የገዳ ሥርዓት በዓለም ቅርስነት የተመዘገበበትን 4ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለሁለት ቀናት የተካሄደው ዝግጅት ተጠናቀቀ

የገዳ ስርዓት በዓለም ቅርስነት የተመዘገበበትን 4ኛ ዓመት የመታሰቢያ በዓል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የገዳ ፓናል ውይይት በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተከፈተበት ወቅት የዕለቱ እንግዳ የሆኑት የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰብ አገር ናት። ኦሮሞ ደግሞ አንዱ ነው ፣ የአኩሪ ታሪክ ባለቤት ነው ያሉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በዩኔስኮ የተመዘገበው የገዳ ሥርዓት ዋናው ሲሆን፣ ይህም የማይዳሰስ ቅርስ እንደመሆኑ ህልውናውን ማስቀጠልና ማስጠበቅ የሚቻለው በመንከባከብና ከትውልድ ወደትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ እንደሆነ አመልክተዋል።


አቃፊነትና ሰላም የገዳ ስርዓት እሴት ስለመሆናቸው ማሳወቅ ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ይህንኑ በማድረጉ በኩል በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ጠንክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። የገዳ ስርዓት በማንሰራራት ላይ እንደሚገኝ ገልፀው፣ በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ እንዲሰጡ መደረጉ የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
የገዳ ሥርዓት በዓለም ቅርስነት የተመዘገበበትን 4ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለጉብኝት የተዘጋጀው የጉጂ የባሕል አልባሳት፣ ጌጣጌጥ እንዲሁም ምግቦች እና የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች በዕለቱ እንግዶች እና የበዓሉ ታዳሚዎች ተጎብኝቶ ለሁለት ቀናት የቆየው ዝግጅት ተጠናቅቋል።
በዕለቱ ከደበሌ ጀምሮ ያለውን የገዳ ሥርዓት ደረጃን የሚያሳይ ትርኢት ለተመልካች ቀርቧል።
መርሐ ግብሩ በአባ ገዳዎች ምርቃት ተጀምሮ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የምዕራብ ጉጂ ዞን አስተዳደር ለክብር እንግዶች የጉጂን የባሕል አልባሳት ተሸልመዋል፡፡


ዜናዎች ዜናዎች