ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የተሰጠ መግለጫ

የኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ ሰጋት ሆኖ መቀጠሉ ይታወቃል። በተመሳሳይ በአገራችን የተጋረጠ ወቅታዊ ችግር መሆኑ ለሁላችንም ግልፅ ነው። የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑና ሰዎችም ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩ ስለሆነ በእንግዶች በኩልም ሆነ በመስተንግዶ ተቋማት በኩል ከፍተኛ ጥንቃቄ ካልተደረገ በስተቀር ለቫይረሱ መስፋፋት ዓይነተኛ አስተዋፅዖ ሊኖረው እንደሚችል ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል።
በሌላ በኩል ቫይረሱ እየተስፋፋ ከመሆኑ አንፃር በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገራችን የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል። ይህን መነሻ በማድረግ በአንድ በኩል ቫይረሱን ለመግታትና ለመቆጣጠር ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ፣ በሌ በኩል ደግሞ ችግሩ በቀጣይ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ በአንድነትና በተባበረ ክንድ መመከት እንዲቻል ይህን መግለጫ ማውጣት አስፈልጓል።
1. የውጭ ዜጎች ወደ አገራችን ሲገቡ 14 ቀናት ከማህበረሰቡ ጋር ሳይቀላቀሉ በሚዘጋጅላቸው ሆቴሎች እንዲቆዩ መንግስት ያስተላለፈውን አቅጣጫ መሰረት በማድረግ ለጊዜያዊ ማቆያነት ጊዮን ሆቴልና ስካይ ላይት ሆቴል የተመረጡ በመሆኑ ሁሉም ሆቴሎችና አስጎብኝ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች በዘርፉ የተሰማራችሁ አካላት ይህን ተገንዝባችሁ አስፈላጊውን ትብበር እንድታደርጉ በአፅንዖት እናሳስባለን።

2. ለጊዚያዊ ማቆያነት የተመረጣችሁ ሁለት ሆቴሎችም (ጊዮን ሆቴልና ስካይ ላይት ሆቴል) የጉዳዩን አሳሳቢነትና የፈጠረውን ስጋት የሚመጥን ዝግጅት በማድረግ በተለይም፣
የሆቴሎቹን ሁሉም አመራሮችና ሰራተኞች በቂ ግንዛቤ በማስጨበጥ፣
ከሆቴሎች መግቢያ ጀምሮ የመገልገያ ቁሳቁሶችንና ፋሲሊቲዎችን በጥንቃቄ በመያዝና በማፅዳት፣
ከውጭ ከገቡ ዜጎች ውጭ የትኛውም አይነት ተገልጋይ ወደ ሆቴሎቹ ቅጥር ግቢና መገልገያ ስፍራዎች እንዳይገቡ በመከልከል፣
በተለይ እንግዳን የመቀበልና የመንከባከብ ነባርና ውብ ባህል ያለን እንደመሆኑ ኢትዮጵያውያን ላልሆኑና በአገራችንና በሆቴላችን እኛን አምነው ለሚኖሩ ሰዎች በትሁት ስብዕና የተለየ ድጋፍና እንክብካቤ ማድረግ ይኖርብናል፣የሚያልፍ ቀን የማያልፍ ስም ይተክላልእንደሚባለው አርቆ አሳቢዎችና ሩህሩሆች መሆን ይኖርብናል፡፡በዚህም የአገራችን ስምና ዝና ከፍ እናደርጋለን፡፡
ከሚመለከታቸው የመንግሰት ተቋማት ተገቢውን ትስስር በመፍጠር፣
የሚሰጡ መግለጫዎችንና ማስጠንቀቂያዎችን በመከታተልና ተግባራዊ በማድረግ፣ ከውጭ ለሚገቡ ዜጎች የምትሰጧቸውን አገልግሎቶች ዋጋ ከሌላው ጊዜ በተለየ ከፍተኛ ቅናሽ በማድረግ አገራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ሚኒስቴሩ በጥብቅ ያሳስባል።

3. አሁን የገጠመን ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ችግር በቱሪዝም ዘርፉ ለተሰማሩ ሁሉም አካላት የጋራ አደጋ በመሆኑና ጉዳቱም በተናጠል ሳይሆን በዘርፍ ደረጃ የተጋረጠ ስለሆነ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ የተሰማራችሁ ሁሉም አካላት ይህን ተገንዝባችሁ ከመቸውም ጊዜ በተለየ መተሳሰብና መተባበር በተሞላበት መልኩ መረባረብ ያስፈልጋል። ስለሆነም ሁሉም ሆቴሎች ቫይረሱ ከመከሰቱ ቀደም ብለው ለውጭ ጎብኝዎች የጉዞና ጉብኝት ጥቅል ፕሮግራሞችን የሸጡ አስጎብኝ ድርጅቶች ለሆቴል አገልግሎት ቀደም ብለው የከፈሉትን ክፍያ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍላቸው በማድረግ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትውጡ እናስገነዝባለን።

4. በዘርፉ የተሰማራችሁ የንግድና የሙያ ማህበራት፣ ሆቴሎች፣ አስጎብኝ ድርጅቶች፣ የሆስፒታሊቲና ቱሪዝም ባለሙያዎች እንዲሁም ከፌደራል እስከ መዳረሻ ድረስ ያላችሁ ሁሉም በቱሪዝም አገልግሎት እሴት ሰንሰለት ውስጥ የተሰማራችሁ አካላት የዘርፉን ልዩ ባህሪይ ተገንዝባችሁ ከመንግሰት የሚሰጡ መመሪያዎችንና መግለጫዎችን በንቃት በመከታተል ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረግ ጥረት የተቀናጀ ርብርብ እንድታደርጉ ከአደራ ጭምር እናሳስባለን።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣
ችግሩም መፍትሄውም የጋራ ነው!


News and Updates News and Updates