በሐረሪ ብሔረሰብ ማህበራዊ ተቋማት፤ የአፎቻ ማህበራዊ አደረጃጀት እና ፋይዳው

ሐረሪ ብሔረሰብ ማህበራዊ ተቋማት፤ የአፎቻ ማህበራዊ አደረጃጀት እና ፋይዳው

በወ/ት አሲያ አማን

ዋና ጭብጥ

ከ1000 አመታት በላይ እድሜ ባሰቆጠረችው ሐረር ከተማ በአሁኑ ወቅት ለረጅም አመታት ሲወርድ ሲዋረድ የመጡ ባህላዊ፣ማህበራዊ አደረጃጀቶች (አፎቻ፣ ባሐ፣ ጌል፣ ጀመአ ወዘተ) አደረጃጀቶች እንደሉ ይታወቃል፡፡ በተለይም የሴቶችና የወንዶች አፎቻ (እድሮች) በሐረር ህብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ይታመናል፡፡ እንደሁም የፖለቲካ አደረጃጀት መሰረት እነዚህ አፎቻዎች መሆናቸው ይናገራል፡፡ ሆኖም ግን ይህ በጥናት ተረጋግጦ አይታወቅም፡፡  ሰለዚህ የዚህ ጥናት ዋና አላማ የሐረር ብሔረሰብ ባሕላዊና ማህበራዊ አደረጃጀትና ተቆማት ተጠብቆ ለተተኪ ትውልድ እንድተላለፍ ማድረግ አፎቻ በአሁኑ ወቅት ያሉበትን ሁኔታ በመገምገም አሁን ያለው ትውልድ ሰለ አፎቻ ግንዛቤ እንድኖረው ለማድረግ የታሰበ ነው፡፡  ይህን ጥናት ከግብ ለማድረስ ሶሰቱን የመረጃ ማሰብሰቢያ ዘደዎች ማለትም ምልክታ፣ ድርሳነ ክለሳ እና መጠይቅ ተጠቅመናል፡፡ በውጤቱም እነዚህ አፎቻዎች፣ ከፍተኛ ማህበረዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቅሜታ እንዳላቸው ታውቀዋል፡፡ ሰለዚህ በቀጠይነት አሁን ያለው ትውልድ ይህንን አውቆ መደረጃጅቱ ከትወልድ ትውልድ መተላለፍ ይኖርባቸዋል፡፡

ዋና ቃላት፡-  የሐረሪ ብሄረሰብ የማህበራዊ ተቋማት ውስጥ አንዱ የሆነው ‹‹አፎቻ ማህበራዊ አደራጃጅት ››

 

 

 

 

 

 

  •  

         የቅድመ ስልጣኔ አሻራ፣ የታሪክ መዘክር አንድ ሺህ ዘመን ያስቆጠረ የቋንቋ የባህልና ታሪክ መገኛ የሆነችው ሐረር በ10ኛው ክፍለ ዘመን እንደተመሰረተች ይገመታል፡፡ ሐረሪ የሚለው ስያሜ ረጅም ታሪክ ያለውና በምእራባዊያን እና በአረብ ጸሀፊዎች ዘንድ ብሄረሰቡ በዋነኝነት የሚታወቅበትና በታሪካዊ ሰነድም ጭምር የተመዘገበበት ስያሜ ነው፡፡ሐረሪ የሚለው አባባል ወይም አጠራር በብሄረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የክልሉና የብሄረሰቡም መጠሪያ ሆኖ የሚያገለግል ስያሜ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ስያሜ ታሪካዊና በታሪክ ሰነዶች መመዝገቡ እንደ  ተጠበቀ ሆኖ ብሄረሰቡ ራሱን በራሱ የሚጠራው ‹‹ጌይ ኡሱዕ›› የከተማ ሰው ወይም ከተሜ በማለት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ቋንቋውን ‹‹ጌይ ሲናን›› የከተማ ቋንቋ እንዲሁም ባህሉን ‹‹ጌይ አዳ›› የከተማ ባህል ወይም የከተማ የአኗኗር ዘዴ ማለትን ይመርጣል፡፡

     ጥንታዊነቷን የሚንፀባርቁ በርካታ ቋሚ ፣ ተንቀሳቃሽና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ስትሆን ከነዚህም የጁገል ግንብና አምስቱ በሮች ፣ በስነ-ህንፃ ያሸበረቁ ባህላዊ ቤቶች፣ ጥንታዊ መስጂዶችንና አድባራቶች፣ ከ500 ዓመት ዕድሜ በላይ ያስቆጠሩ ጥንታዊ ቤቶች፣ ማራኪና ውብ የዕደ-ጥበብ ውጤቶች፣ እንዲሁም የሐረር ብሔረሰብ የአኗኗር ባህል እና ወግ ሐረር ከብዙ በጥቂቱ ያሏት ሀብቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም ሐረር ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉ በውስጡዋ ለብዙ ዘመናት አምቃ ይዛ ቅርሶችዋ የሐረር ብቻ ሳይሆኑ የአለምቅርስም ጭምር ሆነዋል::

     ሐረር እዚህ ደረጃ ላይ ብትገኝም እነኚህ የአለም ቅርሶች እና ማንኛውም ቅርሶች በአግባቡ ካልጠበቅነውና ካልተንከባከብነው ለተለያዩ አደጋዎች መጋለጡ አይቀሬ መሆኑ የማይታበል እውነታ ነው::

      ‹‹ለጌይ ኡሱዕነት›› /አይደንቲቲ/ መለያና ማህበራዊ አደረጃጀት መሰረት የሆኑ አራት ማህበራዊ ተቋማት አሉ እነሱም1. ‹‹አፎቻ›› /ማህበራዊ መረዳጃ ማህበር/ 2. አህሊ (የስጋ ወይም ቤተሰባዊ ዝምድና)፣ 3. ጀመአ፣ እና 4. ሙጋድ ወይም መሪኛች(የጓደኝነት ቡድን) ናቸው፡፡እነዚህ አራት ህብረቶች ከእያንዳንዱ የሀረሪ ተወላጅ ዘንድ ይደርሳሉ፡፡ የከተማዋን ህብረተሰብ በአንድ ጥላ ስር ያሰባስባሉ፡፡ በመላው አለም የሚኖሩ ሀረሪዎችንም ለአንድ አላማ ያሰልፋሉ፡፡ የህዝቡ ማህበራዊ ደህንነት ያለበትንም ሁኔታ ለማስረዳት የመጀመሪያ ደረጃ የመረጃ ምንጮች ሆነው የሚያገለግሉትም እነሱ ናቸው፡፡ ጌይ ኡሱአች /ሐረሪዎች/ ለገጠማቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ ለማስገኘት ሲሹም ፈጣን የመሰባሰቢያ መንገዶች ሆነው የሚያገለግሉም እነዚህ አራት ህብረቶች ናቸው፡፡/አፈንዲ ሙተቂ ገጽ 51/ እነዚህ አራት ማህበራዊ ተቋማት የሐረሪ ብሄረሰብን አንዱን ግለሰብ ከሌላው ግለሰብ እንዲሁም አንዱን ቡድን ከሌላው ቡድን ጋር የሚያገናኙና የሚያስተሳስሩ ማህበራዊ ተቋማት ናቸው፡፡

      ከነዚህ ማህበራዊ ተቋማት ውስጥ አንዱና ዋነኛው የሆነው አፎቻ ከጥንት ጀምሮ ማህበረሰቡን ከተለያየ አካባቢ እንዲሁም ሀብታም ደሃ ሳይለይ አንድ ላይ በማሰባሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ተቋም ነው፡፡ አፎቻ የሚያስተባብረው የሀዘንና የሰርግ ስነስርአቶችን ብቻ ሳይሆን እንደ ኢንፎርማንቶች አገላለጽ በሁሉም የማህበረሰቡ ጉዳዮች ላይ የአፎቻ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ሐርሺ አፎቻ (የእርሻ አፎቻ) ላይ ሁሉም የአፎቻ አባላት አንድ ላይ ተሰባስበው በእያንዳንዱ የአፎቻው አባል እርሻ ላይ በጋራ የሚሰሩበት ሁኔታ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

የሐረሪዎች ባህላዊ ህይወት /ጌይ ዓዳ/

       የሐረሪዎች ባህላዊ ህይወት በሐረሪ ቋንቋ ጌይ ዓዳ ተብሎ ይጠራል ፡፡ ጌይ ዓዳ የህይወት መገለጫ እንደመሆኑ መሰረቱ ኢስላማዊ ባህል ሆኖ ሐረሪዎች በግል፣ በቤተሰብ፣ በጎረቤት፣ በሰፈር እና በአገር እንዲሁም ከዚህም ባሻገር አለማቀፋዊም የሆነውን የሚያስተናግዱበትና በውስጡም ሆነው ከሌሎችም ጋር ያላቸውንና የሚኖራቸውን የእርስ በርስ ግንኙነት - - በኑሮም ውስጥ የሚያከናውኑት ጥበብንና ፈጠራን - - የስራ ባህላቸውና ማህበራዊ ህይወታቸውን ሁሉ አጠቃሎ ፡ የሚያከናውኑትን አካቶ - - ጌይ ዓዳ የሐረሪዎች / የሐረሪነት (ጌይ ኡሱእነት) ባህላዊ መገለጫ ነው፡፡

      የሐረሪዎች መናገሻ ሐረር ጌይ በመካከለኛው የኢትዮጵያ ደጋማ ክፍልና በዘይላዕ ወደብ መሐከል በተዘረጋው የንግድ መስመር ላይ የምትገኝ መሆኗና የከተማዋ አመራር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሐረርን የምስራቅ አፍሪካ ታዋቂ የንግድ ማዕከል አድርጓታል ፡፡ በሌላ በኩል ኢስላምን በቀዳሚነት ተቀብላ በማስተናገዷ የሐረሪዎች የስልጣኔ ጎዳና አዲስ የጥንካሬና ሐይል ምንጭ እንዲሆንላቸው አስችሏል፡፡ ጌይ ዓዳ የነዚህና ሌሎችም ድምር ውጤት ነው፡፡

በጥንት ታሪክ እንደሚታወቀው ሐረሪዎች በየወቅቱ ከነበረው ስልጣኔ ጋር በእኩል መጓዝ መቻላቸው የሚያስረዱ የፅሁፍ ማስረጃዎች ያረጋገጡት ሐቅ ነው ፡፡ /አህመድ ዘካሪያ ፡ የሐረሪ አመፅ ፡ ገፅ - 13 › 1992 ሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ /

2. አፎቻ

 የአፎቻ አመጣጥ ፡-

አፎቻ የሚለው ቃል ታሪካዊ አመጣጥ ‹‹ ጋር አፎች›› ከሚለው ቃል የመጣና ትርጉሙም ጋር አፎች ማለት አንድ አካባቢ ላይ የሚኖሩ ወይም ጉርብትና ያላቸው ሰዎች ተደራጅተው የሚያቋቁሙት ባህላዊ ማህበራዊ ተቋም ነው፡፡ ቀደም ሲል የአፎቻ መሰረተ ሀሳብ ከጉርብትና ጋር የተያያዘ ጽንሰ ሀሳብ መሆኑ ተገልጽዋለ፡፡ አፎቻ መቼና እንዴት እንደ ተጀመረ የሚታወቅ ነገር የለም ምክኒያቱም ብዙው የአፎቻ ታሪክ በቃል የተነገረ ስለሆነ እና በጽሁፍ የተቀመጠ ታሪክ በብዛት አይገኝም፡፡ ቢሆንም እንደ ኢንፎርማንቶች ገለጻ አፎቻ የተጀመረው ሀረሪዎች ታሪክ መጀመሪያ ጀምሮ እንደሆነ እና አሁንም ድረስ መዝለቅ የቻለ ማህበራዊ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡

የአፎቻ አመሰራረት (መዋቅር) 

አንድ አፎቻ ሲመሰረት ወይም ሲቋቋም የተለያዩ ነገሮች/ምክኒያቶች/ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ለምሳሌ  በጉርብትና ወይም  በአካባቢ  የሚመሰረት ‹‹ጋር አፎቻ››፣ በእርሻ ቦታ መቀራረብ የሚመሰረት ‹‹ሐርሺ አፎቻ››፣ ‹‹ቶያ አፎቻ›› በሰፈር የሚመሰረት፣ ‹‹መስጂድ ቶያ አፎቻ›› መስጊድ አካባቢ የመመሰረት፣  እና ዱካን አፎቻ በንግድ ቦታ የሚመሰረቱ አፎቻዎች ናቸው፡፡ ከነዚህ የአፎቻ አይነቶች ውስጥ ‹‹ሐርሺ አፎቻ›› የእርሻ ቦታን የሚመለከት ማለትም አንድ አካባቢ ያሉ እርሻዎች ባለቤቶች በጋራ የሚመሰርቱት ሲሆን ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል የአንድ አፎቻው አባል እርሻ  ሲታረስ ሁሉም አባላት ሄደው በጋራ ሚሰሩበት  ማህበራዊ ተቋም ነው፡፡ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ሐርሺ አፎቻ የለም፣  ምክንያቱም አብዛኛው የሀረሪ ብሄረሰብ ነዋሪዎች የእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩ አይደሉም፡፡ በአሁኑ ሰአት ማህበረሰቡ አፎቻን የሚመሰርተው ወይም አባል የሚሆነው ለሁለት ትላልቅ ተግባራት ሲሆን እነሱም የሰርግ ስነ ስርአት ማስፈጸም ማድመቅ እና የሀዘን (አሙታ) ስነ ስርአት ማስፈጸም ናቸው፡፡ አፎቻ ጾታን መሰረት በማድረግ በሁለት የሚከፈል ሲሆን፡-  እነሱም ‹‹አቦቻች አፎቻ››የወንዶች አባቶች አፎቻ እና ‹‹ኢንዲቻች አፎቻ››የሴቶች እናቶች አፎቻ ናቸው፡፡

‹‹አፎቻ›› አባላት፣ የተጻፈ ወይም ሁሉም አባላት ተስማምተውበት በቃል የሚያውቁት ህግ መብት ግዴታዎችና የስነ ምግባር መመሪያዎች፣ኮሚቴዎች፣ አስተዳዳሪ እንዲሁም አጠቃላይ ስብሰባዎች አሉት፡፡ኮሚቴዎቹና አስተዳዳሪው ወርሀዊ ወይም ሳምንታዊ ስብሰባዎች አላቸው፡፡ በስብሰባዎች፣የሀዘን ስርአት እና ሰርግ ላይ መገኘት ግዴታ ነው፡፡ እነዚህ መዋቅሮችና መብትና ግዴታዎች በሴቶችም ሆነ በወንዶች አፎቻ ተመሳሳይ ናቸው፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት መዋቅሮች በተጨማሪ አፎቻ በአባላቱ መካከል የስራ ክፍፍልም አለው፣ ለምሳሌ ገንዘብ ያዥ፣ ንብረት አስተዳዳሪ፣ ሂሳብ ሰራተኛ፣ ቀብር ቁፋሮ አስተባባሪ፣‹‹አሙታ ጋር››የሀዘን ቤት ስርአት አስተባባሪ፣ እና ‹‹የፊርዛል››የስብሰባ ጥሪ አስተላላፊ የመሳሰሉት ናቸው፡፡

አፎቻን የሚመሩት በእድሜ የበሰሉ በምግባራቸው የተመሰከረላቸውና ‹‹በሸሪአ› እውቀታቸውም ደህና ደረጃ ላይ የደረሱ አባቶች/እናቶች ናቸው፡፡ በአመራር የሚቀመጠው ቡድን የሚሾመው ደግሞ በአባላቱ ተሳትፎ በሚከናወን ምርጫ ነው፡፡ ለአመራር የተቀመጠ ሰው ጥፋት እስካልተገኘበት ድረስ በቦታው ይቆያል፡፡ በማንኛውም ወቅት ከአባላቱ መተማመኛ ድጋፍ ካጣ /ድምጽ ከተነፈገ/ ግን ጥፋት ባየገኝበትም እንኳን ከሀላፊነቱ ይወርዳል፡፡/አፈንዲ ሙተቂ ሀረር ጌይ፣ ገጽ67/

አፎቻ አስፈላጊነት፡-

አፎቻ በሀረሪ ማህበረሰብ ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነ ማህበራዊ ተቋም ነው፡፡ አፎቻ በሐረሪ ብሄረሰብ ማህበራዊ ግንኙነት አንዱና መሰረታዊ ወይም ከግለሰብ አቅም በላይ የሆኑ ማህበራዊ ችግሮችን በጋራ ለመወጣትና ማህበራዊ ውህደቱን የሚያመላክት የህብረ ዋስትና ነው ማለት ይቻላል፡፡ በሀረር ያለ ዘመድ መኖር ይቻላል ያለ አፎቻ ግን መኖር አይቻልም ስለዚህ እያንዳንዱ ሐረሪ የግድ የአፎቻ አባል ነው፡፡ /ዩሱፍ መሀመድ ወበር፣ 1965/፡፡ በማህበረሰቡ አንድ ግለሰብ ትዳር ከመሰረተ በኋላ አፎቻ አባል መሆን አለበት ይህ ማለት አንድ ሰው ትዳር ከመሰረተ በኋላ ከወላጆቹ ተለይቶ የራሱን ህይወት መኖር የሚጀምር ሲሆን የወላጆቹን አፎቻ ለሱ አገልግሎት ስለማይሰጥ እራሱን ችሎ የአፎቻ አባል ይሆናል፡፡

‹‹ጌይ ኡሱእ›› የአፎቻ አባል የሚሆነው /የምትሆነው/ ካገባ በኋላ ነው፡፡ በመሆኑም የአንድ ቤት አባ ወራ /አቦች/ በትዳር ዓለም ያሉ ጌይ ኡሱአችን የሚያቅፈው አቦቻች አፎቻ የወንዶች አፎቻ አባል ይሆናል፡፡ እማ ወራዋም በኢንዶቻች አፎቻ የሴቶች አፎቻ ትሳተፋለች፡፡

የአፎቻ አይነቶች፡-

አፎቻ በሀረሪ ሁለት አይነት ነው፡፡ አንዱ የወንዶች ወይም ‹‹አቦች››አፎቻ ሲሆን ሁለተኛው የሴቶች ወይም ‹‹ኢንዶች አፎቻ›› ናቸው፡፡ ይህ አፎቻን በጾታ የመከፋፈል ሁኔታ እምነትን መሰረት ያደረገ ነው፡ ይህም የሐረሪ ብሄረሰብ ሙሉ በሙሉ ሙስሊም ስለሆነ በሙስሊም ማህበረሰብ ውስጥ ሴቶችና ወንዶች በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ መቀላቀል የማይፈቀድ ስለሆነ ነው፡፡  ለምሳሌ ሁለቱም ሴቶችና ወንዶች በቀብር ስነስርአት ላይ በጋራ አይሳተፉም፡፡ በተመሳሳይ በሰርግ ስነስርአት ላይም ሴቶችና ወንዶች በጋራ ወይም ተቀላቅለው አይሳተፉም፡እንዲሁም ሴቶችና ወንዶች አፎቻዎች በለት ተለት የማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የየራሳቸው የብቻ ሚና አላቸው፡፡ ምክኒያቱም የሴቶችም ሆነ ወንዶች አፎቻ የሚሰሩት ስራ እርስ በርስ የሚደጋገፍ ቢሆንም እስላማዊ ባህሉን በጠበቀ መልኩ ሁለቱም አፎቻዎች የየራሳቸው ድርሻና ሀላፊነት አለባቸው፡፡

አቦች አፎቻ (የወንዶች አፎቻ)፡-

በሐረሪ ማህበረሰብ አንድ ወንድ ትዳር ሲመሰርት የአፎቻ አባል መሆን አለበት፡፡ የአፎቻ አባልነት በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም የቤተሰብ ጥሪ ወይም ግብዣም አለበት በመሆኑም ወንድ የአባቱ አፎቻ አባል እንዲሆን ይጋበዛል፡፡ ይህ በአባት አፎቻ ተጋብዞ አባል የመሆን ስርአት አንድን ቤተሰብ በአፎቻ አባልነታቸው ለረጅም ዘመናት ማለትም እስከ ስድስት ትውልድ ድረስ የአንድ አፎቻ አባል ሆነው እንዲቆዩ እንደ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ በወንዶች አፎቻ ወይም ‹‹አቦች›› አፎቻ ወንድ አባላትን ብቻ የያዘ ሲሆን ይህ እንዳለ ሆኖ ባሏ የሞተባትና ተጠሪ የሌላት ሴት በባሏ ምትክ ስሟ በወንዶች አፎቻ አባላት መዝገብ ይመዘገባል፡፡ ነገር ግን የአባልነት ክፍያ ብትከፍልም የወንድ አባላት የሚሰሩትን ስራዎች መስራት የለባትም፡፡

አቦች አፎቻ (የወንዶች አፎቻ) በሀዘን ወይም ቀብር ስነ ስርአት፡-

የአፎቻ አባሉ ወይም የአባሉ የቅርብ ዘመድ መሞቱ ሲታወቅ በመጀመሪያ የአፎቻው ተላላኪ ወይም ሞትና መርዶ ነጋሪ ለአባላቱ ከቤት እቤት እየዞረ በቃል ለሚችለው ሁሉ ይነግራል፡፡ ቀጥሎም የሰሙት አባላት ላልሰሙት አባላት በተቻላቸው መንገድና ሁኔታ መልክቱን ያደርሳሉ፡፡ የወንዶች አፎቻ አባላት የሟቹን ቀብር ስነስርአት በእስልምና ደንብና ሀይማኖት ማስፈጸም ዋና ተግባራቸው ነው፡፡ በቀብር ስነስርአቱ ላይ የመጀመሪያው ወንዶች አባላት አቅሙ ያላቸው ማለት ነው የመቃብር ቁፋሮ ስራ ያከናውናሉ፡፡ መቃብር ቁፋሮው በወጣቶቹ ሲከናወን በእድሜ የገፉት አባላት ደግሞ ቤት ውስጥ የሬሳ እጥበት ስራ ያከናውናሉ እንዲሁም ሬሳውን በማጠብ ላይ ያልተሳተፉት ደግሞ ቁርአን በመቅራትና ለሟቹ ዱአ በማድረግ ይጠባበቃሉ፡፡ የመቃብር ቁፋሮው ከተጠናቀቀ በኋላ ሁሉም የአፎቻው አባላት ሴቶችን አይጨምርም ሟቹን ለመቅበር ይሄዳሉ፡፡ በመጨረሻም ከተቀበረ በኋላ ሁሉም የአፎቻው አባላት በጋራ ያሲን (ሱረቱል ያሲን) እና ተባረክ (ሱረቱል ሙልክ) ቁርአን አንቀጾች በመቅራት (በማንበብ) እንዲሁም ለሟች ዱአ በማድረግ የቀብር ስነ-ስርአቱን አጠናቀው ወደ ሀዘን ቤቱ ይመለሳሉ፡፡ በሀዘን ቤት ‹‹አሙታ ጋር›› ለሶስት ቀን ይቆያሉ፡፡ በሶስተኛው ቀን ቁርአን በመቅራትና ‹‹ኻቴን›› ማጠናቀቂያ ይቀራሉ፡፡ የማጠናቀቂያው ስነ ስርአት ላይ ሶስት የአፎቻው አባላት አነስ አነስ ያሉ አራት መአዘን ድንጋዮችን ‹‹ቀብሪ ኡን›› በመቃብር ቦታው ላይ ያቆማሉ ይህም መቃብሩ የማን እንደ ሆነ ለመለየት የሚረዳ ምልክት ነው፡፡ ይህ ስነ-ስርአት ለሁሉም የአፎቻው አባላት በተመሳሳይ ሁኔታ የሚፈጸም ስነ-ስርአት ነው፡፡ ይህም አፎቻን በማህበረሰቡ ውስጥ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ማህበራዊ ተቋም ያደርገዋል፡፡ ሌላው የአቦች አፎቻ በ‹‹አሙታ ጋር›› የሚያከናውነው ስራ ምግብ አቅርቦት ነው፡፡ በተለምዶ በሀዘን ቤት የምግብ አቅርቦቱ በፈቃደኝነት የሀዘንተኛው የቅርብ ዘመድና ጓደኛ ከየቤቱ ሰርቶ ይዞ የሚመጣ ቢሆንም ይህ ሁኔታ አስተማማኝ ስላልሆነ የወንድ አፎቻ የምግብ መስሪያ ያሟላል ምግቡን ማብሰል ግን የሴት አፎቻ ስራ ነው፡፡

አቦች አፎቻ (የወንዶች አፎቻ) በሰርግ ስነ ስርአት፡- ወንድ አቦች አፎቻ በሰርግ ስነ ስርአት ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ የሚጀምረው በሽምግልና ጊዜ ነው፡፡ አንድ ወጣት ወንድ ለማግባት ያሰባትን ሴት ለአባቱ ይነግርና አባት ደግሞ የአፎቻውን ትልልቅ ሰዎች ያማክራል፡፡ አፎቻውም ለሽምግልና የሚላኩ ሰዎች ይመረጡና ወደ ልጅቷ ቤተሰቦች ሄደው ካስፈቀዱና ‹‹ዘገን›› ጥሎሽ ላይ ከተስማሙ በኋላ የሰርጉን ቀን ቆርጠው ይመለሳሉ፡፡ የወንድ አፎቻ አባላት በሰርጉ ቤት ለሁለት ቀን (ቅዳሜና እሁድ) ይቆያሉ፡፡ ቅዳሜን የአፎቻው አባላት በሰርጉ ቤት የሚገኙት ለሰርጉ ዝግጅት የሚጠበቅባቸውን ስራ /እንደ የሰርጉ ቤት ድግስ ይለያያል/ ለመስራት ይሰባሰባሉ፣ ይህ በአፎቻው አባላት መሀከል ያለውን ቅርርብ ያጠናክራል፡፡ እሁድ ቀን ሁሉም የአፎቻው አባላት በጋራ ‹‹መውሉድ›› (የነብዩ መሀመድ /../ ውዳሴ) ያነባሉ፡፡ በሰርጉ ወቅት ቅዳሜና እሁድ ማለት ነው የቅርብ ዘመድ፣ ጓደኛ እና አፎቻ ተሰብስበው ጫት ይቅማሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ብዙ ማህበራዊ ጉዳዮችን ይወያያሉ፡፡

ኢንዶች አፎቻ (የሴቶች አፎቻ)-

በሐረሪ ማህበረሰብ ውስጥ ሴት ልጅ እንደ ወንድ ትዳር ስትመሰርት የአፎቻ አባል መሆን አለባት፡፡ የአፎቻው አባልነት በተመሳሳይ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ሴት ልጅ የአማቾቿ አፎቻ አባል እንድትሆን ትጋበዛለች፡፡ ነገር ግን ሴቶች አብዛኛውን ጊዜ ለማህበራዊ ግንኘኙነቶች ትኩረት የሚሰጡ በመሆናቸውና ከወንዶች ይልቅ የሴቶች አፎቻ ከፍተኛ ጊዜ ስለሚወስድባቸው በቅርብ ያለ አፎቻ አባል መሆንን ይመርጣሉ፡፡ የሐረሪ ሴቶች ለአፎቻቸው ከፍተኛ የሆነ ታማኝነታቸውን ሲገልጹ ‹‹ቂጤ ሺዕ በቀድ አፎቻ›› የሚል አባባል አላቸው ትርጉሙም ከሁሉ በፊት መጀመሪያ አፎቻ እንደ ማለት ነው፡፡ የሴቶች አፎቻ ‹‹ኢንዶች አፎቻ›› ከወንዶች አፎቻ በተለየ ሁኔታ በሀዘንና በሰርግ ስነ ስርአቶች ላይ በስፋት ተሳትፎ ያደርጋል፡፡

ኢንዶች አፎቻ (የሴት አፎቻ) በሀዘን ስነ ስርአት

እንደ አቦች አፎቻ ኢንዶች (የሴት) አፎቻም የሀዘኑን መልእክት ለአባላቱ የሚያደርሱበት መንገድ ተመሳሳይ ነው፡፡ መልክቱም እንደ ደረሳቸው ሁሉም የአፎቻው አባላት ‹‹ከፋራ ኢንጪ›› ይዘው ወደ ሀዘን ቤቱ ይሄዳሉ፡፡ ከፋራ ኢንጪ ‹‹ከፋራ›› (ከስንዴ የሚሰራ ቂጣ) ለመስሪያ ማገዶ ሲሆን የቀብሩ ስነ ስርአት ከተፈጸመ በኋላ የቀበሩ ሰዎች የሚበሉት ነው፡፡ ሴቶቹ ከፋራውን ጋግረው ለመቅበር ለሚሄዱት ወንዶች ይሰጣሉ፡፡ የሴት አፎቻ አባላት የእስልምና ሃይማኖት ሸሪዓ ስለሚከለክል ወደ ቀብር አይሄዱም ነገር ግን በሟቹ ቤት ወይም ዘመድ ቤት ሆነው ለቀብር አስፈላጊውን ዝግጅት ያከናውናሉ፡፡ የሟቹንም ቤተሰብ ያስተዛዘናሉ፡፡ የሴት አፎቻ ‹‹በአሙታ ጋር›› የሚያደርገው እንቅስቃሴ በጾታ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ከወንድ አፎቻ እንቅስቃሴ ይለያል፡፡ ወንዶች ወደ ቀብር በሚሄዱበት ወቅት ሴቶች በአሙታ ጋር ይቆያሉ፡፡ በመሆኑም ከቀብር ለሚመለሰው ሐዘንተኛ አስፈላጊውን ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ ኢንዶች አፎቻ በአሙታ ጋር ውስጥ ለሶስት ቀን ‹‹ሰለዋት›› ያደርጋሉ፡፡ ከዛም በሶስተኛው ቀን ጠዋት ‹‹ቀህዋ መሐለቅ›› የሚባለውን ስነ ስርአት ያከናውናሉ፡፡ በዚህ ስነ ስርአት የአፎቻው አባላት ገንዘብ ያሰባስባሉ፡፡ በመቀጠል በዛው በሶስተኛው ቀን ‹‹ቁርአን ገበታበሴት አፎቻ የሚደረግ የምግብ ማብላት ወይም ሰደቃ ሲሆን ይህም የሀዘኑን ማጠናቀቂያ ስነ ስርአት ነው፡፡ ከዚያም ሁሉም የአፎቻው አባላት ወደ የቤታቸው ይመለሱና በዘጠነኛው ቀን ደግሞ ‹‹አህሊ ፋታሕ›› ተሰባስበው ‹‹ሹሁም›› ከተለያዩ ጥራጥሬዎች የሚሰራ ንፍሮ አዘጋጅተው ለሟች ዱአ የሚያደርጉበት ስነ ስርአት ነው፡፡

ሟቹ የአፎቻቸው አባል ባል ከሆነ ደግሞ ባሏ የሞተባት ሴት ለአራት ወር ማግባትም ሆነ ምንም አይነት ጌጥ ማድረግ አትችልም፡፡ ከዚያም በአራተኛው ወር ከአፎቻዋ ጋር ሆና ‹‹አሳይ ሞረድ›› ስነ ስርአት ይደረጋል ይህም ከዚህ በኋላ ሀዘንተኛዋ ለማግባት ነጻ መሆኗን ያመለክታል፡፡ የሴት አፎቻ ጥንካሬና ድክመት መለኪያው ‹‹በአሙታ ጋር›› እና በሰርግ ድግስ ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ ነው፡፡

ኢንዶች አፎቻ (የሴት አፎቻ) በሰርግ ስነ ስርአት

የአፎቻ ዋነኛ ተግባር ውስጥ አንዱ በሰርግ የሚያደርገው ተሳትፎ ነው፡፡ ይኸውም የሰርግ ጉዳይ በአብዛኛው የሚመለከተው የሴቶች አፎቻን ነው፡፡ የወንድ አፎቻ በሰርግ ስነ-ስርአት ላይ ተሳትፎ ቢኖረውም የሴት አፎቻ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ የሀረሪ ሰርግ በእቅድ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ጋብቻ የሚፈጸመው በዓመቱ ስምንተኛ ወር ‹‹ሱጢ ዋህሪ›› አረፋና መውሉድ ወር ላይ ነው፡፡ የአፎቻ እንቅስቃሴ ጎልቶ የሚታየው በዚህ ጊዜ ነው፡፡

የሴት አፎቻ አባላት ካለባቸው ድርብ ሃላፊነት /ከጾታና ከሙያ/ አንጻር ከፍተኛው የሠርጉ አንቀሳቃሽ ሀይል ናቸው፡፡ በመሆኑም ለሰርጉ ከፍተኛ ድምቀት የሚሰጡት የሴት አፎቻ አባላት ናቸው፡፡ የሴት አፎቻ የሰርግ ቤት ማድ ቤትን በመቆጣጠር የሐረሪ ባህላዊ ምግብና መጠጥ ያዘጋጃሉ፡፡ እንዲሁም ሙሽሪትን የማስዋብ ስራ ይሰራሉ ይህን ዝግጅት በሚያከናውኑበት ወቅትም የሀረሪ ባህላዊ ዘፈኖችን እየዘፈኑ ይጨፍራሉ፣ የሰርገኞችን ቤተሰብም ይመርቃሉ፡፡ የሰርጉ ስነ ስርአት የሚጀምረው ቅዳሜ ሲሆን በሴቶች አፎቻ የሚከናወኑት ባህላዊ ጭፈራዎች ውስጥ ቅዳሜ ማታ የሚያደርጉት ‹‹አንቀር ማህጠብ›› አንዱ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የተለያዩ ባህላዊ ዘፈኖች እየዘፈኑ ይጨፍራሉ፡፡ እሁድ ዋናው ሰርግ ይደረግና ሙሽሮች ወደ ተዘጋጀላቸው አሩዝ ጋር ይሄዳሉ፡፡ ከዚያም ማክሰኞ ለሚደረገው ‹‹ኢናይ ገበታ›› የአፎቻ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በመጨረሻም ሀሙስ ‹‹አሩዝ መውጣእ›› የጫጉላ ጊዜ መጠናቀቁን የሚገልጽ ስነ ስርአት ይደረግና የሰርጉ /በለቹ/ ስነ-ስርአት ይጠናቀቃል፡፡

አፎቻና የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች

አፎቻ በፍትህ ስርአትና በባህላዊ ግጭት አፈታት

አፎቻ ቋሚ ከሆነው ስብሰባዎቹ በተጨማሪ በሁኔታዎች አስገዳጅነትና በአባላቱ ጥያቄ መሰረት ወቅታዊ ስብሰባዎች ‹‹አፎቻ መሳመት›› ይካሄዳሉ፡፡ በዚህም መሰረት በአፎቻ አባላት መካከል ለተከሰተ ችግር ወይም አለመግባባት መፍትሄ ለመስጠት ‹‹የአፎቻ መሳመት›› /ስብሰባ/ ይጠራል፡፡ እንዲሁም የአፎቻ አባላትን የግል ችግሮች ለመፍታት ወይም አስቸኳይ እለታዊ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር በአመቺ ጊዜና ቦታ ስብሰባ ይካሄዳል፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ በግለሰቦች እና አንዳንዴም በሰፈር፣ በቤተሰብ መሀከል የተከሰተ ግጭትን በባህላዊ ግጭት አፈታትና በአፎቻው ደንብ መሰረት ይዳኛል፡፡ እንዲሁም በማህበረሰቡ ውስጥ የተፈጠረ ሁከትን የማረጋጋት ተግባራት ይሰራል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ከአፎቻ በላይ የሆነ ችግር ወይም ወንጀል ሲያጋጥም አፎቻው ጉዳዩን ለአካባቢው የህግ አካላት ያቀርባል፡፡

አፎቻ የተደነገገ ህግ ወይም በጽሁፍ የሰፈረ መተዳደሪያ ደንብ የለውም፡፡ ነገር ግን አባላቱ ሁሉ በቃል የሚያውቁትና ተገዢ የሆኑለት ባህላዊ መተዳደሪያ ደንብ አለ፡፡ ይህን ደንብ የጣሰ ወይም የተላለፈ ግለሰብ ይቀጣል፡፡ ቅጣቱም እንደ ተጣሰው ደንብ ይዘትና አይነት ይለያያል ይኸውም በገንዘብ በአይነት ወይም በሞራል ቅጣት ማለት በተቀጣው ሰው ዘመድ ሰርግ ወይም ሀዘን ላይ የአፎቻው አባላት እንዳይገኙ እገዳ መጣል ሊሆን ይችላል፡፡ የአፎቻ ከፍተኛና የመጨረሻ ቅጣት ግለሰቡን ከአፎቻ አባልነት ማስወገድ ነው፡፡ የአፎቻን አባል ከአፎቻ ማሰናበት በቀላሉ የሚደረግ ውሳኔ አይደለም፡፡ ማሰናበት ማለት ከሐረሪ ማህበራዊ ግንኙነትና እንቅስቃሴ ተሳትፎ መታቀብ መሆኑን ሁሉም ይረዳዋልና፡፡

በሐረሪ ማህበረሰብ በህግ አካላት ወይንም ፍርድ ቤቶች ከሚወሰን የፍርድ ውሳኔ ወይም ቅጣት በአፎቻ ባህላዊ ህግና ደንብ መሰረት በአፎቻቸው የሚወሰን ፍርድ ወይም ቅጣት የበለጠ ተአማኒነት እና ክብር ይሰጠዋል፡፡

አፎቻ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ

በአሙታ ጋር፣ በበለቹ ጋር እንዲሁም በተለያዩ ማህበራዊ ክዋኔዎች ወቅት ከተለያዩ የከተማው አካባቢ የመጡ የአፎቻ አባላት እጅግ የቀረበ ግንኙነት ይፈጥራሉ፡፡ በመሆኑም በጥንድ ወይም በቡድን በቡድን ተመራርጠው የተቀመጡ አባላት ስለአፎቻቸው ጥንካሬ ወይም ድክመት አንዳንድ ነጥቦችን በማንሳት ይወያያሉ፡፡ በመቀጠልም ሰሞኑን በከተማው ስለተከሰቱ አንዳንድ ማህበራዊ ችግሮች በተለይም በግለሰብ ደረጃ የተፈጸሙና በህብረተሰቡ ዘንድ አሉታዊ ገጽታ ያላቸው ማህበራዊ ሁኔታዎችና ችግሮች የውይይቱ የትኩረት ነጥቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን ግለሰብን አስመልክቶ የሚደረጉ ውይይቶች በተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመሰረቱ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

     ‹‹በአሙታ ጋር›› አንድ ግለሰብ ያልፈጸመውን ተግባር ማንሳት ተጠያቂነትን የሚያስከትል ጉዳይ ስለሆነ አይነሳም፡፡ በዚህ ቦታ የተሳሰቡት ግለሰቦች በአብዛኛው የሚተዋወቁና በሶስቱ የሐረሪ ማህበራዊ ተቋማት ‹‹በአህሊ፣ በመሪኛች ወይም በአፎቻ›› አንዱ ወይም ድርጊት በሚነሳበት ወቅት ጉዳዩ በጥንቃቄ መያዝ አለበት፡፡ እንዲሁም ጉዳዩ በአውንታ ላይ የተመሰረተ ከአሉባልታ የራቀ መሆን ይኖርበታል፡፡

በአጠቃላይ ግን በዚህ ወቅት የሚነሱ ማህበራዊ ጉዳዮች በአብዛኛው ስለ ፍቺ፣ ስለ ሀብትና ንብረት ውዝግብ፣ ስለ ውርስና ሌሎች ማህበራዊ ችግሮችን የሚነኩ ናቸው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች አስቸጋሪ ማህበራዊ ጉዳዮች በመሆናቸው በዘፈቀደ የሚቀርቡ ሳይሆን በግለሰቦች መካከል ቅራኔ በማይፈጥርና ውዝግብ በማያስነሳ ዘዴ ይሆናል፡፡ አቀራረቡን ከእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮት ጋር እያጣጣሙ ለማቅረብ ጥረት ከመደረጉም ሌላ በተጨማሪም ከነቢዩ መሐመድ ሐዲስ እየጠቀሱና ከተጨባጩ ሁኔታ ጋር እያገናዘቡ ድርጊቱ የሚወገዝ ከሆነ ይወገዛል፣ የሚያስመሰግን ከሆነም ይመሰገናል፡፡

አፎቻ ለሐረሪ ሕብረተሰብ ማህበራዊ ህብረትን ወይም አንድነትና ትብብርን የፈጠረ ተቋም ከመሆኑም ሌላ በከተማው ሕዝብ ዘንድ ማህበራዊ ቁጥጥር እንዲዘረጋ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በመሆኑም በዚህ በተዘረጋው ማህበራዊ ቁጥጥርአ ማካኝነት አጥፊው ግለሰብ ላይ ማህበራዊ ተጽእኖ እንዲደርስ ይሆናል፡፡

አፎቻ እና ትምህርት

ሌሎች ማህበራዊ ክንውኖች ላይ እንደ ሚሳተፉት ሁሉ አፎቻ ለሀረሪ ማህበረሰብ ውስጥ ትምህርትን ያስፋፋል፡፡ ይህም ማለት አንዳንድ ጊዜ አፎቻ ‹‹ቁራን ጌይ›› የማቋቋም ስራ ይሰራሉ የነበሩ ‹‹ቁርአን ጌዮች›› ላይ ደግሞ የአስተማሪዎችን ደሞዝ የመክፈል ሐላፊነትን ይወስዳሉ፡፡ ‹‹በቁርአን ጌይ›› ህጻናት ከእምነት ትምህርት በተጨማሪ የባህል እና የስነ-ምግባር ትምህርት ይማራሉ፡፡ በዚህም ቁራን ጌይ ህብረተሰቡን በማስተማር ረገድ የራሱን ሚና ያበረክታል፡፡

አፎቻ እና ባህል

የሐረሪ ብሄረሰብ የራሱ የሆነና ከትውልድ ትውልድ ተጠብቆ የተላለፈ ባህል (ጌይ አዳ) ባለቤት ነው፡፡ ይሄንን ባህል ከመጠበቅና ከማስተዋወቅ ረገድ አፎቻ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

ለምሳሌ የኢንዶች አፎቻ አባላት በተለያየ የሰርግ፣ ሀዘን እንዲሁም በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ሲሳተፉ የሐረሪ ባህላዊ ልብስ ‹‹ጤይ ኢራዝ›› ‹‹አጥላስ›› ወይም ‹‹ጌይ ገናፊ›› አሸብርቀው ነው፡፡

ይህ ባህል የብሄረሰቡን ባህላዊ አለባበስ ከማስተዋወቅ ጀምሮ ወጣቱ ትውልድ ያንን ባህል ይዞ እንዲሄድ አፎቻ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

እንዲሁም አፎቻ በሰርግ ስነ ስርአት በባህላዊ ዘፈኖችና ጭፈራዎች የሚያደምቁት የኢንዶች አፎቻ አባላት ናቸው፡፡

የሐረሪን ማህበረሰብ ባህላዊ እሴቶች ለምሳሌ በተለያዩ ማህበራዊ ክዋኔዎች ላይ ሲሳተፉ እያንዳንዱ የአፎቻ አባላት በባህላዊ አልባሳት አሸብርቀው መሆኑ፣ የብሄረሰቡን ባህላዊ አለባበስ ከማስተዋወቅ ጀምሮ ህብረተሰቡ አልባሳቱን በስፋት እንዲጠቀምበት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል

በእያንዳንዱ የሐረሪ ማህበረሰብ ሰርግና፣ የተለያዩ ባህላዊ ክብረ በኣላት ላይ የሚዘጋጁ ማህበረሰባዊ ትውን ጥበባት፣ ለምሳሌ ባህላዊ አገር በቀል የሆኑ ዘፈኖችና ጭፈራዎችን በማድመቅና በመምራት አፎቻ የባህሉን ቀጣይነት በማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በአጠቃላይ አፎቻ የብሄረሰቡን ባህል ማስተዋወቅና በመጠበቅ አፎቻ ያንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡

ማጠቃለያ

በሀረሪ ማህበረሰብ የተለያዩ ማህበራዊ ተቋማት አሉ እነዚህ ማህበራዊ ተቋማት ከተለያየ አቅጣጫ እክል ይገጥማቸዋል ከነዚህ እክሎች መካከል በአሁኑ ጊዜ ወጣቱ ትውልድ አገር በቀል የሆኑትን ባህሎች እንደ ኋላ ቀር በመቁጠር የምእራቡን አለም ተከታይ ሆኗል፡፡ አፎቻም የዚህ ችግር ተጠቂ እየሆነ ነው፡፡

አፎቻ በሀረሪ ብሄረሰብ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ህይወት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተና አሁንም እያበረከተ ያለ ባህላዊ ተቋም ነው፡፡

አስተያየት

      በአፎቻ ላይ ያለው ግንዛቤ በጣም አናሳ ስለሆነ ለወደፊቱ በማህበረሰቡ ዘንድ ሊኖረው የሚችለው ጥቅም በሰርግና በሀዘን ላይ ብቻ እየተገደበ ነው፡፡ ለዚህም ችግር የመፍትሄ ሀሳብ መንግስትም ሆነ ማህበረሰቡ የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አፎቻን የሚያሳትፉ እንቅስቃሴዎች ቢሆኑ ጥሩ ውጤት ይገኛል፡፡ በዚህ ሁኔታ አገር በቀል እውቀቶቻችንን እና ባህልን ከማሳደግ አንጻር የአፎቻ ሚና ቀላል ስለማይሆን በጋራ ለመስራት በስፋት መንቀሳቀስ አለብን፡፡

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በኩል በአፎቻ ዙሪያ ሰፋ ያለ የጥናትና ምርምር ስራዎች ቢሰሩና በድረ ገጾችና ህትመቶች ላይ ቢካተት ለመላው የኢትዮጲያ ባህሎችና አኗኗር ዘይቤዎች በሐረሪ ‹‹ጌይ ኡሱእ›› ማህበረሰብ የሚበረከት ማህበራዊ ተቋም ሊሆን ይችላል፡፡

ዋቢ መፅሐፍት

አብዱላሂ ሼኽ አህመድ ቡህ (1998 .) የሐረሪና ሐረር ከተማ ታሪክ፣ ሐረር

 

አህመድ ዘከሪያ፡ የሐረሪ አመፅ፡/1992 ሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ/

 

አፈንዲ ሙተቂ፣ ሐረር ጌይ፣ የአስገራሚዋ ከተማ ኢትኖግራፊክ ወጎች፣ ጥር 2004፣ ሐረር

 

Ali Naji, Values, Norms, and Customs in Harari self-identifications, August 2012, Diredawa.

 

Hamza Yousuf, Afocha Harari people indigenous social institution, a BA thesis, department of History and heritage management, DD University. June 2014.

 

History harar and the Hararis, Harari people regional state culture heritage and tourism bureau. October 2015 Harar

 


Cultural studies and research Cultural studies and research