​የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የጉዞ ቱሪዝምና ዐውደ-ርዕይ ባዛር በሀዋሳ ከተማ በደማቅ ስነ-ስርዓት ተጀመረ!

የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መዲናዋ ሀዋሳ በዛሬው ዕለት በተከፈተው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የጉዞና ቱሪዝም ዐውደ-ርዕይ ደምቃለች፡፡ በአገችን ከሚገኙ ከተሞች መሃከል በርካታ ቱሪስቶችን እያስተናገደች የምትገኘው ሀዋሳ ዛሬ ደግሞ በአገራችን የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ጉልህ ስፍራ ያለው ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ በማዘጋጀት ለዘርፉ እድገት እምርታ ማሳያ የሆነውን ጅማሮ እንካችሁ ብላለች፡፡

የደቡብ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና ኢኖቪዥን ኢቨንትስ በጋራ ያሰናዱትና ከነሀሴ 11-16/2009 ዓ.ም በሚቆየው በዚህ አውደ-ርዕይ ላይ መሰረታቸውን በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ያደረጉ በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች ተሳትፎ አድርገውበታል፡፡

የክልሉን መንግስት በመወከል ንግግር ያደረጉት በክልሉ የከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ክፍሌ ገብረማርያም በመልዕክታቸው ከ56 በላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተፈቃቅደውና ተቻችለው በአንድነት የሚኖሩበት በርካታ ቋንቋዎች፣ ባህል፣ ታሪክና ማራኪ የሆኑ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ መስህቦች የሚገኙበት እንዲሁም ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው 12 የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ  አራቱን አቅፎ መያዙን በመግለፅ መንግስታቸው እነኝህንና ሌሎችን  እንዲለሙ እንዲጠበቁና እንዲተዋወቁ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የሀዋሳ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደችው ዓለም አቀፍ የጉዞና ቱሪዝም አውደ-ርዕይ የክልሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መገለጫ የሆኑ ሀብቶችን በተደራጀ እና በተቀናጀ አግባብ ለማስተዋወቅና ለማበልፀግ አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው እምነታቸውን በመግለፅ የክልሉ መንግስት ይህ ተግባር ቀጣይነት እንዲኖረው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም በመልዕክታቸው  እንደገለፁት  አሁን ባለንበት ወቅት የቱሪዝም ዘርፍ የሀገራትን ገቢና ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ከፍ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ እምርታ እያሳየ መሆኑን፤ መንግስታትም ይህን ሁኔታ በውል በመረዳት ከእስካሁኑ በተሻለ ሁኔታ ለዘርፉ መጠናከር ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን  እየነደፉ ወደ መሬት የሚወርዱበትን መንገድ በማመቻቸት ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢና በአጠቃላይ ዘርፉ ለአገር የሚያበረክተውን ድርሻ ትርጉም ባለው መልኩ እንዲወጣ ለማድረግ እየሰሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የቱሪዝም ዘርፍ በዓለም ላይ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት ቢሆንም አህጉራችን አፍሪካ ግን ከተጠቃሚነት አንፃር  ያላትን መስህቦች ያህል ባለመሆኑ በዓለም አቀፍ ድርሻ ላይ የምታበረክተው አስተዋፆ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከአብዛኛው የአፍሪካ አገራት የተለየ አፈፃጸም ያልታየባት መሆኑንና  ለዚህም እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መሃከል ባለፉት ጊዜያት ከዘርፉ ተዋናዮች የሚጠበቀውን ያህል ሀገራችንን ተወዳዳሪና ተመራጭ ሊያደርግ በሚችል መልኩ ዘርፉን የማዘመንና የማሳደግ ስራ አለመከናወኑ መሆኑን ገልፀው ይህም ሲባል የመዳረሻዎቻችንን አካባቢ ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በማልማት ረገድ ክፍተቶች መኖራቸው፣ አገልግሎት አሰጣጣችን በተማረና በሰለጠነ የሰው ሀይል በመጠቀም ረገድ ብዙ ርቀት አለመራመዳችን፣ ያሉንን ብርቅዬ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ሀብቶቻችንን የዘመኑን ቴክኖሎጂ ተጠቅመን ለዓለም የሚጠበቀውን ያህል ማስተዋወቅና ተወዳዳሪ የሆነ የግብይት ስርዐት በመመስረት ረገድ ብዙ ርቀት አለመጓዛችን መሆኑን   ገልፀዋል፡፡

ሚኒስትሯ አያይዘውም የኢፌዲሪ መንግስት እነኝህን እና ተያያዥ ችግሮችን በመረዳትና በማጤን ተጨባጭ የሆኑ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ በማሳወቅ፤ ለዚህም እንደ አብነት ከሚጠቀሱት ተግባራት መካከል በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት፣ የቱሪዝም ቦርድ መመስረትና የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት እራሱን ችሎ እንዲደራጅ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በአጠቃላይ በዘርፉ አገራችንን ተወዳዳሪ ለማድረግ እንዲሁም የሚፈለገውን ጥቅም ለማግኘት እንድንችል የተለያዩ የትውውቅ ጉዞዎችን ማዘጋጀትና አገራችንን በማስተዋወቅ እንደዚህ ዓይነት ዓለም አቀፍ የጉዞና ቱሪዝም ኤግዚቢሽኖችንና የ ንግድ ትርኢቶችን በማዘጋጀት አገራት እንዲሳተፉባቸው በማድረግ ያሉንን ሀብቶች ማስተዋወቅ ጥሩ ጅምር መሆኑን እና ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባ በማሳሰብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚጠበቅበትን ስራ እንደሚያከናውን ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም የእለቱ የክብር እንግዳ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ በርካታ መስህቦች ያላት እንዲሁም ገና ያልተጠቀምንባቸው የቱሪዝም መስህብ ሊሆኑ የሚችሉ  የተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽና ባህላዊ ሀብቶች ባለቤት ብትሆንም የቱሪዝም ገቢያችን ግን ዝቅተኛ መሆኑ ሊያስቆጨን እንደሚገባ እና  ዘርፉ እንደ ሌሎች መስኮች ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራበት ትልቅ አቅም ያለው ምናልባትም የተሻለ መሆኑን በመግለፅ የዘርፉ ተዋንያን ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚገባቸው በማሳሰብ መልእክታቸውን አስተላልፈው ለመክፈቻ የተዘጋጀውን ሪባን በመቁረጥ ዐውደ-ርዕዩን በይፋ አስጀምረዋል፡፡

News and Updates News and Updates