በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከፍተኛ ተፅዕኖ ውስጥ የሚገኘውን የሀገራችን የቱሪዝም ዘርፍ በቀጣይ ከገባበት ቀውስ ማገገም የሚችልበት እቅድ ተዘጋጀ፡፡

የኢፌዲሪ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከቱሪዝም ኢትዮጵያና ከሆቴልና አስጎብኝ ማህበራት ጋር በመሆን ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የቱሪዝም ማገገሚያ እቅድ ባሳለፍነው አርብ ለዚሁ ተግባር በተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ የፀደቀ ሲሆን በዛሬው እለት ደግሞ ከክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በቪዲዮ ኮንፈረንስ የተደረገውን ውይይት የመሩት የኢፌዲሪ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ክብርት ዶ/ር ሂሩት ካሳው የኮሮና ወረርሽኝ በቀዳሚነት ከሚጎዳቸው ዘርፎች ዋነኛው ቱሪዝም ነው ያሉ ሲሆን ይህንኑ ግምት ውስጥ በማስገባት ፈጣን የማገገሚያ እቅድ ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ ይህ ወቅታዊ እቅድ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
የየክልሉ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የሚመለከታው አካላት ወረርሽኙ የጋረጠውን አደጋ ግምት ውስጥ በማስገባት ይህን እቅድ በፍጥነት ማዘጋጀታቸው የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡


በተጨማሪም ከየክልሎቹ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ወረርሽኙ ያስከተለባቸው ፈተናዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው ሀገራችን ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ በአዲስ መልክ ተጠናክሮ የሚመለስ የቱሪዝም ዘርፍ ለመፍጠር የተፈጠረውን ችግር እንደ መልካም አጋጣሚ ልትጠቀምበት ትችላለች ያሉ ሲሆን እቅዱም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልፅዋል፡፡
ነገ ለመጓዝ ዛሬን ከቤታችን አንውጣ የሚለውን ዘመቻ በማጠናከር ከኮሮና መልስ ጠንካራ ቱሪዝም ይዘን ወደ አለም አቀፍ ገበያ መመለስ እንችላለን ብለዋል፡፡
በሰነዱ ዝግጅት ላይ የተሳተፉት በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የአለም አቀፍ ቱሪዝም ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ቴድሮስ ደርበው በበኩላቸው ቱሪዝም በባህሪው ከገባበት ችግር በፍጥነት የመውጣት ባህሪ ያለው ኢንዱስትሪ እንደመሆኑ ይህንኑ የሚያግዝ እና በቀላሉ ሊተገበር የሚችል ማገገሚያ እቅድ አስፈላጊ በመሆኑ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡


ይህ እቅድ ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ እስከ ትልልቅ ባለሀብቶች ድረስ ያለውን የዘርፉ እንቅስቃሴ መልሶ ለማነቃቃት ታስቦ የተዘጋጄ መሆኑን ያብራሩት ደግሞ በእቅድ ዝግጅቱ ላይ ሲሳተፉ የነበሩትና ሰነዱን ለውይይት ያቀረቡት የቱሪዝም ዘርፍ አማካሪው አቶ ይስፋልኝ ሀብቴ ናቸው፡፡ በመጨረሻም አጠቃላይ የማነቃቂያ እቅዱ እንደ የአለም ቱሪዝም ድርጅትና አለም አቀፍ የጉዞና የቱሪዝም ካውንስል (UNWTO, WTTC) ከመሳሰሉ አለም አቀፍ ተቋማቶች የማገገሚያ እቅዶች ጋር ተቀናጅቶ እየተመራ መሆኑን ክብርት ሚኒስትሯ ገልፀዋል፡፡
በክልሎችና በፌደራል ተቋማቱ በሚሰሩ ስራዎቹ ዙሪያ ወጥ የሆነ የመረጃ ፍሰት ለመፍጠር እንደሚሰራም ተገልጧል፡፡


News and Updates News and Updates