በመሆኑ እንደሆነ ተገልጾል፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን የመገለሉ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱ እና የአመጋገብ ስርአታቸውም እየተሻሻለ መምጣቱ ይናገራሉ፡፡

የከፋ ዞን ማህበረሰብ በአብዛኛው በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን በደን አካባቢ አነስተኛ የእርሻ ማሳ ይጠቀማሉ::

በ1999 የስታትስቲክሰ ባለ ስልጣን መረጃ 92.29 ፐርሰንት የህዝቡ ቁጥር በገጠር የመኖር እና በእርሻ ስራ ላይ የሚተዳደር ነው፡፡በከፋ ዞን ካለው የመሬት አቀማመጥ 56 ፐርሰንት ለእርሻ ምቹ የሆነ ፣29 ፐርሰንት ደን እና ጫካ እንዲሁም 14 ፐርሰንት ህዝብ የሰፈረበት እና ለተለያዮ አገልግሎቶች የሚውል ነው፡፡

በከፋ ዞን ከሚመረቱት ዋና ዋና ምርቶች ዉስጥ በቆሎ፣ማሽላ፣እንሰት፣ገብስ፣እና ስንዴ ይገኝበታል፡፡ በከፋ ዞን ቡና እና ጤፍ ዋናዎቹ የገቢ ምንጮች ናቸው፡፡ከአንስሳት ከብት፣በግ፣ፍየል፣ዶሮ፣አህያ፣ፈረስ እና በቅሎ ወናዎቹ የዞኑ ሃብቶች ናቸው፡፡

የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱ የኤክስፖርት ምርቶች መካከል በዋናነት ቡና በስፋት የሚመረትባት፣ውሽውሽ ሻይ ልማት፣ማር ምርት፣ቅመማ ቅመም ወዘተ በከፍተኛ ደረጃ ስለሚመረት ሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ዞኑ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡                            

1.3.የከፋ ዞን የደን ሽፋን እና የብዝሃ ህይወት ጥብቅ ደን ገፅታ

1.3.1. የካፋ ዞን የደን ሽፋን

ከጠቅላላው የከፋ 10,602.7 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ውስጥ የተፈጥሮ የደን ሽፋን ከፍተኛውን የመሬት ሽፋን ይይዛል፡፡ደን እና የተፈጥሮ ጨካ የከፍቾ ብሄረሰብ ኑሮ እና ማህበራዊ ህይወት አንድ አካል ነው፡፡በቅርብ ጊዜ እየወጡ ያሉት የምርምር ውጤቶች እንደሚያስረዱት በከፋ ምድር ውስጥ ባሉት ጫካዎች በአብዛኛው የጫካ የተፈጥሮ ቡና ይበቅላል፡፡ከዚህም በመነሳት በከፋ ጫካዎች ዉስጥ የበቀሉና ተራብተው የሚገኙ ከ5 ሺ በላይ የቡና ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ደን ለከፊቾ ህዝብ ሁሉም ነገሩ ነው ማር፤ኮረሪማ፤ጥምዝ የተለያዩ የተፈጥሮ ፍራፍሬዎች፣ቶጆ፣ጋሮ ስራስሮች ወይም አኖ በከፋ ደን ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡እነዚህ የከፋ የተፈጥሮ ደኖችና ጫካዎች በከፊቾ ብሄረሰብ ባህል ከአባት ወደ ልጅ ሲወራረሹ የመጡ እያንዳንዱ ዛፍ ከትዉልድ ወደ ትውልድ ሺተላለፍ የመጣ እና ባለቤት ያለው ነው፡፡የዚህ የባለቤትነት ባህላዊ የደን እንክብካቤና አጠባበቅ የኮቦ ስርአት ተብሎ ይጠራል፡፡ተፈጥሮ ሀብቱንና ደኑን ለመጠበቅ አስተዋጽኦ ካደረጉት ሀገር በቀል ዕዉቀቶች አንዱ የኮቦ ስርአት ነው፡፡

 

Figure 2የከፋ ዞን የደን ገጽታ በከፊል

1.3.2.የከፋ የብዝሃ ህይወት ጥብቅ ቦታ ወይም ባዮስፌር ገጽታ

በደቡብ ክልል በከፋ ዞን ከ760 ሄክታር በላይ የሚሸፍነው የባዮስፌር ጥብቅ ቦታ በሰኔ 2010.እ.ኤ.አ በዩኔስኮ በአለም የብዝሀ ህይወት ጥብቅ ቦታ ተብሎ ተመዝግቧል፡፡በዚሁ የብዘሀ ህይወት ጥብቅ ቦታ ጥቅጥቅ ደኖች፣የጫካ ቡና፣ረግረጋማ ቦታ፤የግጦሽ መሬት፤የቀርከሃ ደን እና ሌሎችም የሚገኙበት ነው፡፡ከፋ በአለም በብዝሃ ህይወት ከሚታወቁ 34 ቦታዎችአንዱ ነው፡፡ በከፋ ጥብቅ ደን ከ250 በላይ የእፅዋት ዝርያዎች፣የጫካ ቡና የአፍሪካ ቀይ እንጨት፣ቀርከሃ ስድስት መቶ የሚሆን የእንስሳት ዝርያ፣ዝንጀሮ፣ጉማሬ አንበሳ እና የተለያዩ የወፍ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡

የባዮስፌር ጥብቅ ቦታዎች መርህ ብዝሃ ህይወቱን በመጠበቅ የአካባቢ ማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያጎለብት የዘላቂ ልማት ስትራቴጅ ነዉ፡፡ የሰውና  የባዮስፌር ፕሮግራም ሀገራችን በሁለተኛ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዉስጥ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሰጠችውን ልዩ ትኩረት በቀጥታ የሚደግፍ በተጨማሪም በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ያፀደቀችዉን አለም አቀፍ ዘላቂ ልማት ግቦች ወደ ተግባር የማሸጋገሪያ ድጋፍ ሰጭ ፕሮግራም ነው፡፡የባዮስፌር ጥብቅ ቦታዎች በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኙ ሲሆን የሀገራት መንግስታት በቂ የህግ ሽፋን ሰጥተዉ የሚጠበቁ ናቸው፡፡የባዮስፌር ጥብቅ ቦታዎች ህይወት ያላቸው ላብራቶሪዎች ሲሆኑ በተለይም የመሬት፣የውሃ እና የብዝሃ ህይወት ቅንጅታዊ አስተዳደር ውጤታማነት የሚፈተሸበት የምርምር ቦታ ነው፡፡

በአለም ደረጃ የባዮስፌር ጥብቅ ቦታዎች ሰፊ ትስስር እና ኔት ዎርክ የፈጠሩ ሲሆን በዩኔስኮ መረጃ መሰረት በአለም ላይ የባዮስፌር ኔትዎርክ ውስጥ ስድስት መቶ ሃምሳ የባዮስፌር ጥብቅ ቦታዎች ከ 120 በላይ ሀገራት ውስጥ እንደሚገኙ ተብራርቷል፡፡

በባዮስፈር መርህ መሰረት ጥብቅ ቦታዎቹ ለሶስት ዋና ዋና ዓላማዎች የሚዉሉ ሲሆን የተፈጥሮና የባህል ብዝሃነትን ለመጠበቅ በዚህም የብዝሀ ህይወት ዝርየዎች፣ስነ-ምህዳሩና የተለያዩ የእፅዋትና የእንስሳት ዘሮች እነዲጠበቁ ይረዳል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ በጥብቅ ቦታዎቹ አካባቢ ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ልማት በማምጣት ለዘላቂ ልማት፣ለአካባቢ ጥበቃ እና ለባህል እሴቶች መጠበቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ሲሆን

ሶስተኛ የባዮስፌር ጥብቅ ቦታዎቹ ለተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎች ግብአት የሚሰጡ የፕሮጀክት፣የትምህርትና ስልጠና እንዲሁም ልምድ ልውውጥ ለማድረግ በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥበቃና ልማት መረጃዎችን ለመለዋወጥ ይጠቅማሉ፡፡

በአጠቃላይ መልኩ ባዮስፌር ሪዘርቭ ማለት መሬትን፣ደንን፣እርሻ፣ግጦሽናረግረጋማ ቦታዎችን፣የባህር ዳርቻ፣የውሃ አካልና በውስጡ የሚኖሩ ህይወት ያላቸው እፅዋትና እንስሳትን እንዲሁም ሰውንና ባህሉን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ጥናት በዩኔስኮ አስተባባሪ ካውንስል ወይንም ዩኔስኮ ያስቀመጠውን መስፈርት አሟልቶ የተመዘገበ ቦታ ነው፡፡

የባዮስፌር ጥብቅ ቦታዎች በሦስት ደረጃ ተከፍለው የተቀመጡ ሲሆን እነሱም ጥብቅ፣ዳርቻ እና መሸጋገሪያ   (core, buffer and transit) አካባቢ ተብለው ተመድበዋል፡፡

 

 

 

1.4.መረጃ ትንተና እና የጥናቱ ግኝቶች

1.4.1. ለባዮስፌር ጥብቅ ቦታ ዘላቂነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሀገር በቀል ዕውቀቶች

እንደሚታወቀው ሀገር በቀል እውቀት ብዙ ዘርፎች ያሉትና በአንድ ማህበረሰብ ባህል ውስጥ የሚገኝ የእውቀት፣የጥበብና የአስተሳሰብ ሀብት ነው፡፡ይህ ሃብት ብዙ ዘርፎች ያሉት የባህላዊ ክንዋኔዎችና ስርአቶች (rituals) የተፈጥሮ ሃብት አያያዝና አጠቃቀም፣የግብርና እርሻ ዘዴዎች እውቀት፣የደን እና የዱር አራዊት ጥበቃ፤ባህላዊ መድሃኒት፣ቅመማ፤የከብት ጤና አጠባበቅ ባህላዊ የግጭት አፈታትና የዳኝነት ስርአት፤እደጥበባትና ባህላዊ የስራ ፈጠራ ይገኝበታል፡፡ሀገር በቀል እውቀት ብዙ ጊዜ በቃልና በልማድ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የባህል ሃብታችን ነዉ ፡፡ የተለያዩ ፀሃፍት ለሀገር በቀል እውቀት የተለያዩ ስያሜዎችን ይሰጣሉ፡፡ብዙዎቹ የሚነሱት አገራዊ እውቀት በአብዛኛው በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚፈጠር ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚወራረስ፣የህብረተሰብ አባላት ለተለያዩ ማህበራዊ፣አኮኖሚያዊ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች የሚጠቀሙበት የዕዉቀት ሀብት ነው ይላሉ፡፡

በአገር በቀል እውቀት ላይ የፃፉ ምሁራን እንደሚሉት አገር በቀል እውቀት በአንድ የህብረተሰብ ባህል ውስጥ የሚገኝ ልዩ አካባቢያዊ እውቀት ነው፡፡አገር በቀል እውቀት በግብርና፣በጤና አጠባበቅ፤በምግብ ዝግጅት፣በትምህርት፣በተፈጥሮ ሃብት አያያዝ፣በእደ ጥበብና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመስጠትና ዘላቂ ልማት ለማስፈን ጉልህ ድርሻ እንዳለው አረጋግጠዋል፡፡በመሆኑም ሀገር በቀል እውቀት ዘላቂ ለሆነ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፤ለደን፤ለውሃ፤ለአፈር፤ለእርሻ ስራና ለአካባቢ ጥበቃ ያገለግላል፡፡በአሁኑ ወቅት የሰው ልጆች በተፈጥሮ ሃብት መሸርሸርና የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ትልቅ ተግዳሮት እየገጠማቸው ነው፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ የስነ-ምህዳር ለውጦችና ተግዳሮቶች ኢፍትሃዊ ከሆነው የሃብት አጠቃቀም ጋር ተዳምሮ የድሃውን ህብረተሰብ ደህንነት ስጋት ላይ ጥለዉታል፡፡ይህንን ስጋት ለመቀነስ የተለያዩ የተፈጥሮና የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች በቅንጅት የስነ-ምህዳር ጥበቃና መልሶ ማልማት ተግባራት በጥናትና ምርምር እና በፖሊሲ ታግዞ የዘላቂ ልማት ስትራቴጅ አካል እንዲሆን እየሰሩ ነው፡፡

ባህላዊ እውቀት ማህበረሰብ፤ ለችግሮቹ ወይም አኗኗር ተግዳሮቶቹ የሚሰጠው መፍትሄ እራሱን የሚያስተዳድርበት ስልት፣ግጭቶችን የሚፈታበት ዘዴ፣ በሽታን የመከላከል ስልት፣የውሳኔ አሰጣጥ ዘዴዎች እራሱን የሚገልጽበት ጥበቦች፣ተፈጥሮ ሃብትና አካባቢውን የሚጠብቅበት እውቀት ነው፡፡

የከፋ ባዮስፌር ጥብቅ አካባቢ የህብረተሰቡን ዕውቀት ማዕከል ያደረገ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ልማትና እንክብካቤ ይደረግለታል፡፡ ከዳሰሳ ጥናቱ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመዉ በከፋ ብሄረሰብ አራት ዋና ዋና የሀገር በቀል ዕውቀቶች ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና እንክብካቤ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡

1.4.2.የከፊቾ ብሄረሰብ ጉዶ ዲጆ አምልኮአዊ ስርአት    

በከፊቾ ብሄረሰብ ከተፈጥሮ ሀብት እና ከደኑጋር የተያያዘው ትልቁ ባህላዊ ስርአት የባህላዊ የእምነትና አምልኮ ነው፡፡ይህ የአምልኮ ስርአት በባህላዊ የእምነት መሪዎች የሚመራና በተከታዮቹ ተግባራዊ የሚደረግ ከትውልድ ወደትውለድ ሲተላለፍ የቆየ እና አሁን ተግባረዊ የሚደረግ ነው፡፡ይህ አምልኮአዊ ስርአት ጉዶ ዶጆ በመባል የሚጠራ የምስጋና በዓል ያካተተ ነው፡፡ይህ በአል ጥቅጥቅ ባለ ደን ሲከናወን በአካባቢው ገብቶ ዛፍ መቁረጥ፤እሳት መለኮስ፣የዱር እንስሳትን መግደል፤ማሳደድ በእምነት መሰረት የተከለከለ ነው፡፡ደን በሌለበት ተራራ ላይ የእምነቱ ስርአት የማይካሄድ መሆኑን ከተገኘው መረጃ ለመረዳት ችለናል፡፡ደን ከጠፋ የእምነቱ መንፈስ እንደሚጠፋ ይታመናል በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንዳለው በከፋ ደን ውስጥ የደን መንፈስ (sprit of forest)እንዳለ ታመናል::

በከፊቾ ብሄረሰብ በዓመት ሁለት ጊዜ የምልጃ እና የምስጋና ስርዓት ይከናወናል፡፡ይህ ስርዓት በደን ውስጥ የሚከናወን ሲሆን የእህል ምርት በደረሰ ጊዜ እሸት ዝም ብሎ መብላት አይፈቀድም ለደኑ አባት ወይም መንፈስ ቆርሶ ይሰጣል፡፡በታህሳስ ወር ጤፍ ሲደርስ ትልቅ የምስጋና በዓል ተዘጋጅቶ እርድ ተደርጎ ህብረተሰቡ ተሰብስቦ በጋራ እህል ይቀምሳል፡፡አምላካችን ደኑን፣ከብቱን፣ልጆቻችንን ጠብቅልን በማለት ለግፔታቶ ምስጋና ያቀርባል፡፡ይህ ባህላዊ የእምነት ቦታ የተከበረ እና ዳኝነት የሚሰጥበት በመሆኑ ደኑ በትውልዱ ባህላዊ እምነት የተጠበቀ መሆኑ ከዳሰሳ ጥናቱ መረዳት ችለናል፡፡

የካፋ ማሀበረሰብ ታላለቆቹ ዘመናዊ እምነቶች (የክርስትናና እሰልምና ሃይማኖቶች) ወደ ሀገራችን ከመግባታቸው  ከብዙ ዓመታት በፍት ጀምሮ  እያመነና እየከወነ ያቆያቸዉ ባህላዊ እምነት አላቸው፡፡ የዚህ እምነት ተከታዮች የእምነታቸውን ስነስራት የሚያከቡሩት ጥቅጥቅ ባሉት ደን ውስጥ ነው፡፡  በሌላ በኩል ማህበረስቡ እነዝህን ቦታዎች ለማሚለኪነት እነደሚጠቀም መረጃ ሰጪዎቹ ያብራሩ ሲሆን እነዚህ ቦታዎች በባህሉ ቅዱስ ስፍራዎች እንደሆኑ ይታመናል፡፡በዚህ ቦታ ደን መቁረጥ ብቻ ሳይሆን ደኑ ዉስጥ የገባ እንስሳ እንኳን አይነካም፡፡በተጨማርም ይህንን ቦታ ሁሉም ሰው መግባት እንደማይችልና ጥብቅ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

የከፋ ብሄረሰብ እንደሌሎች ብሄረሰቦች ሁሉ ቀደምት ባህላዊ እምነቶች አሉዋቸዉ፡፡በከፋ ያሉ ጎሳዎች (ጉምቦ) የየራሳቸው አምልኮ አዊ መናፍስት አሉዋቸው፡፡እነዚህ መናፍስት ኢኮ የሚባሉ ሲሆን እነዚህን መናፍስት የሚጠቀሙ መንፈሳዊ መሪዎች አላሞዎች ናቸዉ፡፡እነዚህ አላሞዎች ባህላዊ ህክምና በመስጠትና በሽተኞችን በመፈወስ እና ትንቢት በመናገር ይታወቃሉ፡፡

በየአካባቢው ያሉ አላሞዎች ወይም መንፈሳዊ መሪዎች በማህበረሰቡ የተከበሩ እና እውቅና ያላቸው ናቸው፡፡በየአካባቢውና ወረዳው የሚገኙ መናፍስት ስም የሚለያዩ ሲሆን በጨና ወረዳ የሚገኘው ደሞቼች፤ያፌሮቺ ሸረዳ አካባቢ፤ዎግዶች አዲዮ አካባቢ፣አሽሎጅ በአብዛኛው የከፋ አካባቢ የሚሰጥ ስያሜ ነዉ፡፡ ጋራ ማንጅ ቤንቺ፣ናኦ፣ሜኢነት፣እና ጫራ ብሄረሰቦች አካባቢ ዶች ወይም ዴህ ታቴኖ በአብዛኛው የከፋ ክልል የሚገኝ የሁሉም መናፍስት መሪ ሆኖ የሚታይ ነው፡፡ ናዮ መንፈሱን የሚያስተናግዱ መሪዎች ጥቅል ስም ነው፡፡

እንደ ቀደምት ግሪኮችና ሮማዊያን የከፋ መናፍስት የራሳቸው አባትና ንጉስ አላቸው፤የሁሉም መናፍስት አባት በከፋ ዶቺ ወይ ዴህ ታቴኖ ይባላሉ፡፡ይህም ዶቺ-ናኦ በከፋ ብሄረሰብ ዘንድ አብደችኖ ወይም አብዴ ጉዴና ይባላሉ፡፡የጥናት ቡድኑ ከተዘዋወረባቸው ወረዳዎች በአዲዩ ወረዳ በቦቃ አካባቢ ያነጋገርናቸው የከፋ ዋና መንፈሳዊ አባት ኢበዳ ጎዳ አበራ ኢማሞ ይባላሉ፡፡የተለያዩ ጎሳዎች ለመናፍስቱ የሚሰጡት ስያሜ የተለያየ ቢሆንም በጋራ መሪ እና ንጉስ ይመራሉ፡፡በጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም እና ስርአት አላቸው፡፡በደን ጥበቃና እንክብካቤ ላይ መንፈሳዊ መሪዎች ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋሉ፡፡(በቀለ፡2010፡101) 

1.4.3.የከፋ ባህላዊ አስተዳደር እና መዋቅር      

ከፋ ከ13ኛው ከፍለ ዘመን ጀምሮ እጅግ ጠንካራ እና የተደራጀ መንግስትና ንጉሰዊ አገዛዝ ስርዓት ያለው እጀግ የሰለጠነ እና የተደራጀ የፖለቲካ መዋቅር እንደነበረዉ ሰፊ የታሪክ ማሰረጃዎች ያሳያሉ፡፡ይህ ጥንታዊ መንግስት በበላይነት በንጉሱ ወይም በንጉሰ ነገስቱ የሚመራ ቢሆንም ምክረቾ ወይም አማካሪ ካብኔ የነበረው አመራረጡም በችሎታ እና በስነ-ምግባር ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ፀሃፍት ይገልጻሉ፡፡ ንጉሱ በሀገሪቱ የመንፈሳዊ እና ፖለቲካዊ የበላይ መሪ ቢሆኑም የመስፈጸም ትልቁ ስልጣን ያለው በጉጄ ራሾ እጅ ነው፡፡ይህም በዘመናዊው አጠራር ጠቅላይ ሚኒስቴር እንደማለት ነው፡፡የከፋ ንጉስ በባህላዊ አስተዳደር መዋቅር ከፍተኛውን ቦታ የያዘ ቢሆንም ስልጣኑ ግን ውስን አና የተከፋፈለ ነው፡፡በከፊቾ ብሄረሰብ ንጉሳዊ ስልጣኑን የሚይዙት ጎሳዎች የሚንጀ ዴንቱ ወይም ሚንጆ ቡሻሻ ጎሳዎች ናቸው፡፡ለንጉሳዊ ስርአቱ እነዚህ ጎሳዎች የተመረጡት በልማዳዊ መመዘኛ ነው፡፡ንጉሶቹ በመጀመሪያ የሚሰጣቸው ስያሜ ወይም ማዕረግ ታቶ የሚል ሲሆን በኋላ የተለያዩ ነገስታቶች እየተፈጠሩ ሲሄዱ የንጉሰ ነገስት ማዕረግ ወይም አዲዮ ወይም አቲዮ ተብለው ይጠራሉ፡፡በ19ኛው ክፍለ ዘመን የከፋ ነገስታት መቀመጫ ቾንጋ፣ አዲያ፣ቫዳ፣ቦረቲ እ.ኤ.አ 1897 በኋላ ቦንጋ እና አንድራቻ ዋና ከተማ እንደነበረ በቀለ ወ/ማሪያም በመፅሃፋቸው አብራርተዋል፡፡

የከፋ ንጉስ የተለያዩ ሃላፊነቶች የነበሩት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የፍትህና የዳኝነት አስተዳደር፣የጦር ወታደሮች ክትትልና ቁጥጥር፣ሰፈራ፣የጦር ምርኮኞች ቁጥጥር፣አዲስ የተቀላቀሉ ማህበረሰቦች ጉዳ፣የከፋ ህዝቦችና ጎሳዎችን ማስተዳደር፣ለጦር ጀግኖች ሜዳልያና ሽልማት መስጠት፣ለተለያዩ አውራጃ እና ወረዳ ገዥዎች ሹመት መስጠት ናቸው፡፡

በከፋ የአውራጃ ገዥዎች ወራፌ ሪሾ ወይም ወራቤ ራሾ የሚባሉ ሲሆን አውራጃዎቹ ወራፌ ሾዎ ይባላሉ(ላንጌ፡1982፡215)ከአውራጃ ዝቅ ብሎ ያለው ደረጃ ወረዳ ወይም ራሼ ሾዎ የወረዳ አስተዳደር አኩሮ ይባላል፡፡የመጨረሻው ግፔ ታቶ ጉዶ ወይም ቱጌ ኒሆ በመባል መሪዎቹ እስከ ታችኛው እርከን ይታወቃሉ፡፡የከፋ ጠንካራ መንግስት ለጉጂ ራሾ ወይም ዋና ሚኒስትር የሚመራ የሚኒስትሮች ም/ቤት ይገኛል፡፡በሚኒስትር ደረጃ ሹመት ያላቸው ማዕረጎች የሚከተሉት ናቸዉ፡፡

ካታሜ ራሾ--የመከላከያ ሚ/ር

አዋ ራሾ--የፍትህ ሚ/ር

አዲዮ ራሾ --የግንባታ ወይም ኮንስትራክሽን ሚ/ር

ቦዲ ራሽ--የንጉሱ አማካሪ እና ፕሮቶኮል

ሾዴ ራሽ---የማህበራዊ ደህንነት ሚ/ር

አሪቼ ራሽ---- የኮሚኒኬሽን ሚ/ር

በከፊቾ የንጉስ ስርአት ውስጥ የአዝመራ አባት ተብሎ ምስጋና የሚቀርብለት ኮሎ የተባለ መንፈስ ያለ ሲሆን ለዚህ የጣኦት አምላክ የሚቀርበው መስዋዕት ኮሎ-ዴጆ በመባል ይታወቃል፡፡በዚህም ወቅት ትኩስ የሆኑ የእንስሳትና የአዝዕርት ምርቶች እንደመስዋዕት ሆነው ይቀርባሉ፡፡ይህም ምክንያቱ በወቅቱ ጥሩ ሰብል ምርት፣ያልተበላሸ በመሰብሰብ ምክንያት ለአምላካቸው ምስጋና ለማቅረብ እንዲሁም ብዙ ምርት በመገኘቱ ኃይለኛ አዉሎ ንፋስ፣በሽታ፣ከባድ ዝናብ፣መጥፎ ክስተቶች ከህዝቡ በመወገዱ ምክያንት ለማመስገን ነው፡፡(ላንጌ፡1982፡284)

በየጎሳው ይህን የመሰሉ መንፈሳዊ አገልግሎትና ሌሎች የአስተዳደር ስራዎችን የሚያከናውኑ ባለስልጣናት ግፔ ታቶ የሚል ማዕረግ ይሰጣቸዋል፡፡ይህ መንፈሳዊ አባትና መሪ በመፀለዩና ምስጋና በማቅረቡ ምክንያት መሬቱ ተጠብቆ እንደቆየ ይታመናል፡፡

የኮሌ-ዲጆ ሰርአት የሚከናወነው በጤፍ ምርት መሰብሰብ ወቅት ወይም ጋሾ ወይም በበቆሎ ምርት መሰብሰብ ወይም ባሮ ወቅት ሆኖ በታህሳስና በሀምሌ ወራት መጨረሻ ላይ ነው፡፡

የዚህ ምስጋና በዓል ምክንያት መሬት አብቅላ ጥሩ ምርት በመስጠቷ ለምድር ወይም ለመሬት መናፍስት ምስጋና እና መስዋዕት ለማቅረብ እንደሆነ ይታመናል፡፡ከምስጋና በዓል በፊት ሰውነት መታጠብና መንፃት፣ ከሃያ አንድ ቀን በፊት ጀምሮ ግብረ-ስጋ ግንኑነት ያለማድረግ፣ለስርአቱ ምግብ የሚያዘጋጁ ሴቶች ከ አንድ ቀን በፊት ግብረ-ስጋ ግንኙነት ማድረግ አይፈቀድላቸውም፡፡

ይህንን ስርዓት የማይከተሉ አባላት በኮሉ ይቀሰፋሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ሴቶች መስዋዕት የሚቀርቡበትን ግቢ መግባት አይፈቀድላቸውም፡፡ይህንን ስርዓት የሚያስፈፅሙት ግፔ ታቶ ወይም አላሞዎች ናቸው፡፡በስርአቱ ውስጥ ጉድጓድ ተቆፍሮ በጉድጓዱ ውስጥ ዶሮ ታርዶ ደሙ ይረጫል፡፡ እህሉ፣ ጠላ እና ዳቦ አብሮ በጉድጓዱ ዉስጥ ተጨምሮ እንዲህ በማለት ይጨፈራል፡፡

                                       ንጉሳችንን ጠብቅ     

              መንግስታችንን ጠብቅ

          እህል በሰፊው አትረፍርፈህ ስጠን ይላሉ፡፡

ይህ ምስጋና በዓል በከፊቾ ብሄረሰብ ለጥብቅ ደኖች መቆየትና ዘላቂነት አስተዋፅኦ ያላቸው ከመሆኑም ሌላ አምልኮአዊ የዛፍ አጠባበቅ (sacred forests) ዘዴ አንዱ የሀገር በቀል እውቀት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ይህም ስርአት ብሄረሰቡ ለደኑ ካለው አክብሮትና ተፈጠሮን የማምለክ፤የመጠበቅ ስልትና ዘዴ ነው፡፡

በከፊቾ ብሄረሰብ የደን መንፈስ (sprit forest) እንዳለ ይነገራል፡፡ደኑ እና ውስጡ ያሉ ዛፎች የቅድመ አያት መናፍስት ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ህብረተሰቡ ዛፍን ይመርቃል፣እንደ ሰብአዊ ፍጡራን ይንከባከባል፡፡ደን የቆረጠ ሰው እንደገደለ ይቆጠራል፡፡ በከፊቾ ደን ከሌለ መንፈስ የለም ተብሎ ይታመናል፡፡አንድ ኃይል (super natural) በደን ውስጥ እንደሚገኝ ይታመናል፡፡ በባዮስፌር ፅንሰ ኃሳብ ጥብቅ (core area) በባህሉ ምስጋና የሚቀርብበት ከሰው ጋር ንክኪ የሌለው ቦታ ነው፡፡በዚህ ቦታ ያለው መንፈስ ጉዶ ተብሎ ይጠራል፡፡

የጥናት ቡድኑ በመስክ ባደረጋቸው ምልከታ እና ቃለ መጠይቅ በአንጎቅላ ቦቃ ቀበሌ፣በአዲዮ ወረዳ አቢዮ ጎዳ አበራ ኢማሞ በከፊቾ ዋና መንፈሳዊ መሪ ቃለ መጠይቅ ሲሰጡ የከፊቾ ማህበረሰብ ደን ጥበቃ ከባህላዊ የእምነት ስርአቱ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ዛፍ ያለ አግባብ የቆረጠ በኢበዳ ጎዳው ይዳኛል፣ይቀጣል፣ይረገማል፣ከማህበረሰቡ ይገለላል፡፡በደን ጭፍጨፋ ውስጥ የተሳተፉ አካላት በህዝብ መወያያ አደባባይ ሾዴ ኬሎ በቂ ውይይት ወቀሳ ቅጣት ይጣልባቸዋል፡፡  

የካፋ ማህበረሰብ ለዘመናት ሲተዳደር የነበረበት፣ የራሱ የሆነ ጥንታዊ ባህላዊ አስተዳደር ስርዓት ካለቸው ጥቅት የሀገራችን የህብረሰብ ክፍሎች አንዱ ነው፡፡የካፋ ማህበረሰብ በባህለዊ አሰተዳደረ ውስጥ የደን  ጠባቂ የሚል የስራ መደብ በባህላዊ አስተዳደር ዉስጥ እንዳለ የሀገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡ይህም የማዕረግ ስም ጉዶ ታቶ ይባላል፡፡እንደ መረጀ ሰጭዎች አገለለጽ ከሆነ ይህ ባህላዊ ደን የሚያስተዳደረው ክፍል የዛሬውን የደንና አከባብ ጥበቃ ሚንስቴር ጋር የሚመሳሰል ስልጣን ያለው መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገለጹ ተደምጠዋል፡፡በዘሁ የባህል አስተዳደር ውስጥ  የአንድ ጎሳ ከሌላ ጎሳ ዛፍን እንዳይቆርጥ እያንዳንዱ የጎሳ አባል በጥንቃቀ የራሱንና የሌላውን የጎሳ አባለት ይዞታ የሆነውን በተደረጀ መልኩ ይጠብቃሉ፡፡በአጋጣሚ ሆኖ ዛፍ ተቆርጦ ከተገኘ ከሆነ ሁሉም የጎሳ አባለት እንደተደፈሩ ይቆጡሩታል፡፡ባህላዊ የዳንኝነት ስርዓት ሌላኛዉ በካፋ ማህበረሰብ ሀገር በቀል እውቀት አንዱ ሲሆን ለደን ጥበቃዉ ከፍተኛ አሰተዋጾ እንደሚያደርግ የመረጃ ሰጭዎቹ አብራርተዋል፡፡

1.4.4. የኮቦ የከፊቾ ብሄረሰብ የደን እንክብካቤና አጠባበቅ ስርአት 

የኮቦ ስርአት በተፈጥሮ ጫካ ውስጥለብዙ ሺ አመታት ማህበረሰቡ በስምምነት ክልሎ አና ተከፋፍሎ እየጠበቀ ለትውልድ የሚየስተላልፍበትስርአት ነው፡፡በኮቦ ስርአት ውስጥ ማህበረሰቡ የየራሱ ድንበር ያለው ሲሆን በክልሉ ውስጥ ለማር ምርት ቀፎ የመስቀል፤የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ለምሳሌ እንደ ኮረሪማ፤ቡና ጥምዝ የመጠቀም መብቱ በኮቦ ስርአት የተጠበቀ መብት ነው፡፡

በኮቦ ስርአት ውስጥ በየክልሉ እና ድርሻ ውስጥ ያለውን ምርት የመጠበቅ መብትና ግዴታ ይኖረዋል፡፡በእያንዳንዱ ክልል ውስጥ ፍቃድ ሳያገኝ መግባት፣ቀፎ መስቀል፣ቡና መልቀም፣ዛፍ መቁረጥ እጅግ የተከለከለ ነው፡፡ባህላዊ የኮቦ ስርአት ውስጥ የደን አጠባበቅ ጉዳይ እጅግ ጥብቅ ነው በዚህም የብሄረሰቡ አባላት ደንን ከሰው ለይተው አይመለከቱም፡፡አንድ የደን ዛፍ እንደ አንድ የቤተሰብ አባል ከትዉልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ እንክብካቤ የሚደረግለት ነው የኮቦ ስርአት የደን አጠባበቅ የማህበራዊ አደረጃጀት ስርአት ነው፡፡

በከፊቾ ብሄረሰብ ልዩ ከሆኑት ባህላዊ ሰርአቶች አንዱ በቤተሰብ ሐረግ፣ዘር እና ጎሳ ተከትሎ የሚወራረስ የደን አጠባበቅ ክፍፍልና አጠቃቀም ስርአት ኮቦ ነው፡፡ በኮቦ ስርአትና ደንብ መሰረት በአንድ የደን ማሳ ውስጥ የተለያዩ ቤተሰቦች በግል እና በጋራ የደን ሀብቱን ማለትም የማር ቀፎ፤ቡና፤ቅመማ ቅመም እና ሌሎች ተክሎች እያመረቱ የሚጠቀሙበት ከትውልድ እስከ ትውልድ የሚተላለፍ ስርአትና ደንብ ነው፡፡

ይህንን ስርአት እና ደንብ ተከትሎ ህብረተሰቡ ደን የመጠበቅና የመንከባከብ ባህል አዳብሯል፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ የኮቦ የሀገር በቀል እውቀት ደንብ በመኖሩ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፤ዘላቂ ልማትና ትብብር በህብረተሰቡ ዳብሯል፡፡ይህም በመሆኑ ዛፎችን ደን እና ሀገር በቀል ተክሉን ማልማት መልሶ መትከልና ተፈጥሮውን የመጠበቅ ባህል ስር የሰደደ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ መሆኑ ከዳሰሳ ጥናቱ መረዳት ችለናል፡፡

ይህ ማህበረሰብ ከሌላው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ክፍል በተለየ ሁኔታ ደንን እንደ አንድ ቤተሰብ በተምሳሌታዊነት ይመለከተዋል፡፡ አንድ ዛፍ የአንድ ሰው ነፍስ ያህል ይታያል፡፡‘’ አንድ ዛፍ ከአንድ የሰው ነፍስ እኩል ናት’’ ይላሉ፡፡ስለዚህ በማህበረሰብ ባህል ሰውን መግደል በጣም የተወገዘዉን ያህል ዛፍን ያለግባብ መቁረጥ ውግዝ ነው፡፡አንድ ዕድሜ ጠገብ ዛፍ በጓሮ ካለ በቤተሰብ ዉስጥ የረጀም ዕድሜ ባለቤት ይኖራል  ተብሎ ይታመናል፡፡አንድ ትልቅና ዕድሜ ጠገብ  ዛፍ  የዚያን ግለሰብ መኖሪያ ዕድሜን፣የሀብት መጠንና ማህበራዊ ደረጃ የሚያሳይ  ምልክት ነው ይላሉ፡፡ ለምሳሌ  አንዱ መረጀ ሰጭ እንደተናገሩት ይህን ዛፍ ያዉረሱኝ አባተናቸዉ ስለዚህ ይህን ዛፍ ከአባቴ ለይቼ አላየውም ስሉ ተናግሯል፡፡

የማህበረሰብ ሳይንሰ ምሁራን ባህል የአንድን ሰው አስተሳሰብና አመለካከት የመቀየር ከፍተኛ አቅም እንዳለው ይገልጻሉ፡፡ስለሆነም ካፍቾን፤ጫራና ናኦ ማህበረሰብ ደን ላይ ያላቸው አመለካከት የሚመነጨው ከራሳቸው ባህል ነው፡፡ ይህ ማህበረሰብ ደንን እንደ ልብሱ፣መኖሪያ ቤቱ እና ምግቡ እንዲሁም ማንነቱ እንደሚመለከት  መረጀ ሰጭዎች ተናግሯል፡፡ስለዚህ ልብሱ እንዲቀደድና እንዲበላሽበት እንድማይፈቅድ ሁሉ ደን በዘፈቀደ እንዲቆረጥ አይፈቀድም፡፡በባህሉ  ሀገር በቀል የሆነ ደን የመትከል ስርዓት አለ፡፡በብሄረሰቡ የደን ዛፍ ለይቶ ለተለያዩ አገልግሎቶች ያዉላል፡፡ከነዚህም ዉስጥ የሚሰሶ ዛፍ፣የማር፣ለቤት ማገር፣ለመጋዶ የሚጠቀማቸዉ ዛፎች ይለያያሉ፡፡በከፍቾ ማህበረሰብ ደንና ማህበራዊ ሕይወቱ የተቆራኙ ናቸዉ፡፡

1.4.5. ናሎ የከፋ ባህላዊ የፍትህ ስርአት

በከፋ ማህበረሰብ ከጥንት ጀምሮ ሲተላለፍ የቆየ ባህላዊ የፍትህ ስርአት አለዉ፡፡ይህም ስርአት በስድስት ደረጃዎች የተከፋፈለ ሲሆን የንጉሱ ፍርድ ቤት ኡምቦቴ፣የወንጀል ፍርድ ቤት  ሁኬ ታቶ፤የፍትሃ ብሄር ያፔ ታቶ፣የወረዳ ፍ/ ቤት ዎራቤ ታቶ፣አጠቃላይ ፍርድ ቤት ዝግ እና ክፍት ተብሎ ለሁለት ይከፈላል፡፡ያጊ ታቶ ክፍት ችሎት ሲሆን ይህ ደግሞ ዝግ ችሎት ተብሎ ይታወቃል፡፡

በከፋ የናሎ የግጭት አፈታት ስርአት እና ፍርድ ቤት ውስጥ የተፈጥሮ ደን አጠባበቅ ጉዳይ ትኩረት ያገኘ ነው፡፡በባህሉ ያለአግባብ ዛፍ አይቆረጥም እንደ ነውር እና ወንጀል የሚቆጠር ነው በዚህ ስርአት ውስጥ ደን ጠባቂ ማእረግ የሚሰጠው ባለስልጣን ቆምቤ ጉዶ ወይም ጉዶ ታቶ ይባላል፡፡ ዛፍ የቆረጠ ያለ አግበብ የጣለ ካለ በባህላዊ አስተዳደሩ ይጠየቃል፡፡ በደን ውስጥ የህግ ከለላ የተሰጣቸው ቦታዎች ምንም አይነት የሰው ንክኪ እና ግንኙነት አይኖራቸውም፡፡ጥብቅ ቦታዎች ናቸው እነዚህ ጥብቅ የደን ክልል በባህሉ ሸራሼዎ የሚባሉ ሲሆን በዘመናዊው የባዮስፌር ፅንሰ ሃሳብ (core area) የሚባሉ ናቸው፡፡

እነዚህ ቦታዎች በተለያዩ ሀገር በቀል ተክሎችና ደኖች የተከበበ ነው በነዚህ ትላልቅ ዛፎች ስር ቡና አለ፡፡ዛፍ በሌለበት ቡና አይኖርም ዛፍ የቡና ከለላ እና ጥላ ሆኖ ያገለግላል፡፡በቡና ስር ኮረሪማ ይኖራል፣ከኮረሪማ አጠገብ ጥምዝ ይኖራል፡፡እነዚህ ተክሎች ተመጋጋቢ ናቸው፡፡

እነዚህ ተክሎችና ደኖች የአየር ንብረቱን ይጠብቃሉ፡፡ህብረተሰቡን ይመግባሉ፡፡ደኑ የህብረተሰቡ የህይወት አካል ነው፡፡በባህላዊ አስተዳደሩ ውስጥ ለቤት መስሪያ የሚጠቀሙበትን ምሰሶ ለመቁረጥ ባህላዊ ውስጥ መሪዎችን ጠይቀው ከመቁረጥ ውጭ ያለምክንያት ደን መቁረጥ የሚያስቀጣ ነው፡፡ ዛፍ ያለአግባብ ከወደቀ ህብረተሰቡ ያዝናል፡፡

1.5.የከፍቾ ብሄረሰብ ማህበራዊ መዋቅርና አደረጃጀት

የከፋ ስርዓተ-መንግስት ከ1896 ጀምሮ ከፍተኛ ለውጥ ላይ ነበር፡ማህበራዊ መዋቅሩና አደረጃጀቱ በስራ ደረጃ፣በቤተሰብና በዘር የተደራጀ ነበር፡፡የከፋ ማህበረሰብ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ በሦስት የዘር ምንጭ የተከፋፈለ ነው(ላንጌ፡1982፡239)እነዚህም ዋቶ፣ከፊቾ እና ሲዳማ ይባላሉ፡፡ሌሎች አጥኝዎች የከፋ ማህበረሰብ ወይም ከፊያኖ በዘጠኝ ዞኖች እና ዋና ዋና ቤተሰቦች ይከፋፈላሉ(ባይቨር፣1906፡202) እነዚህም

1.ጎንጋ (ካፊቾ)

2.ሼ

3.ናኦ

4.ናጋዶ

5.ማንጆ

6.ህናርዮ(እናሪያ)

7.ጎንጌቾ

8.ጉራቦ

9.ዳጄቦ

ከነዚህም የመጀመሪያዎቹ አራቱ ያሮ ወይም አማሮ ተብለው የክርስትና እምነት ተከታይ ጎሳዎች እንደሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በሌላ በኩል የከፋ ማህበረሰብ በእምነቱ ደረጃ በሦስት ይከፈላል ይህም የከፋ ሙስሊም ማህበረሰብ ናጋዳ፣የክርስቲያን ማህበረሰብ አማሮ እንዲሁም የከፋ እምነት የለሽ እና ሌሎች ጎንጋ እና ዕደ ጥበብ ባለሙያዎች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ሌሎች ፀሃፊያን የከፋን ማህበረሰብ ንጉሳዊያን እና ተራ ማህበረሰብ በሚል ለሁለት ይከፍሉታል፡፡ሆኖም የከፋ ዋና የጎሳ ግንድ በሁሉም ዘንድ ጉምቦ በመባል ይታወቃል፡፡በጉምቦ የጎሳ ዋና ግንድ ውስጥ 10 ንዑሳን ጎሳዎች አሉ እነሱም አኪ፣ጎዲ፣ጉቺ፣ማሂ፣ሼቾ፣ሺሎ፣ማሪ፣ኩሊ፣አቲ ናቸው፡፡ በአጠቃይ በከፋ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ጎሳዎች ቁጥር ወደ 242 እንደሚደርስ ጥናቶች ያብራራሉ፡፡

1.6. የከፊቾ ብሄረሰብ ትውፊታዊ ትውን ጥበባት ለባዮስፌር ጥብቅ ስፍራ ቀጣይነት ያለው አስተዋጽኦ

     ትውፊት ከዘመን ዘመን  ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር  የሚመጣ አንድ የጥበብ ዘርፍ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ትውፊት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያስተላልፋቸውን እሴቶች ሙሉ በሙሉ ሳይቆራረጡና ይዘታቸውን ሳይለቁ  ለሚቀጥለው ትውልድ ይደርሱታል ማለት ግን አይቻልም፡፡ ትውፊትን ተቀብሎ ለሚቀጥለው ትውልድ የሚያስተላልፈው ትውልድ ለራሱ የሚመቹትን አጉልቶ የማይመቹትን ትውፊቶች ቀንሶ ያወርሳል፡፡በዚህ ቅብብሎሽ አማካኝነት ትውፊት የራሱን ቀለምና ይዘት ሊለቅ ይችላል፡፡የብሄረሰቡ ትውፊታዊ ትውን ጥበባት ለከፋ ጥብቅ ደን ቀጣይነት ያላቸውን ሚና ስንመለከት ከሚከተሉት ትውፊታዊ የተውኔት አላባውያን አንጻር ይሆናል፡፡እነሱም

1.ቃለ ምልልስ

2.ሚና ክፍፍል

3.ከዋኝ

4.አልባሳት

5.ቁሳቁስ

6.የመከወኛ ቦታና ጊዜ ናቸው፡፡

 

 

1.ቃለ ምልልስ

በሁለትና ከዛን በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል የሚደረግ ንግግር ሲሆን ሰዎች አጥንተውት ሳይሆን ድንገታዊ በሆነ መልኩ የሚናገሩት ንግግር ነው፡፡

2.ሚና ክፍፍል 

ሚና ክፍፍል ማለት ተውኔቱ በቡድን የሚከወን  እንደመሆኑ መጠን ሰዎች የሚሰሩትን፣ የሚናገሩትን፣የሚለብሱትን፣ወዘተ.በመልክ በመልኩ የሚያደርጉት ድርጊት ወይም በተውኔት ውስጥ የስራ ክፍፍል ማለት ነው፡፡

3.ከዋኝ

ትውፊታዊ ተውኔቱ ለመድረክ ሲበቃ ድርጊቱን (የተከፋፈሉትን ሚና) የሚከውኑ ማናቸውም ሰዎች ከዋኝ ይባላሉ፡፡

4.አልባሳት

ትውፊታዊ ተውኔቱ ለመድረክ ሲበቃ ከዋኞች የሚለብሱት ልብስ ነው፡፡ ይህ ልብስ የስርአቱን ባለቤት፣ የማህበረሰቡን ታሪካዊ ዳራ፣ባህል፣የእድሜ ደረጃ፣የትምህርት ሁኔታ  ወዘተ. ያሳያል፡፡

5.ቁሳቁስ

ትውፊታዊ ተውኔት ሲከወን በመድረኩ ላይ ከዋኞች የሚጠቀሟቸው ቁሶች ሲሆኑ የትውፊቱን ባለቤቶች  የስልጣኔ ምንጭና ማንነት ይጠቁማል፡፡በተጨማሪም ያላቸውን ክብርና ስልጣን በሚዪዙትና በሚጠቀሙት ቁሳቁሶች ይገለጻል፡፡

Figure 3የከፋ ማህበረሰብ የመገልገያ እቃዎች

6.የመከወኛ ቦታና ጊዜ

ትውፊታዊ ተውኔት አቀራረቡ እንደሌሎች የቴአትር አይነቶች በቴአትር አዳራሽ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ክፍት ቦታ (Open air) ይታያል፡፡ ነገር ግን ይህ የመከወኛ ስፍራ የማህበረሰቡን ትክክለኛ ድርጊያ (ማህበራዊ እውነታ) መልቀቅ የለበትም፡፡ ስለሆነም ትውፊታዊ ተውኔቱ በዋርካ ስር፣በወንዝ ዳር፣በተራራ ላይና ከማህበረሰቡ ባህላዊ ትርዒቶች ጋር በተቆራኙ ቦታዎች ላይ ይቀርባል፡፡

    በከፋ የጥብቅ ደንና የብሔረሰቡን ባህላዊ ክንዋኔዎችንና ትስስርን ከላይ በተዘረዘሩት አላባዊያን መሰረት እንመለከታለን፡፡ በመሆኑም በከፋ ብሔረሰብ ዘንድ ብሄረሰቡ ከጥንት ጀምሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲቀባበለው የቆየ የተለያዩ ባህላዊ እምነቶች፣ ልማዶችና መልካም እሴቶች አሉ፡፡ ባህላዊ እምነቶችና እሳቤዎች በብሄረሰቡ ትልቅ ቦታ በሚሰጣቸው የእምነት  አባቶች የሚመራ ነው፡፡

       እነዚህ እምነቶችና አስተሳሰቦች በዞኑ የሚገኘውን ደን በዩኔስኮ የአለም ቅርስ (ጥብቅ ደን) በመሆን እንዲመዘገብ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ከነዚህ እምነቶችና አስተሳሰቦች መካከል የሚከተሉትን እንመልከት፡

1.የዴጆ ስርአት

     ይህ ስርአት በአብዛኛው የከፋ ብሔረሰብ ዘንድ የሚተገበር ሲሆን አላማው ለፈጣሪ ምስጋና ማቅረብ (thanks giving) ነው፡፡የዴጆ ስርአት በብሄረሰቡ ዘንድ በአመት ሁለት ጊዜ ይካሄዳል፡፡ ይህም ገበሬዎች ጤፍ፣ በቆሎና የመሳሰሉትን አዝዕርቶቻቸውን ከሰበሰቡ በኋላ በቀጥታ ምርቱን ወደ ጎተራቸው ከማስገባታቸው በፊት ሠብሉ ተወቅቶ በአውድማው ላይ እንዳለ ከቤት የተዘጋጀውን ምግብና መጠጥ የአካባቢው ነዋሪዎች ተሰባስበው ፈጣሪያቸው አዝመራቸውን ስለባረከላቸው፣ ቤተሰቦቻቸውን ሰላም ስላደረገላቸው፣ አዝመራው ለልጆቻቸውና ለጎረቤቶቻቸው በሰላም ስለደረሰ በአካባቢው ላለ ቆሌ (አድባር) የምስጋና ስነ-ስርአት ያካሂዳሉ፡፡ በስርአቱ ላይ የተለያዩ ምግቦች ይቀርባሉ፡፡ በሚቀርቡ ምግቦች መካከል ከጤፍ የሚሰራ መጠጥ (ሸኮ)፣ ዶሮ፣ ቆጮና ማንኛውም ቤት ያፈራው ምግብ በስርአቱ ላይ የሚቀርብ ይሆናል፡፡

       በዚህ ስርአት ላይ የተጣሉ ግለሰቦች በበአሉ ቦታ ታዳሚ ሊሆኑ አይችልም፡፡ስለዚህ ወደ ስርአቱ ቦታ ለመሄድ የተጣሉ ሁሉ መታረቅ አለባቸው፡፡በዴጆ ስርአት ላይ ለእርድ የሚቀርብ በሬ በአካባቢው ነዋሪዎች ይዘጋጃል፡፡ ይህ በሬ ሲታረድ ቢለዋ አንገቱ ላይ ሲያርፍ ሊጮህም ላይጮህም ይችላል፡፡ይህ ሲባል በሬው ሊታድ ሲል ከጮኸ የተጣላ ሰው በበአሉ ቦታ እንደሌለ ያመለክታል፡

      ነገር ግን በሬው ሊታረድ ሲል ካልጮኸ የተጣሉ ሠዎች በቦታው መገኘታቸውን ይገልጻል፡፡ በዚህ ወቅት የአካባቢው ታላላቅ ሰዎች የተጣሉት ሰዎች እነማን እንደሆኑ በመጠየቅ እንዲታረቁ ያደርጋሉ፡፡ በስርአቱ ላይ ታላላቅ አባቶች ይመርቁና የስርአቱ ፍጻሜ ይሆናል፡፡

 

 

 

 

2.  የኢበዳ ጎዳ ባህላዊ የእምነት መሪ

አበራ ኢማሞ አሊቶ በተባሉ ግለሰብ አማካኝነት የሚፈጸም የእምነት ስርአት ነው፡፡ይህ እምነት በዘር የሚወራረስ ሲሆን መንፈሱ ያለበት ግለሰብ ካረፈ በግለሰቡ ልጅ አልያም የቅርብ ዘመድ ላይ መንፈሱ ይታያል፡፡መንፈሱ በአዲስ መልክ የታየበት ተተኪው ሰው በአለ ሲመት ይፈጽማል፡፡ በእለቱም ግለሰቡ በእምነቱ ተከታዮች በመታጀብ ወደ ወንዝ በመሄድ 50 ከብቶች እንዲታረዱ በማድረግ መንፈሳዊ አባትነቱን በይፋ ያውጃል፡፡ኢበዳ ጎዳ ማለት በግለሰቡ (በባለ ውቃቢው) ላይ ያደረው የመንፈስ ስም ሲሆን አበራ ኢማሞ አሊቶ የግለሰቡ ስም ነው፡፡በዚህ ግለሰብ አማካኝነት የተለያዩ ስርአቶች ይፈጸማሉ፡፡በአካቢው ያሉ ነዋሪዎቸም ይሁኑ ከሌላ አካባቢ (ሀገር) የሚመጡ ባለጉዳዮች የደረሰባቸውን በደል፣ጭቆና፣ወንጀል ወዘተ በመናገር መፍትሄ የሚያገኙበት ስርአት ነው፡፡ መንፈሱ በዞኑ ያለውን የደን ሀብት ህዝቡ መጠበቅ መንከባከብ እንዳለበት ይመክራል፣ ያስተምራል፡፡የዚህ እምነት ቦታ በግለሰቡ መኖሪያ ግቢ ሲሆን የተቸገሩ ሁሉ በመምጣት መፍትሄ እንዲያገኙ ያደርጋሉ፡፡የኢበዳ ጎዳውን ቃል አልሰማም አልቀበልም የሚል ሰው ካለ መንፈሱ (ኢበዳ ጎዳው) እምቢተኛው ሰውዬ ባንቀላፋበት (በህልሙ) ባለ አንድ ስለት ባለው ጦር ያስፈራራዋል፡፡ ይህ እምቢተኛ ሰው አሁንም የመንፈሱን ቃል አልቀበልም ቢልና በአቋሙ የሚፀና ከሆነ አሁንም ዳግመኛ ባለ 7 ስለት ባለው ጦር መንፈሱ በህልሙ ያስፈራራዋል፣ሲገለው ይመለከታል፡፡ (በህልሙ የሞተ መስሎ እንዲታየው ያደርጋል፡፡በመጨረሻ  ግለሰቡ ጥፋቱን ካመነ ወደ ኢበዳ ጎዳ አበራ ዘንድ በመሄድ  ጥፋቱን ያምናል፤ ይቅርታቸውን ይማጸናል፡፡ ነገር ግን ይህንን ባያደርግ እና በእምቢተኝነቱ ቢቀጥል መንፈሱ ይገለዋል፡፡

Figure 4ባህላዊ እምነት መሪ

     ቤተሰቡም ይጠራና ልጃቸው የሞተው ኢበዳ ጎዳው (መንፈሱ) ያዘዘው ለመፈጸም ፈቃደኛ ባለመሆኑ የተነሳ እንደሆነ ይነገረቸዋለ፣(በእራሱ በመንፈሱ)በዚህ ወቅት ቤተሰቡ እንዲህ አይነት ጥፋት እንዳይደገም ይለምናሉ፣ ይሰግዳሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ይህ አይነቱ ቅጣት ለመላው የአካባቢው ነዋሪዎች የማሳመኛና የማስፈራሪያ ትምህረት ሆኖ በመጥቀሙ ምክንያት ማንም ሰው የእምነቱ አባት ከተናገሩት ንግግር ውልፍ የሚል አይኖርም፡፡

3. ባህላዊ እርቅ ስነ-ስርዓት አፈፃፀም

       ይህ የማሸማገል ተግባር የሚፈፀመው ገደቢ ታቴ (የእምነት አባት) ኃይለሚካኤል ጋኒ በተባሉ ግለሰብ አማካኝነት ነው፡፡እኚህ ሰው በአካባቢው ማበረሰብ ዘንድ እንደ አንድ የእምነት አባት ይታያሉ፡፡ የእምነት አባቱ ለቤተሰቦቻቸው 13ኛው የእምነት አባት ሲሆኑ  ከእሳቸው በፊት አባታቸው 12ኛው የእምነት አባት ነበሩ፡፡የእምነት አባትነት ማዕረጉ በዘር ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ በመሆኑ በአንድ የዘር ግንድ ስር ላሉ ተተኪዎች ብቻ የሚወራረስ ነው፡፡ ይህ ባህላዊ ዕርቅ የሚፈፀመው በእምነት አባቱ (በአስታራቂው) ግለሰብ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ማንኛውም ተበዳይ ወደዚህ ቤት በመምጣት የበደለውን ሰው ማንነት ይናገርና ይሄዳል፡፡ የእምነት አባቱም አቤቱታውን ከሰሙ በኋላ ወደ በዳዩ ግለለሰብ መልእክተኛ በመላክ እንደሚፈለግ ይነግረዋል፡፡ በተቀጠሩበት ቀን ተበዳይና በዳይ ግለሰቦች ይቀርባሉ፡፡ የእምነት አባቱ የራሳቸው የስጋ ዘመድ የሆኑ የተወሰኑ ሽማግሌዎች አሏቸው፡፡እነዚህ ሽማግሌዎች ሰዎችን ለማስታረቅ የተሾሙ (የተመረጡ) ግለሰቦች ናቸው፡፡ማንኛውም ክስ ሲቀርብ የእምነት አባቱ በበዳይና ተበዳይ የቀረበውን ክስ ከሰሙ በኋላ እነዚያ በእርሳቸው የተመረጡ ሽማግሌዎች እንዲያስሟሟቸው ያደርጋል፡፡ሁለቱ ባላንጣዎች በአስታራቂ ሽማግሌዎች አማካይነት መታረቅ ከቻሉ ወደ እምነት አባቱ በመቅረብ መስማማታቸውን በመግለፅ ከእግራቸው ስር ይወድቃሉ፣ (ይሰግዳሉ)፡፡ ነገር ግን በዳይና ተበዳይ በተመረጡት ሽማግሌዎች መታረቅ ካልቻሉ ጉዳዩ ወደ እምነት አባቱ ይመጣና እሳቸው በወሰኑት ማንኛውም ውሳኔ ጉዳዩ እልባት ይሰጠውና እንዲታደረቁ ይደረጋል፡፡በዳይና ተበዳይ ሽማግሌዎቹ ካሏቸው ቃል መውጣት ቢችሉ እንኳን የእምነት አባቱ ካሏአው ቃል ግን መውጣት አይችሉም፡፡ በማንኛውም የፍርድ ውሳኔ ይስማማሉ፡፡የበደለው አካል የእምነት አባቱ የወሰኑትን ያህል ገንዘብ ካሳ ለተበዳይ እንዲከፍል ይወሰንበታል፡፡ካሳ የተቆረጠለት ተበዳይ በበኩሉ ካሳውን ሙሉ በሙሉ የመቀበልም ይሁን ምህረት የማድረግ መብቱ የእርሱ ነው፡፡

    

Text Box: Figure 5ባህላዊ ዳኝነት

Figure 5የባህላዊ ዳኝነቱ መሪ

 በዳይናተበዳይከታረቁበኋላያላቸውንአቅማቸው የፈቀደውን ያህል ብር መስጠት ይችላሉ፡፡ በስጦታው አይገደዱም፤ይህ ባህላዊ የፍርድ አሰጣጥ ሂደት የሚመለከታቸው የተለያዩ ጉዳዮች (cases) አሉ፡፡ ለምሳሌ የድንበር ጉዳይ፣ የባልና ሚስት ግጭት፣ የስርቆት ወንጀል፣ የእምነት ክህደት፣ የስም ማጥፋት ወንጀል ወዘተ አይነት ችግሮች በዚህ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት እልባት የሚያገኙ ጉዳዮች ናቸው፡፡

        ከላይ የተመለከትናቸው ስርአቶችና የእምነት አባቶች ተግባር የአንድ ማህበረሰብ የማንነት መገለጫዎች ናቸው፡፡ይህ ሲባል በሀይማኖታዊ ስርዓቶች ውስጥ የማህበረሰቡ (የብሔረሰቡ) ትውፊት፣ ፍልስፍና፣ ስነ-ልቦና፣ ወግ፣ ስነ-ቃል፣ ወዘተ በኪነ-ጥበብ ሊገለፅ የሚችል ቱባ የባህል ሀረግ የሚመዘዝ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

4 ዕሳቤዎች

በካፋ ብሔረሰብ ዘንድ ባህሉን ከጥብቅ ደኑ ጋር የሚያቆራኙ የተለያዩ እሳቤዎች አሉ፡፡ እነዚህ እሳቤዎች ደኑ ከጥንት ጀምሮ ተጠብቆ እዲቆይ የራሳቸው ጉልህ ተፅእኖ ይፈጥራሉ፡፡ ከእነዚህም እሳቤዎች መካከል፡-

 

 

 

 

ሀ) የጎዶ እሳቤ

      ጎዶ በብሔረሰቡ ዘንድ የሚከበር ስለ ረቂቅ መንፈስ የሚደረግ ስርዓት ነው፡፡መንፈሱ የሚኖረው እጅግ ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ በመሆኑ ወደ ጫካ ለመግባት የሚያስፈራ ይሆናል፡፡ በተጨማሪ ወደ ጥቅጥቅ ደን ለመግባት ሴቶች እስከ ሰባት ቀን ያህል ከወር አበባ የፀዱ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

             ወንዶችም በተመሳሳይ ንፁህ ሆነው በንፁህ ልቦና ካልሆነ በስተቀር ወደ ጫካው መግባት አይችሉም፡፡የአካባቢው ነዋሪዎች የአንድን ሰው ንፅህና የሚያረጋግጡባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ወደ ጫካ ለመግባት ለሚፈልገው አካል ነዋሪዎቹ የሚሰጡትን ምግብ እንዲበላና እንዲጠጣ ይደረጋል፡፡በመሆኑም በዚህ በጉዶ ስርአት ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ልጆቻቸው ቢታመሙ ወይም ሌላ አዲስ ክስተት ቢፈጠር ይህን የሚያደርገው በዚህ ጥቅጥቅ ደን ውስጥ የሚኖር መንፈስ ነው በማለት የተለያዩ ምግብና መጠጦችን ይዘው ወደ ጫካው ይሄዳሉ፡፡ ይህ ስርአት የሚከናወነው ልጆቻቸው እንዳይታመሙ ሠፈር፣አካባቢ ሠላም እንዲሆን በማሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ደን ከሌለ ቆሌ የለም፡፡ ደን ሲኖር የሆነ ጥሩ መንፈስ ይኖራል ያርፍበታል የሚል ባህላዊ እሳቤ ይራመዳል፡፡

 

 

ለ/ አደገኛ አራዊትን ማራባት

      ሌላው ጥብቅ ደኑ ተጠብቆ እንዲቆይ እንደምክንያት የሚጠቀሰው ዓውሬዎችን ማራባት ነው፡፡ ብሔረሰቡ ደኑ እንዳይጠፋ የተለያዩ የዱር አራዊትና ተሳቢ ፍጥረታት እንዲራቡ ያደርጋል፡፡ ማንኛውም ሰው ወደ ጫካው በማምራት ዛፍ ለመቁረጥ ወይም ወደ ውስጥ  ለመግባት ቢፈልግ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የሚነገረው የማስፈራሪያ አፈታሪክ እንዳይገባ ያደርገዋል፡፡ በጫካው ውስጥ የጅቦች መራቢያ፣ የእባቦች መራቢያ፣ የትንኝ መራቢያዎችና ገደላማ ስፍራዎች እንዲፈጠሩ በማድረግ ለማስፈራሪያነት ይጠቀሙበታል፡፡ስለሆነም ማንም ሰው ይህንን እየሰማ ወደ ጥቅጥቅ ደኑ የመግባት ድፍረቱ አይኖረውም፡፡

ሐ/ ደኖች የሰዎችን ችግር  ተጋሪ ስለመሆናቸው

     ጥንታዊ ደኖች ችግርን ለመካፈል ይጠቅማሉ፡፡ይህ አይነቱ እሳቤ የሚፈፀመው አንድ ሰው በህልሙ በተደጋጋሚ የሞተ ሰው ካየ ህልሙን ለሰው ከመናገር ይልቅ በደን ውስጥ ወደሚገኝ ረጅምና ጥንታዊ ዛፍ ጋር በመሄድ ያየውን ህልም ለዛፉ በሚገባ ይናገራል፡፡ ከዚያ በኋላ በህልሙ ያንን የሙት መንፈስ ዳግመኛ አያየውም፡፡

      ከዚህ ጋር ተያይዞ ማናኛውም የአካባቢው ነዋሪ ማንኛውንም አይነት ህልም ባለመ ጊዜ (ባየ) ጊዜ የህልሙን ፍቺ ለሰው እንዲናገር አይመከርም ይልቁንም ወደ ጫካ (ወደ ጥቅጥቅ ደን) ሄዶ ከትልቅ ዛፍ ስር ቁጭ ብሎ ህልሙን ተናግሮ ይመጣል፡፡ “ያለምከውን ህልም ለሰው ከምትናገር ወደጫካ ሄደህ ለዛፍ ተናገር” የሚባል ብሂል ይዘወተራል፡፡ህልማቸውን ለሌሎች ሰዎች ቢናገሩት ሰዎቹ የተለያየ አይነት ፍቺ ይሰጧቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ በጥሩ መልኩ ሲተረጉሙ ሌሎች ደግሞ የህልሙን ፍቺ አስፈሪ ያደርጉታል፡፡ ከዚህ ፍርሃት ለመሸሽና ከአላስፈላጊ የስነ-ልቦና ጫካ ለመዳን ሲባል ለግለሰቦች አይናገሩም፡፡ዛፉ ግን ሰምቶ መናገር ስለማይችል ባለህልሙ የዛፉን ዝምታ በጥሩ ጎን ይተረጉመዋል፡፡

መ/ የመቃብር ስፍራዎች

     በብሔረሰቡ ዘንድ ሁለት አይነት የመቃብር ስፍራዎች አሉ፡፡ እነሱም

            1, ማሾ የመቃብር ስፍራና

            2. ሞጎ የመቃብር ስፍራ

 

1/ ማሾ

     የመቃብር ስፍራ የሚገኘው በጥቅጥቅ ደኖች ውስጥ ሲሆን በዚህ የመቃብር ስፍራ የሚቀበሩ ሰዎች ተራ ግለሰቦች (ምንም ታዋቂነት የሌላቸው ) ሰዎች ናቸው፡፡

2/ ሞጎ

    ተብሎ የበሚጠራው የመቃብር ስፍራ ላይ የሚቀበሩ ሰዎች ደግሞ በብሔረሰቡ ዘንድ የሚከበሩ፣ የሚፈሩና ታዋቂ ሰዎች የሚቀበሩበት ስፍራ ነው፡፡ይህ የመቃብር ስፍራ እንደ ማሾ የመቃብር ስፍራ ሁሉ በጥቅጥቅ ደን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ማንም ሰው ከደኑ አንዲት ዛፍ እንኳን መቁረጥ አይችልም፡፡ምክንይቱም መቃብሩ በመኖሩ የተፈራ እና የተከበረ ቦታ ሆኖ ይኖራል፡፡ይህ ክልከላ በዞኑ ለሚገኘው ጥብቅ ደን ከፍተኛ ከለላ በመሆን ከመመንመን እና ከጥፋት አድኖታል፡፡

 

ሠ/ የኮሎ ዴጆ ባህላዊ የክልከላ ደንብ

       ይህ ደንብ በዋናነት ማንም ሰው ወደ ደን እንዳይገባ እና ዛፉ እንዳይቆረጥ የሚከለክል ስርአት ነው፡፡ስርአቱ ማንም  ወደ ደን እንዳይገባ የሚከለክል በመሆኑ የስርአቱን ክልከላ ተላልፎ ወደ ደን የሚገባና የሚቆርጥ ሰው በጠና ይታመማል የሚል ንግርት በመኖሩ ምንም ቢሆን ደኑ ውስጥ መግባትና ለመቁረጥ ድፍረት አይኖረውም፡፡ይህም የደኑ ማቆያ አንዱ ጥበብ ነው፡፡

5 የከፍቾ ብሔረሰብ ሙዚቃ

      የከፋ ዞን ብሄረሰብ ከጥንት ጀምሮ ሲጠቀሙባቸው የቆየ ባህላዊ ሙዚቃዎች አሏቸው፡፡ እነዚህ ሙዚቃዎች በተለያዩ ሀይማኖታዊ ክብረ በአላት፣በሰርግ፣በማህበራዊ ጉዳዮች (የጋራ ዝግጅቶች ላይ) በአዲስ አመት ወዘተ ላይ ይዜማሉ፡፡እነዚህ ባህላዊ ዘፈኖች የማህበረሰቡን ማንነትና ከደን ጋር ያላቸውን ቁርኝት አጥብቀው የሚገልፁ ናቸው፡፡

       በከፋ ሰው እና ደን ተለይቶ አይታይም፡፡ማንኛውንም ዛፍ የቆረጠ ግለሰብ አንድ ሰው እንደገደለ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህን የመሳሰሉ አስተሳሰቦችን የሚያንፀባርቁ ባህላዊ ውዝዋዜዎችና ሙዚቃዎች አሉ፡፡ የዞኑ ወረዳዎች በቁጥር 11 ሲሆኑ በቦንጋ በየአመቱ ለአዲስ አመት ለመስቀል በዓል ባህላቸውን የሚያሳዩበት ቦታ ተሰጥቷቸው የእንግዶች ማረፊያ ቤት ገንብተዋል፡፡የቤቶቹ አሰራሮች የየወረዳቸውን የቤት አሰራር ባህል የሚያንጸባርቁ ናቸው፡፡ይህ ስርአት ከጥንት የከፋ ነገስታት ጀምሮ በየዐመቱ መስከረም ሲጠባ የሚደረግ ታላቅ የአዲስ አመት ዝግጅት ነው ይህ ዝግጅት የሚካሄደው በከፋ ነገስታት ቤተ-መንግስት አካባቢ ነው፡፡ዝግጅቱን ከየወረዳው የተመረጡ የሀገር ሽማግሌዎች (በአካባቢው አጠራር አላሙዎች) ያስጀምራሉ፡፡የዝግጅቱ መክፈቻ የሚሆነው ፈረሰኞች ፈረሳቸው ላይ እንዲቀመጡ በማድረግ ሲሆን  የፈረሶቹ አይነት ጥቁር፣ነጭና ቀያይ ፈረሶች ሲሆኑ እያንዳንዳቸው መቶ መቶ ፈረሰኞች ናቸው፡፡እነዚህ ፈረሰኞች በሽማግሌዎቹ ትእዛዝ መሰረት ሾሻ ወደምትባል ቦታ ሄደው አካባቢው ሰላም መሆኑን፣በሽታ አለመኖሩን፣ችግር አለመኖሩን፣ዝናብ መዝነቡን አይተው እንዲመጡ ይደረጋል፡፡ሾሻ ተብላ የምትጠራው ስፍራ የከፋ ነገስታት መነሻ ቦታ ናት፡፡ በዚህ የተነሳ ፈረሰኞቹ ቦታዋን አይተው ይመጣሉ፡፡ ሲመለሱ የጉግስ ስነ-ስርአት ይካሄዳል፡፡ እያንዳንዱ ወረዳ ካለው የህዝብ ብዛት አንጻር በሬዎች ይታረዳሉ፡፡ የአዲስ አመት ዘፈኖች ይዘፈናሉ፡፡ይሁን እንጂ የዞኑ ባህል ቱሪዝምና ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ተወካይ እንደገለጹት ዛሬ ላይ የቀድሞው ትውፊት በተወሰነ መልኩ እየቀረ እንደመጣ ይገልጻሉ፡፡

         ይህም ሲባል ጥንት በነገስታቱ ጊዜ የፈረሰኞች ቁጥር ነጭ 100 ፈረሰኞች፣ጥቁር 100 ፈረሰኞና ቀይ 100 ፈረሰኞች የነበሩት ዛሬ ላይ ነጭ 10፣ጥቁር 10፣ቀይ ፈረሰኞች 10 በድምሩ 30 ፈረሰኞች ብቻ እዲሳተፉ  ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ፈረሰኞቹ በሽማግሌዎቹ  ሾሻን አይተው እዲመጡ ሲታዘዙ ፈረሰኞቹ ወደ ሾሻ አቅጣጫ ጥቂት ሄድ ብለው ይመለሳሉ፣ደርሰው እደመጡ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በአካባቢው የቦታ ጥበት መኖሩ እንደ አንድ ምክንያት ይቆጠራል፡፡በእለቱ የተለያዩ ባህላዊ የዳንስ  (የውዝዋዜ) ትእይንቶች ይካሄዳሉ፡፡ ይህ ስርአት መከወኑ ለዞኑ የኪነ-ጥበብ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ፡፡

     5.1 የሙዚቃ መሳርያ

         በከፋ ብሄረሰብ ዘንድ የተለያዩ ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያዎች መኖራቸውን በብሄራዊ የቡና ሙዝየም ውስጥ ተመልክተናል፡፡ አብዛኛዎቹ  የሙዚቃ መሳርያዎች የትንፋሽ መሳርያዎች ሲሆኑ ስሪታቸው ከዱር እንስሳት ቀንድ፣ከደንና ከብረት የተገኙ የትንፋሽ መሳርያዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የተወሰኑትን እንመልከት፡

 • ሸመቶ፡ ከጎሽ ቀንድ  የተሰራ  የትንፋሽ መሳርያ ሲሆን በሰርግ እና በሀዘን ቀን የሚነፋ የሙዚቃ መሳርያ ነው፡፡
 • ትሮ፡  ይህ የሙዚቃ መሳርያ የትንፋሽ ሲሆን ሰዎች ወደ አደን ሲወጡና አንድ ጎጆ ቤት ከአንድ ቦታ ነቅሎ ወደ ሌላ ቦታ ይዞ ሲኬድ የሚነፋ የትንፋሽ  መሳርያ ነው፡፡
 • ሽምብራ፡   ባለ ሦስት ቀዳዳ የትንፋሽ መሳርያ ሲሆን በማንኛውም ዝግጅት ላይ የሚነፋ የሙዚቃ መሳርያ ነው፡፡
 • ሂኖ፡ በባህላዊ መንገድ ልጆች ከተገረዙ በኋላ የሚነፋ የትንፋሽ መሳርያ ነው፡፡
 • ቲምቦ፡ ይህ የሙዚቃ መሳርያ ከእንጨት የተሰራ ሆኖ በትልቅነቱ ይጠቀሳል ፡፡ በአብዛኛው አገልግሎቱ በነገስታቱ  ጊዜ አውሬዎችን ለማባረር ማታ ማታ  የሚነፋ የትንፋሽ  መሳርያ ነው፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ክፍል ሁለት

2.የካፋ ባዩስፌር ጥብቅ አካባቢ የኢኮቱሪዝም ልማት ጥናት

2.1.የካፋ ብዝሃሕይወት ዓለም አቀፍ ጥብቅ ቦታና የኢኮ ቱሪዝም አቅም

የካፋ ብዝሀሕይወት ዓለም አቀፍ ጥብቅ ቦታ ከሚሸፍነው አጠቃላይ 760,144 ሄክታር ቦታ ውስጥ 55.6% የሚሆነው በደን የተሸፈነ ነው፡፡ቦታው ካለው የባህር ወለል ስብጥር ከ500 – 3350 ሜትር በላይ በመሆኑ ለተለያዩ እፅዋትና እንስሳት መኖሪያ ነው፡፡ በካፋ ብዝሃ ሕይወት ዓለም አቀፍ ጥብቅ ቦታ እስከ 250 የሚደርሱ የእፅዋት አይነቶች፣300 የአጥቢ እንስሳት አይነቶች እና 300 የአዕዋዕፍት አይነቶች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ አዕዋፍት ውስጥ 11 የሚያህሉት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቦታው የቡና (Coffee Arabica) መገኛ ነው፡፡

 

በካፋ ዞን በሚገኘው የካፋ ብዝሃ ሕይወት ጥብቅ ቦታ በርካታ ለቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ ቦታዎች ይገኛሉ ከነዚህም መካከል የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በካፋ ብዝሃሕይወት ላይ እየሰራ የሚገኘው NABU ፐሮጀክት እስካሁን በጥብቅ ቦታው ውስጥ ወደ 22 የሚደርሱ የቱሪስት መዳረሳችን ለይቷል፡፡ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ መስፍን እንደገለፁት ከነዚህ መዳረሻዎች መካከል፣ ብሔራዊ የቡና ሙዚየም፣ አለምጎኖ የአዕዋፍት መጉብኛ ስፍራ፣ ፍል ውሃዎች፣ ፏፏቴዎና ክፍት ሙዚየም (Open Air Museum) ይገኝበታል፡፡

 

በአጠቃላይ በጥብቅ ቦታው የሚገኙ መዳረሻዎች በርካታ ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል፣ ፍል ውሃዎች ፣ ፏፏቴዎች፣ ውሃ አዘል ቦታዎች፣ ታሪካዊ የእምነት ቦታዎች፣ ወንዞች፣ ደን እና ጫካዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በዞኑ የባህልና ቱሪዝም እና የመንግስት ግንኙነት ጉዳሮች ጽ/ቤት ከተዘጋጀው የጎብኚዎች መምሪያ መፅሀፍ ላይ የተገለፁ መዳረሻዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

 

 

2.2.የካፋ ዓለም አቀፍ የባዮስፌር ጥብቅ ቦታ የቱሪዝም ሁኔታ መሰረተ ልማት

የካፋ ዞን ዋና ከተማ ቦንጋ ከአዲስ አበባ በ466 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን ሙሉ አስፋልት መንገድ ነው፡፡እንደ አጠቃላይ ጥብቅ ስፍራው የሚገኝበት ካፋ ዞን ከመሰረተ ልማት አኳያ፡-

 • ወደ ዞኑ ዋና ከተማ የሚወስድ አስፋልት መንገድ፤
 • የዞኑን ወረዳዎች የሚያገናኝ የጠጠር መንገድ(ሳይለም ወረዳ በመንገድ አልተሳሰረም)፤
 • የመብራት፣ የውሃና የስልክ አገልግሎት፤
 • የቦንጋ አጠቃላይ ሆስፒታል፤
 • በሁሉም ወረዳዎች ጤና ጣቢያና በሁሉም ቀበሌዎች ጤና ኬላ፤
 • አንድ መምህራን ኮሌጅ፤
 • አንድ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ፤
 • አንድ ዩኒቨርሲቲ (በግንባታ ላይ)፤

ከሞላ ጎደል ዞኑ መሰረታዊ የሆነ የመሰረተ ልማት ግንባታ አቅም ያለውና አካባቢውን ወደ ቱሪዝም ሀበያ ለማስገባት የሚያስችል መነሻ ሁኔታ አለው፡፡

2.3.ሆቴልና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት

ዞኑ እንደ አጠቃልይ የሆቴልና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከፍተኛ ክፍተት ያለበት ቢሆንም ለቱሪዝም መስፋፋት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉና አካባቢውን ለመጎብኘት ለሚሄዱ ቱሪስቶች አገልግሎት መስጠጥ የሚችሉ ሁለት ያህል በመሰረታዊ የሆቴል ደረጃ የሚመደቡ ሆቴሎች ይገኛሉ፡፡

2.4.የቱሪዝም እንቅስቃሴውን የሚያግዙ ማህበራት

በዓለም አቀፍ ጥብቅ ስፍራው ውስጥ በአካባቢው እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ናቡ በተባለ የጀርመን ድርጅት አማካኝነት የቱሪዝም እንቅስቃሴውን እንዲያግዙ በማሰብ የተቋቋሙ

 • የፈረስ አከራይዮች ማህበራት፤
 • አንድ የአካባቢ አስጎብኝ ማህበር፤
 • የንብ አናቢዎች ማህበር፤
 • ምግብ አብሳዮች ማህበር፤
 • የዕደጥበብ አምራቾች ማህበር፤ ወዘተ ይገኛሉ፡፡እነኚህም ማህበራት በአካባቢው የቱሪዝም እንቅስቃሴው ከፍ እንዲል ቢደረግ እራሳቸውን ከመጥቀማቸው ባሻገር ለአካበቢው ልማት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችሉ እሙን ነው፡፡

2.5.የካፋ ዓለም አቀፍ የባዮስፌር ጥብቅ ስፍራ የጉብኝት መስመሮች

በአካባቢው ቱሪዝምን ለማስፋፋት እየተንቀሳቀሰ ያለው ናቡ የተባለ የጀርመን ድርጅት ዓለም አቀፍ የቱሪዝም አማካሪ በመመደብ በጥብቅ ስፍራው አካባቢ የጉብኝት መስመር ብሎ ከለያቸው መካከል የሚተሉት ይገኙበታል፡-

 • ቦንጋ---ጊምቢ---አዲዮ የጉብኝት መስመር፡- ይህ የጉብኝት መስመር በአካባቢው የሚገኘውን 17000 ሄክታር ያህል የሚሸፍነውን ተፈጥሮአዊ የቅረቀሃ ደን ለመጎብኘት አይነተኛ መስመር ነው፡፡
 • የዴቻ ወረዳ ጌደም ቀበሌ የቡና ልማት ጉብኝት መስመር፡- ይህ የጉብኝት መስመር ከቦንጋ ከተማ የ7 ኪሎ ሜተር ጊዞ የሚሸፍን ሲሆን መስመሩ የከፍታኛ ቦታ የቡና ልማት እንቅስቃሴን ለመመልከት አይነተኛ መስመር ሲሆን ከመስመሩ ጋር ተያይዞ የለሙ የቱሪስት ካምፒንግ ሳይቶችንና ሌሎች አገልግሎቶችን ማግኘት ይቻላል፡፡
 • ጌላ የጫካ ቡና የጉዞ መስመር፡- ይህ የጉዞ መስመር ከቦንጋ ከተማ 5 ኪ.ሜ እርቀት ጀምሮ መጎብበት የሚቻልበት መስመር ሲሆን ተፈጥሮአዊ የቡና ጫካን ለመጎብኘት ዓይነተኛ መስመር ነው፡፡
 • የውሽ ውሽ ሻይ ልማት የጉዞ መስመር፡- ይህ መስመር ከቦንጋ ከተማ በ18 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን መስመሩ በሃገሪቱ ውስጥ ትልቅ የሆነውን የውሽ ውሽ የሻይ ልማት እርሻን ለመጎብኘት አይነተና መስመር ነው፡፡
 • አንጃ ቆላ የጉዞ መስመር፡- ይህ መስመር ከቦንጋ ከተማ በ 64 ኪ.ሜ ርት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከፊል በርሃመ ቦታ ነው፡፡መስመሩ የአካባቢውን ባህላው የአስተዳደር ሁኔታና የእምነት አተገባበርን ለመረዳትና ለማወቅ ወሳኝ የሆነ የጉዞ መስመር ነው፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት የጉዞ መስመሮች በተጨማሪ በጥብቅ ስፍራው ውስጥ የሚገኙ ሌሎች መስህቦችን መጎብኘት የሚቻል ሲሆን ከእነዚህ መስህቦች ውስጥ የሚከተሉትን መመልከት ይቻላል፡፡

 

 

ፏፏቴዎች፡ በካፋ ዞን ስድስት ያህል ፏፏቴዎች የሚገኙ ሲሆን እነዚህም ፏፏቴዎች ከ5 ኪ.ሜ. - 135 ኪ.ሜ ከቦንጋ ከተማ ርቀው የሚገኙ ናቸው፡፡ ፏፏቴዎቹም ኤሌሎ፣ በርታ፣ ሻኮ፣ ፋጭ ጉዶ፣ አዲዮ እና ዎሺ ይባላሉ፡፡ ኤሌሎ ፏፏቴ 30ሜትር ወርድ እና 25 ሜትር ቁመት ያለው ሲሆን በዚህ ፏፏቴ ስር እስከ 500 ሰው መያዝ የሚችል የዋሻ ጉድጓድ ይገኛል፡፡ በርታ ፏፏቴ 5 ኪ.ሜ. ከቦንጋ የሚርቅ ሲሆን 20 ሜትር ወርድ እና 50 ሜትር ርዝመት አለው፡ አዲዮ ፏፏቴ ደግሞ በአማካይ 20 ሜትር የሚደርሱ ሦስት ፏፏቴዎች የሚሰራ ፏፏቴ  ነው፡፡

 

ፍል ውሃዎች፡ በዞኑ ሦስት ፍል ውሃዎች የሚገኙ ሲሆን እነርሱም፤ ዳዲቤን፣ ቀጪ እና ጎራ ቅዱስ ፍል ውሃ ናቸው፡፡ ዳዲቤን ፍል ውሃ 39 ኪሜ ከቦንጋ የሚርቅ ሲሆን የአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከል እንዲሁም ለመፈወስ ይጠቀሙበታል እንዲሁም ለመዝናኛነት የሚውል ፍል ውሃ ነው፡፡ይህ ፍል ውሃ በደን የተከበበ መሆኑ በጣም ተወዳጅ ነው፡፡ ቀጪ ፍል ውሃ 43 ኪሜ ከቦንጋ የሚርቅ ሲሆን ከሁሉም ፍል ውሃዎች ሞቃት ነው፡፡ ጎራ ቅዱስ ፍል ውሃ 48 ኪሜ ከቦንጋ የሚርቅ ፍል ውሃ ሲሆን በሚያምር መልክአ ምድር እና ደን የተከበበ ነው፡፡ በአካባቢው ማህበረሰብ እንደ ፍቱን መድሃኒት የሚቆጠር ፍል ውሃ ነው፡፡

 

ዋሻዎች: በካፋ ዞን በርካታ ዋሻዎች ሲገኙ ከነዚህ መካከል ኮሼራ፣ ቦሬቲ፣ ኢኬሮ፣ ዶሻ፣ ቂቲማ/ዩሜያ እና አቤ ጊፒ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡አቤ ጊፒ ትልቁና ጥልቁ የተፈጥሮ ዋሻ ሲሆን ከቦንጋ ከተማ 55ኪሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ቂቲማ/ዩሜያ ዋሻ ደግሞ ከቦንጋ ከተማ 80 ኪሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህ ዋሻ የተለያዩ ክፍሎች አሉት እንዲሁም የአካባቢው አዋቂዎች ይህ ዋሻ አዲዮ እና ጤሎ ወረዳዎችን እንደሚያገናኝ ይናገራሉ፡፡

   

ተራሮች: በካፋ በርካታ ተራሮች የሚገኙ ሲሆን ዋና ዋናዎቹ ሺጤራ፣ሮሻ እና ሾጣ ሲሆኑ ሌሎች ከባህር ወለል በላይ 2539 – 2828 ሜትር ድረስ የሚረዝሙ ተራሮች በካፋ ይገኛሉ፡፡ ሺጤራ ተራራ ከባህር ወለል በላይ 3348 ሜትር ከፍታ ይለው ሲሆን በቀርከሃ ጫካ የተሸፈነ ነው፡፡ እንዲሁም እንደ ኮሶ ያሉ እየተመናመኑ ያሉ የዛፍ ዝርያዎች የሚገኙበት ነው፡፡ ይህ ተራራ ከቦንጋ ከተማ 42ኪሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ሮሻ ተራራ ከባህር ወለለል በላይ 3258 ሜትር የሚረዝም ሲሆን በቀርከሃ እና በኮሶ ዛፍ ጫካ የተሸፈነ ነው፡፡ሾጣ ተራራ ደግሞ ከባህር ወለለል በላይ 3168 ሜትር የሚረዝም ተራራ ነው፡፡

 

የተፈጥሮ ድልድይ (የእግዜር ድልድይ)፡ 10 ኪሜ ከቦንጋ ከተማ ርቆ የሚገኝ ስፍራ ነው፡፡ ይህ ድልድይ በስሩ ጊቻ ወንዝ የሚያልፍ ሲሆን በላዩ መተላለፍ የሚያስችል ድልድይ ነው፡፡ ድልድዩ በጫካ የተከበበ መሆኑ ለጎብኚዎች አስደሳች ይሆናል፡፡

 

ውሃ አዘል ቦታዎች (Wetlands)፡ በካፋ ዞን ሦስት ያህል ውሃ አዘል ቦታዎች የሚገኙ ሲሆን እነዚህም ሜዳቦ፣ አለምጎኖ እና የጎጀብ ወንዝ ውሃ አዘል ቦታ ወይም ጎዴፎ ናቸው፡፡ጎዴፎ ወይም የጎጀብ ወንዝ ውሃ አዘል ቦታ 60 ኪሜ ከቦንጋ የሚርቅ ሲሆን በአካባቢው እንደ አንበሳ፣ አቦ ሸማኔ፣ ጎሽ፣ ነብር እንዲሁም የተለያዩ የውሃ እንስሳት እና አእዋፍት ይገናሉ፡፡

 

ታሪካዊ የእምነት ቦታዎች፡ በካፋ ዞን ከ500 ዓመታት በፊት ጀምሮ በተለያዩ ወቅቶች የተመሰረቱ በርካታ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ያገኛሉ ከነዚህም መካከል ቁንጌ ሚጪ/ጎፓ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ይገኝበታል ምንም እንኳን በዚህ ስፍራ ቤተክርስቲያን ባይኖርም የኦርቶዶክስእምነት ተከታዮች በየአመቱ የጊዮርጊስን ንግስ በዚህ ስፍራ ያከብራሉ፡፡ ኩቲ ቅዱስ ሚካኤል፣ ጪሪ ቅዱስ ሚካኤል እና ባሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በ1529 ዓ.ም የተመሰረቱ በዞኑ የሚገኙ ቤተክርስቲያኖች ናቸው፡፡ እንዲሁም በካፋ ዞን በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተመሰረተ ቶጎሎ የሚባል መስጊድም ይገኛል፡፡

 

በካፋ ዞን ሌሎች መዳረሻዎችና መስህቦች ያሉ ሲሆን ከነዚህም መካከል ማኪራ (የቡና መገኛ ቦታ)፣ የመሬት ጆሮ፣ ጨና የጅብ ጎሬ፣ የካፋ ነገስታት መካነ መቃብር (18 የካፋ ነገስታት የተቀበሩበት ቦታ) እንዲሁም መስከረም 15 የካፋ ዘመን መለወጫ አከባበር ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

 

 

 

2.6. በዚህ የዳሰሳ ጥናት በተመራማሪዎች የተጎበኙ መዳረሻዎች

 1. የቡና ሙዚየም

የዚህ የብሔራዊ ቡና ሙዝየም የግንባታ መሰረተ ድንጋይ የሚሊኒየም በዓል አከባበርን ምክንያት በማድረግ በወቅቱ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ በሰኔ 21 ቀን 1999ዓ.ም የተጣለ ነው፡፡ ይህ የቡና ሙዚየም በሚያዚያ 6/ 2007ዓ.ም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተመርቋል፡፡ ሆኖም እስካሁን ስራ ካለመጀመሩ ባሻገር በርካታ ችግሮች ይስተዋሉበታል፡፡

Figure 6 Figure 7 የቡና ሙዚየም

 

 

በሙዚየሙ ውስጥ የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ የማብሰያና የመመገቢ ዕቃዎች፣ አልባሳትና ማጌጫዎች፣ ስዕሎች፣ የጦር መሳሪዎች እና የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች ይገኛሉ፡፡ ከሙዚየሙ ስፋት ጋር ሲነፃፀር አሁንም ባዶ የሆነ ያህል በዙ ቁሳቆሶች ያስፈልጉታል፡፡

 

በዋናነት የዚህ ሙዚየም ሃላፊነት ማን እንደሆነ በግፅ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዳገኘነው መረጃ ባለድርሻ አካላት ቢሰየሙም ምንም አይነት እንቅስቃሴ እስካሁን አልተደረገም፡፡ የሙዚየሙ ርክክብ እስካሁን አልተፈፀመም፡፡

 

እንደ ጥናት ባለሙያ የቡና ሙዚየሙን በጎበኘንበት ወቅትም ምንም እንኳን ርክክብ ባይፈፀምበትም ህንፃው ላይ በሚያሰጋ መልኩ የሚታዩ መሰነጣጠቆች እንዳሉ፣ ሙዚየሙ መግቢያ በር እንዲሁም አጥር እንደሌለው፣ የመብራት አገልግሎት እንደሌለው፣ መሰማማት በሚያስቸግር መልኩ የድምጽ ማስተጋባት ችግር እንዳለ፣ ብርሃብ እንዲያስገቡ የተዘጋጁ ትንንሽ ባለመስታወት መስኮቶች በኩል ውሃ እንደሚገባ ማየት ችለናል፡፡ በተጨማሪም በርካታ የሌሊት ወፎ በሙዚየሙ ውስጥ ይገኛሉ፣ ቆሻሻቸውም በየወለሉ ላይ ይታያል፡፡ እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ የሌሊት ወፎቹ መግቢያ እስካሁን አይታወቅም፡፡

 

 1. ሙዚየም እና የካፋ ዘመን መለወጫ

 

ክፍት ሙዚየሙ ከቦንጋ አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን በቦታውም ጥንታዊ የካፋ መንግስት ምን እንደሚመስል ማየት ይቻላል፡፡ በክፍት ሙዚየሙ የመጨረሻው የካፋ ንጉስ ቤተ መንግስት እንደገና ተሰርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በካፋ ዞን የሚገኙ ወረዳዎች ባህላዊ ቤት አሰራሮች የሚንፀባረቅበት ስፍራ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የካፋ ህዝብ ዘመን መለወጫ በዓል በዚህ ስፍራ ይከበራል፡፡

 

Figure 8የከፋ ክፍት ሙዚየም(open air museum)

 

ስፍራው ለዕይታ በጣም ሳቢ ቢሆንም ከቤቶቹ ውጪ ምንም ነገር ስለሌለ ህይወት አልባ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ጥሩ ታሪክ ካለ ጥሩ የቱሪስት እርካታ ይኖራል፡፡ ከዚህ አኳያ ሪ እዛ ስፍራ ላይ ስላለው ታሪክ እና የቤት አሰራሮች ማስታወሻ ነገር በስፍራው ቢገኝ ቦታውን የሚጎበኙ ሰዎች በቂ መረጃ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ከእያንንዳንዱ ወረዳ ቤት አሰራር በተጨማሪ የየወረዳው ልዩ የሆኑ መገልገያዎችም በሰፍራፍ ቢኖሩ መልካም ነው፡፡

 

የካፋ ህዝብ በየዓመቱ መስከረም 15 የዘመን መለወጫ በዓሉን ያከብራል፡፡ ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዳገኘነው መረጃ ይህ በዓ በክፍት ሙዚየሙ አቅራቢያ ይከበራል፡፡ ሆኖም በዚህ በዓል ላይ ታድመው የሚያውቁ ቱሪስቶች የሉም፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 1. ጫካ

                    Figure 9 የቀርከሃ ደን

Figure 10የቀርከሃ ጫካ

               

 

በካፋ ዞን ሁለት ወረዳዎችን የሚያዋስንና 17,000 ሄክታር የሚሸፈን የቀርከሃ ጫካ ይገኝል፡፡ በዛ አካባቢ ቱሪስቶች የሚያርፉበት ቦታ ቢመቻች ስፍራው ጥሩ የቱሪስት መዳረሻ እንደሚሆን ይታመናል፡፡

2.6.4.የአለም ጌኖ ውሃ አዘል ቦታ አእዋፍትን መመልከቻ ቦታ

ምንም እንኳን ቦታውን የጎበኘንበት ሰዓት ወፎችን ለመመልከት አመቺ ባይሆንም ስፍራውን ለመጎብኘት እድል አግኝተን ነበር፡፡ ይህ ስፍራ ከዋና መንገድ ዳር ላይ የሚገኝ እና ለአዕዋፍት ምልከታ አመቺ ነው፡፡ በውሃ አዘል ቦታውም ወደ 90 የሚደርሱ የአእዋፍት አይነቶች ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ስፍራውን እንዳየነው እንዲሁም ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንደተገኘው መረጃ በክረምት ወቅት ወደቦታው መሄድ በጣም ከባድ ነው፡፡ ስፍራውን በክረምት ወቅት መኖብኘት የሚቻልበትን ሁኔታ ከማመቻቸት አንፃር ስራዎች መሰራት ይኖርባቸዋል፡፡

Figure 11  አለም ጎኖ ወፎች በብዛት የሚታዩበት ዕርጥበት አዘል ቦታ(wet land)

2.6.5.ታትማራ የቡናና የማር አምራቾች ማህበር

ታትማራ የቡናና የማር አምራቾች ማህበር በእስራኤል ለ8 ዓመታት በስራ ላይ በቆዩ ኢትዮጵያዊ የተመሰረተ ማህበር ሲሆን ስፍራው በቀድሞ ዘመን የካፋ ነገስታት ምህረት የሚያደርጉበት ስፍራ አቅራቢ የሚገኝ በመሆኑ ታትማራ ተብሏል ትርጉሙም የንጉስ ምህተት ማለት ነው፡፡ የአቶ ንጉሴ የእርሻ አሁን አሁን አንዱ የቱሪስት መዳረሻ እየሆነ የመጣ ሲሆን በተለይም በናቡ በኩል የሚመጡ ቱሪስቶች የአቶ ንጉሴን እርሻ ቦታ ሳያዩ አይሄዱም፡፡ አይተውም እንደወደዱት ይገልፃሉ፡፡ አቶ ንጉሴ እንደሚሉት ቢያንስ 10 ቱሪቶች በሳምንት የእርሻ ቦታውን ይጎበኛሉ፡፡

 

 

                  Figure 12ታትማራ የቡና ልማት ማህበር

2.7. መሰረተልማትና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት

የአስፓልት መንገድ ከአዲስ አበባ ቦንጋ ድረስ ያለ ሲሆን ሁሉንም ወረዳዎች የሚያገናኝ ጥርጊያ መንገድ አለ፡፡ የባንክ አገልግሎት አስመልክቶ በቦንጋ ከተማ አራት ባንኮች የሚገኙ ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቦንጋ ከተማ በተጨማሪ በሦስት ወረዳዎች ቅርንጫፎች አሉት፡፡ የስልክና የመብራት አገልግሎትም በዞኑ ያለ ሲሆን የውሃ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ችግር መኖሩን በቆይታችን አስተውለናል፡፡

 

በዞኑ ባህና ቱሪዝም ቢሮ እና በናቡ የተዘጋጁት የቱሪስት መምሪያ መፅሀፍት በዞኑ እንደ ኮፊ ላንድ፣ ማኪራ፣ የካፋ ልማት ማህበር እንግዳ ማቆያ ለቱሪስቶች አመቺ ሆቴሎችና መቆያዎች መሆናቸውን ያሳያሉ፡፡ በካፋ ቆይታችን እንዚህን ሆቴሎች እና እንግዳ ማረፊያ የተመለከትናቸው ሲሆን ከሞላ ጎደል ጥሩ ናቸው፡፡ ሆኖም በአጠቃላይ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር ያለ መሆኑን ማስተዋል ችለናል፡፡ በተለየም የመስተንግዶ ችግርን በሰፊው አስተውለናል፡፡ 

Figure 13የእንግዳ ማረፊያ(guest house)

2.8.የማህረሰብ ተጠቃሚነት

ታው ዓለም አቀፍ ጥብቅ ቦታ ሆኖ ከመመዝገቡ ጋር ተያይዞ ህጋዊ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ በዚህም ጥበቃ ማህበረሰቡ በተዘዋዋሪ መልኩም ቢሆን ከጥበቃው ይጠቀማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሚደራጁ የተለያዩ ማህበራት በመታቀፍ ስራዎችን መስራች ችሏል፡፡ እንዲሁም የማርና ቡና አምራቾች ምርቶቻቸውን ለመሸጥ ጥብቅ ቦታው ብራንድ ሆኗቸዋል፡፡

 

ሆኖም ግን ቦታውን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ክፍያ የሚፈፅሙበት አሰራር ባለመኖሩና በዞኑ የሚቆዩበት አግባብ ተፈጥሮ ገንዘብ የሚገኝበት መንገድ ካለመመቻቸቱ አኳያ ህብረተሰቡ ማግኘት ያለበትን ጥቅም እያገኘ አይደለም፡፡

 3.ማጠቃለያ

 ከዳሰሳ ጥናቱ ከተገኘዉ መረጃ በመነሳት በከፋ ማህበረሰብ ዉስጥ የባዮስፌር ጥብቅ ቦታዉን ዘላቂ ለማድረግ የሚያስችል ሰፊ የሆነ የሀገር በቀል ዕውቀት ሃብቶች በከፍቾ ብሄረሰብ ዉስጥ እንደሚገኙ ተረጋግጧል፡፡ ከእነዚህ ዉስጥ የከፋ ታቶ ስርኣት ወይም ባህላዊ አስተዳደር፣ኮቦ የደን ጥበቃና አጠቃቀም ስርዓት፣የዴጆ ጎዶ አምልኮአዊ ስርዓት፣የናሎ የፍትህ እና የግጭት አፈታት ስርዓቱ ይገኝበታል፡፡ በእነዚህ ስርዓቶች አማካኝነት የብዝሃ ህይወቱና ደኑ ለትዉልድ ተጠብቆ እንዲቆይ ያደረገዉ አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነዉ፡፡ ይህም በመሆኑ እነዚህን የማህበረሰቡን ባህላዊ ሃብቶች አጥንቶ፣መዝግቦና አደራጅቶ ማዥና መቆየት ተገቢና ለባዮስፌሩ ዘላቂነት ጠቀሚታ ያለዉ መሆኑን የጥናት ቡድኑ ያምናል፡፡የከፍቾ ማህበረሰብ ተፈጥሮ ጥበቃ እና አጠቃቀሙ ከባህላዊ ዕሴቱ ጋር የተጣጣመ በመሆኑ ለሀገር በቀል ዕዉቀት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡ ስለሆነም በቀጣይ ሕን ዘርፍ አጠናክሮ ለባዮስፌሩ ጥበቃና ልማት አስተዋፅኦ ልደርግ በሚችል ዝርዝር ጥናት ተመዝግቦ ሊያዝ ይገባል፡፡

የከፋ ባዮስፌር ጥብቅ ቦታዉን በተመለከተ ሁሉም በጥናቱ የተሳተፉ መረጀ ሰጭዎች እንደገለጹት ቦታዉ በተባበሩት መንግስታት፤ትምህርት፤ሳይንስና ባህል ድርጀት (ዩኔስኮ) ባዮስፊር ጥብቅ ቦታ ሆኖ 2010 ላይ  ከመመዘገቡ በፊት ለረጀም ዓመት በማህበረሰቡ ውስጥ ትኩረት አግኝቶ ፤ማህበረሰቡም በደኑ ሀብት ላይ ተደግፎ መቆየቱ ተረጋግጧል፡፡ ከዳሰሳ ጥናቱ መረዳት እንደተቻለዉ ደኑ ለረጀም ዓመታት የቆየበት የራሱ የሆነ ዘዴና ዕውቀት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ እንደሆነ ተመልክቷል ፡፡ ስለዚህም የባዮስፌር ጥብቅ ቦታዎች ልማትና ሀገር በቀል ዕዉቀቱ ተመጋግበዉ የሚሄዱ ስለሆነ የአካባቢዉ ማህበረሰብ ለዓለም የአየር ንብረት ለዉጥና መዛባት መፍትሄ የሚሆኑ የብዝሃ ሕወትና የተፈጥሮ ደን ጥበቃ ላይ አስተዋጽኦ ማድረጉ ግልጽ ነዉ፡፡

የካፋ ጥብቅ ቦታ ለአለማችን ከፍተኛ ችግር የሆነውን የአየር መለወጥና ሙቀት መጨመር ለመቆጣጠርና ለማረጋገት ከፍተኛ ሚና እየተጨወተ መሆኑን የሚታወቅ ነው፡፡ይህ ጥብቅ ቦታ በሥን ፍጥረቱም ብሆን እጀግ በጣም ብዙ (ከ700 ሺ በላይ የዛፍ ዝርያዎች ) በዉስጡ የያዘ ስለሆነ ለመዳኒትነት ከመዋሉም ሌላ የመጥፋት አደጋ ላይ ለሆኑ ዝርያዎች ጥበቃ ከፍተኛ አስተወጾኦ አለው፡፡ ይህንን ከፍተኛ እምቅ ሀብት ለዘመናት ያቆው ካፍቾ ማህበረሰብ ሀገር በቀል ዕውቀት ነው፡፡ ህብረተሰቡ የደኑ አለቃ፣ ጠባቂና ተንከባካቢ ሆኖ ለትዉልድ አሸጋግሯል፡፡

የሀገር በቀል ዕውቀቱ እንደ ማንኛው ሀብት ጥበቃ ካለተደረገለት የመጥፋትና የመረሳት እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ስለሆነም በጣም ዝርዝር የሆነ ጥናትና ምርምር ተደርጎ ሊመዘገብ ይገባል፡፡ ከጥናቱ መረዳት እንደሚቻለዉ የከፍቾ ብሄረሰብ ሀገር በቀል ዕዉቀቱ ከትዉልድ ወደ    ትዉልድ እተሸጋገረ ደኑን መጠበቅ እንደቻሉ መረዳት ይቻላል፡፡ 

በሌላ በኩል ጥናቱ የከፍቾን ብሄረሰብ ሀገር በቀል ዕዉቀት ከትዉፊታዊ ትዉን ጥበባት አንጻር ለመዳሰስ ሞክሯል፡፡ ትዉፊት በባህሪው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ጥንት የነበረው ስርዓት እየተሸራረፈና ትክክለኛ ቀለሙን እየለቀቀ ምናልባትም ከእነአካቴው ሊጠፋም የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ለአንድ ሀገር የማንነትን ደብዛ እንደማጣት ይቆጠራል፡፡በመሆኑም እንደነዚህ ያሉ ጥናትና ምርምሮች ትውፊቱን ከመጥፋትና ከመረሳት የሚታደጉ መደራደርያ የሌላቸው አማራጮች በመሆናቸው ሊደገፉና ሊበረታቱ ይገባል፡፡   በከፋ ብሄረሰብ ዘንድ እጅግ በጣም ያልተነኩ በርካታ የኪነ-ጥበብ ሀሳቦች የሚፈልቁባቸው ባህላዊ ክንዋኔዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ባህላዊ እሴቶች መንግስት አጽህኖት  ሰጥቶበት ከአዳዲስና መጤ ባህሎች መበከል ሊታደገው ይገባል፡፡ ኪነ-ጥበብ የአንድ ህዝብ ማንነት ፣ ታሪክ ፣ የስልጣኔ መነሻ ፣ አብሮ የመኖርን ባህል፣ የሀገርን የእድገት ደረጃ ወዘተ. የማሳየት ከፍተኛ ሀይል አለው፡፡ በተመሳሳይ  መልኩ በከፋ ብሄረሰብ ዘንድ የተፈጥሮ ደንን የሚጠብቁበት ሀይማኖታዊ ስርዓት፣ ስነ-ቃሎች፣ ተረትና ምሳሌዎች፣ አፈ-ታሪኮች፣ ዘፈኖች፣ ህግና ስርአቶች አሉ፡፡  ስለሆነም የሚመለከተው አካል እንዲህ አይነቱን ጥበብ (ጠንካራ ባህላዊ የዳኝነት ስርአት ፣ የአስተዳደር ስርአት ፣ የባህላዊ እምነት የአመራር ስልት እና የደን መጠበቂያ ስልቶችን) ማድነቅና ማበረታታት እዲሁም ኪነ-ጥበብን በመጠቀም እዉቅና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡                

የካፋ ብዝሃ ህይወት ዓለም አቀፍ ጥብቅ ቦታ ትልቅ የኢኮ ቱሪዝም አቅም ያለው ሲሆን በዞኑ የባህና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም በናቡ ፕሮጀክት የተለዩ የተለያዩ መዳረሻዎች መረጃ እና በአካል የተጎበኙ መዳረሻዎች አስመልክቶ የሚከተሉት አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡  

 

በዚህ ዳሰሳ ጥናት የብሔራዊ ቡና ሙዚየም ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልገው ማየት ተችሏል፡፡የሙዚየሙ አደረጃጀትን እንዲሁም እስካሁን ስራ ያልጀመረበት ምክንያትና መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች አስመልክቶ ሰፋ ያለ ጥናት ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ዳሰሳ ጥናት እንደተመለከትነው የብሔራዊ ቡና ሙዚየም ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ እስካሁንም ስራ አለመጀመሩ ከሙዚየሙ ጋር ተያይዞ ሊሰሩ የሚችሉ ስራዎችንም ጭምር ያዘገየ እንደሆነ ይህ ዳሰሳ ጥናት አመላክቷል፡፡ በመሆኑም በዚህ ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለመጠቆም የዋናውን ጥናት አስፈላጊነት ያመላክታል፡፡

በዞኑ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም በናቡ ፕሮጀክት የቱሪስት መምሪያ መፅሀፍ ላይ የተጠቀሱ ነገር ግን በዚህ ዳሰሳ ጥናት ላይ ያልታዩ መዳረሻዎችን ለመጎብኘት እና ያለቸውን የቱሪዝም አቅም እንዲሁም ያሉበት ነባራዊ ሁኔታን ለመመልከት እንዲሁም ለማጥናት ዋናው ጥናት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

 4.ተግዳሮቶች

 • የሕዝብ ቁጥርና የእርሻ በታ ፍላጎት መጨመር
 • በአንዳንድ የማሀበረሰቡ ክፍሎች ለሀገር በቀል እውቀት ያላቸው ትኩረት ማነሰ
 • የአዳዲስ እምነቶች መስፋፋት (expansion of protestant Christianity )
 • ለዝርዝር መረጃ የጊዜ ዕጥረት አጋጥሟል፡፡
 • መረጃ ሰጪ የሆኑ የአስተዳደር አካላት በተለያዩ ስብሰባ ምክንያት ያለመገኘት
 • የጎብኚዎች መምሪያ መጽሀፍ ማዘጋጀት፣ እንዲሁም ስለቱሪዝም ግንዛቤን ለመፍጠር የዓለም የቱሪዝም  ቀንን በገበሬ መንደር ማክበር እና ሌሎችም የዞኑ ባህልና ቱሪዝም እና የመንግስት ግንኙነት ጽ/ቤት ስካሁን ከሰራቸው ስራዎች መካከል ይገኝበታል፡፡ ናቡ ፕሮጀክትም እስካሁን የተለያዩ ማህበራትን፤ የአስጎብኚዎች ማህበር፣ የፈረስ ተንከባካቢዎች እና ሌሎችንም በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ የማስተዋወቅ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡

 

 • የብዝሃ ህይወጥ ጥብቅ ቦታውን ለቱሪስት መዳረሻነት ከማስተዋወቅ እና ጥቅም ላይ ከማዋል አንፃር እስካሁን የነበሩ ተግዳሮቶች ምን ምን እንደሆኑ ለባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ለናቡ ፕሮጀክት፣ እንዲሁም ለአስጎብኚ ማህበሩ ጠይቀን ነበር፡፡ በዚህም መሰረት እስካሁን ያጋጠሙ ተግዳሮቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

 

 • እያንዳንዱ ጎብኚ ለሚጎበኛቸው እያንዳንዱ መዳረሻዎች የፍቃድ ደብዳቤ መያዝ አለበት የሚል አሰራር መኖሩ፡፡ ቱሪስቶች ከሚቆዩባቸው ጊዜ አንፃር በአጭር ጊዜ ደብዳቤውን ማግኘት ከባድ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ደብዳቤ ባለመያዙ ቦታው ላይ ደርሰው ሳይጎበኙ የተመለሱ ቱሪስቶች አሉ፡፡
 • የብሔራዊ ቡና ሙዚየሙ ስራ አለመጀመር፣
 • በአካባቢው ያለው የቱሪዝም ግንዛቤና መረዳት የዳበረ አለመሆን፣
 • በቂ የሆቴሎች፣ የመንገድ እና የውሃ አገልግሎት አለመኖር
 • ብዙዎቹ መዳረሻዎች ላይ አስፈላጊ አገልግሎት መስጫዎች አለመመቻቸት፣
 • ከማህበረሰቡ ባህላዊ እምነት ጋር ተያይዞ መገባት የሌለበት ቦታዎች፣ እንዲሁም መደረግ ያለባቸውና የሌለባቸው ተግባራት ላይ የጠራ ግንዛቤ በሁሉ ዘንድ አለመኖሩ፣
 • የዞኑ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት እስካሁን አለመቋቋሙ እና
 • የተለያዩ ሀገር አቀፍ አስጎብኚ ድርጅቶች ጥብቅ ቦታውን እንደ ቱሪስት መዳረሻ አለማወቃቸው ናቸው

 

 

 

5.ቀጣይ አቅጣጫዎች

 • ለከፋ የባዩስፌር ጥብቅ ቦታ ዘላቂ ልማት የሀገር በቀል ዕዉቀቱን መዝግቦ መያዝና መጠቀም ለተፈጥሮ ጥበቃዉ ከፍተኛ ተቀሜታ ያለዉ በመሆኑ ቀጣይ ዝርዝር ጥናት ተደርጎ ተመዝግቦ ሊቀመጥ ይገባል፡፡
 • የዞኑ፤የክልሉና የሚንስትር መስራያ ቤቶቹ ተቀናጅተዉ  ሚናቸዉን በተገቢዉ ሁኔታ መወጣት
 • የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት በተሟላ መልኩ ማረጋገጥና ለሀገር በቀል እወቀት ተገቢውን ትኩረት መስጠት
 • አዳዲስ እምነቶችና ተከታዮች በደኑ ላይ ያላቸውን አመለካከት የሚያስቀይር፤ቀጣይነት ያለውና ትርጉም ባለዉ መልኩ ክትትልና የማስተማር ሥራ መሰራት አለበት
 • የከፋ ብሔራዊ የቡና ሙዚየም የባህል ቅርስ ማሰተዋወቂያ ሙዚየም በመሆኑ ስራዉን በአገባቡ ማከናወን እንዲችል ድጋፍና ሚኒስቴር መስራያ ቤቱ በባለቤትነት ሊያስተዳደረዉ ይገባል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

6.ዋቢ መጻህፍት

 1. የኢትዮጵያ ባህል ፖሊሲ 2005
 2. ወንድሙ ማሞ ፡ ዩኒክ ካፋ(ያልታተመ) ካፋ ዞን ባህል፤ቱረዘምና የመንግስት ኮምንክሽን ብሮ
 3. Bekele Woldemariam፣ 2010 The History of the Kingdom Of Kaffa.The birth place of Coffee 1390-1935
 4. Adam Asamoah  Kwame

      Some Ghanaian Tradition Practice Of Forest Management and                  Biodiversity Conservation.Forstery research Institute.Ghana.

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

7.የጥናት ቡድኑ አባላት

1.አቶ ደስታ ሎሬንሶ --የአንትሮፖሎጂ ከፍተኛ ባለሙያ

2.አቶ ታሪኩ ፀጋዬ--- የአንትሮፖሎጂ ባለሙያ

3.አቶ ሚሊዮን ታደገ----የቱሪዝም ባለሙያ

4.አቶ ፍቃዱ አንሙት --የተፈጥሮ መሰህብ ሀብቶች ባለሙያ

5.አቶ ነስረዲን ሻፊ -----ተመራማሪ ኢንተርን ሽፕ

6.አቶ አውግቸው ሰሙ -----የተፈጥሮ መሰህብ ሀብቶች ባለሙያ

7.አቶ ተስፋ ነገሰ----የስነ-ጥበብ ባለሙያ

Figure 14የጥናት ቡድኑ


Tourism Studies and research Tourism Studies and research