በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ አራት ቋሚ ቅርሶች ሊታደሱ ነው

አዲስ አበባ ጥቅምት 3/2010 በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ አራት ቋሚ ቅርሶች ላይ ዕድሳት ሊያደርግ መሆኑን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የአክሱም ሐውልት ፣ የጎንደር ፋሲለደስ ግንብና የጢያ ትክል ድንጋዮች በተያዘው በጀት ዓመት እድሳት የሚካሄድባቸው የሚዳሰሱ ቅርሶች ናቸው።
ለቅርሶቹ ጥገና መንግስት ከበጀተው 34 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ ከአውሮፓ ህብረት 400 ሺህ ዶላር፣ከአሜሪካና ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት መገኘቱን ባለስልጣኑ አስታውቋል።

በባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ዘለቀ ቅርሶቹ በእርጅና እና በወቅቶች መለዋወጥ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ሆነው በመቆየታቸው የመሰነጣጠቅ ፣ዝናብ የማስገባት ችግሮች እየተከሰተባቸው በመሆኑ ጥገና ማድረግ አስፈልጓል፡፡
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና የአክሱም ሀውልት የጥገና እና የጥናት ስራዎች በተያዘው በጀት አመት እንደሚከሔድ ነው የሚናገሩት፡፡
የጎንደር ፋሲለደስ አንዳንድ ቤተ መቅደሶች ላይ ቀደም ሲል የተከሰተውን የመፈራረስ ችግር በዘላቂነት ለመጠገን የአማካሪ ተቋም መረጣ ተካሂዶ በተያዘው አመት ወደ ጥገና ስራ እንደሚገባም ነው ያብራሩት፡፡


በጢያ ትክል ድንጋይ ላይ የተከሰተውን የመሰነጣጠቅና መንጋደድ ችግር ከመሬቱ አቀማመጥና ከአፈሩ አይነት የተከሰተ እንደሆነ በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል።
በዚህም ቅርሱን ለማደስ ተጨማሪ የአርክቴክቸርና የአፈር ምርመራ ጥናቶች በሁለት ወራት ውስጥ ተካሂዶ ወደ ጥገና ይገባልም ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመካነ ቅርስ ጥናት መምህር ዶክተር ካሳዬ በጋሻው እንዳሉት በኢትዮጵያ የጎብኚዎችን ቀልብ እየሳቡ ያሉ ቅርሶች ዘመናትን ያስቆጠሩ በመሆናቸው ጥገና ሲታሰብ ስለ ቅርሶቹ በቂ ዕውቀት ያለው ሰው ገበያው ላይ መኖሩን በቅድሚያ ማሰብ ያስፈልጋል።
የቅርሶች ጥገና እና የአስተዳደር ስርዓቱን በባለሙያዎች ከማስመራት በተጨማሪ ባለሃብቱንና ሕብረተሰቡን በሚያሳትፍ መልኩ ማካሄድ እንደሚገባም ተናግረዋል።


ዶክተር ካሳዬ በዘርፉ ቀጥተኛ እውቀቱ ያለው የሰው ሃይል ማፍራት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ነው የሚያመለክቱት፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በተያዘው በጀት አመት ከመንግስት 34 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ ከክልሎችና ከአጋር አካላት በማሰባሰብ የጥገና፣የቅደመ ጥገና ጥናት፣የወሰን መከለል እና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ የትኩረት ማዕከሉ መሆናቸውን ገልጿል፡፡
ምንጭ ኢ.ዜ.አ


News and Updates News and Updates