ምርትና አገልግሎትን ስናስተዋውቅ ተጠቃሚዎቻችንን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንደሚኖርበት ተጠቆመ፤

ምርትና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የምንጠቀመውን ዘልማዳዊ የቋንቋ አጠቃቀምን ለመፈተሸ እና በቀጣይም ተገቢ የእርማት እርምጃ ለመውሰድ ያስችል ዘንድ ‘’የምርት እና አገልግሎት አቅርቦት ከህብረተሰቡ የቋንቋ  አጠቃቀም አኳያ’’ በሚል ርዕስ ሰኔ 5/2010 ዓ.ም  ከሚመለከታቸው ባለድርሻ ጋር በጌትፋም ሆቴል ምክክር ተደረገ፡፡

 

በምክክር መድረኩን ያዘጋጀው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሲሆን፣ በመድረኩ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት፣ የት/ት ቢሮ፣ የደረጃዎች አሰጣጥ ባለስልጣን፣ የፍትህ ቢሮ፣ የመድሃኒት እና ምግብ ቁጥጥር ባለስልጣን ተወካዮች፣ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን፣ ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የመጡ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

 

 

 

በምክክር መድረኩ ላይ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ጥናታዊ  ጽሁፎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን ከነዚህም መካከል  በፕሮፌሰር ባዬ ይማም፤ ‘’ቋንቋ እና ማህበራዊ አገልግሎት’’፣ በዶክተር መልኩ ተዘራ፤ ‘’በአማራ ክልል የንግድ ስያሜዎች ሂሳዊ ዲስኩርና ትንተና፣ በመስተንግዶ ዲስኩር ተተኳሪነት’’  እና  በአቶ አለማየሁ ጌታቸው ‘’በአዲስ አበባ እና ሌሎች የአገራችን የተመረጡ ከተሞች የማስታወቂያና የቋንቋ አጠቃቀም’’ በሚል ርዕስ  የቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች ይገኙበታል፡፡

 

 

ፕሮፌሰር ባዬ ይማም ‘’ቋንቋ እና ማህበራዊ አገልግሎት’’ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ አጽንኦት ሰጥተው እንዳሳሰቡት፤ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምርት እና አገልግሎቶችን ለተደራሹ ህብረተሰብ ስናስተዋውቅ ብሄራዊ የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎቻችን ጨምሮ በሌሎች የዜና አውታሮች የምንጠቀመው ቋንቋ የተጠቃሚውን ህብረተሰብ የእውቀት ደረጃ፣ ባህል፣ ማንነት፣ የቋንቋ  ክህሎት እና ሌሎች የተደራሹን ማህበረሰብ መሰረታዊ ጉዳዮችን ከግምት ያላስገቡ  መሆናቸውን ጠቁመው ምርትና አገልግሎቶችን ስናስተዋውቅ ተጠቃሚዎቻችንን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ  ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ አክለውም በሁሉም ሚዲያዎች ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች፣ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች ለብዙሃኑ ህዝብ ጋር የሚደርስ ንግግር ሲያደርጉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው እና ወልጣቀኝ የሆነ የቋንቋ  አጠቃቀም እንደማያስፈልግ ያሳሰቡ ሲሆን በተለይ ግን ምርት፣ አገልግሎት፣ ት/ት እና መረጃ የህዝብ ስለሆኑ ማድረሻው ቋንቋም የህዝብ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ሌሎች  ጥናት አቅራቢዎችም በተመሳሳይ እደገለጹት ምርት እና አገልግሎትን ለማስተዋወቅና ለመሰየም የምንጠቀመው ቋንቋ መሰረታዊ ችግር  እየተስተዋለበት ያለ መሆኑን ጠቁመው ማንኛውም አምራችም ይሁን አገልግሎት አቅራቢ የሆንን  በእርግጥም ደንበኛ ንጉስ መሆኑን በመረዳት ምርትና አገልግሎቶችን ተገልጋዩ የሚያውቀውን  ቋንቋ መግለጽ  እና በተቻለ መጠን አገራዊ ስያሜዎችን መጠቀም እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ይህንን ማድረጉም   ከምርት እና አገልግሎቱ ጋር ተጠቃሚው ህ/ሰብ ስነ-ልቦናዊ ቁርኝት እንዲኖረው ከማድረጉም  ባሻገር ተገልጋዩ ይዘቱንም በቅጡ ስለሚረዳ ጥቅም እና ጉዳቱን ለመለየት አይቸገርም ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በራሱ የሚተማመንና የሚኮራ ትውልድ በመፍጠር ሂደቱ ላይም ትልቅ ሚና ስለሚኖረው ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ልዩ ትኩረት ሰጥተው በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም ቀጣይነት ያላቸው ተመሳሳይ የውይይት መድረኮች ተዘጋጅተው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ  አካላት ጋር ውይይት እንደሚደረግ እና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የሚኒስቴር መ/ቤቱ አጠናክሮ እንደሚሰራም በማስገንዘብ ነው መርሐግብሩ የተጠናቀቀው ፡፡

News and Updates News and Updates