የሚኒስተሯ መልዕክት የሚኒስተሯ መልዕክት

H.E Dr. Hirut Weldemariam

ከሁሉ አስቀድሜ አገራችንን ለምትጎበኙና በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ  መዋዕለ ንዋያችውን በማሰባሰብ ኢንቨስት ለምታደርጉ ከልብ የመነጨ ላቅ ያለ ምስጋናዬን እንዳቀርብ ፍቀዱልኝ፡፡ ይህ ድረ-ገጽ የሚጠበቀውንና የምትፈልጉትን መረጃዎች ይሰጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ፣ በባህልና ታሪክ ሀብቶቿ ዘመን የማይሽረው አንድነትን የፈጠረች፣ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዩ ከሆነው የራሳቸው ቋንቋ፣ ሐይማኖትና ወግ የሚነገሩባት የሕብረ-ብሔራዊት ሀገር ናት፡፡በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የዓለም ቅርሶች መዝገብ ከተመዘገቡ ዘጠኝ የማይቀሳቀሱ ቅርሶች አንዱ የሆነው  የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን፣ ከ4261 ሜትር ከፍታ ላይ  የሚገኘውን የራስ ዳሸን ተራራን  ጨምሮ  እስከ አፋር ክልል ከባህር ወለል በታች 116 ሜትር ዝቅተኛ ቦታ ዳሎል ዲፕሬሽን ድረስ  በአስደናቂ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና የአየር ንብረት፣ የብርቅዬ የዱር እንስሳት መገኛ፣ የራሷ የዘመን አቆጣጠርና ፊደል፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት በመሆኑዋ  ኢትዮጵያ በእርግጠኝነት በአስገራሚ  የቱሪዝም ሀብቶች መገኛ ምድር /ልዩ ፕላኔት/ አድርጓታል፡፡

ይህም የቅድመ ሰው ዘር መገኛና የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በእግሩ መራመድ የቻለባት ሀገር ናት፡፡ የእኛ ቅድመ አያት የሆነችው የ3.2 ሚሊዮን ዓመት የድንቅነሽ(ሉሲ) እና የአርዲ የ4.4 ሚሊዮን ዓመት ከመሳሰሉት የቅድመ ታሪክ እና ፓሊዮኦ-አርኪዮሎጂካል ቅርሶች ባለቤት ናት፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ የሁላችን ቅድመ አያቶች መገኛ ወብ ምድር /ፕላኔት/  ናት ማለት እንችላለን፡፡  ስለሆነም ሁሉም ዜጋ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የቅድመ አያቶቹን የጣት አሻራ እንዲጎበኝ ተጋብዟል፡፡

በታሪክም አንጻር  ኢትዮጵያን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከታት የ3000 ዘመን ታሪክ ያላት መሆኑዋን ያስገነዝበናል፡፡ ከታላቋ አክሱም  የነገስታት ሥርወ-መንግስታት ዘመን ጀመሮ የጥናታዊ ስልጣኔዋ መነሻ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ ፡፡ ለአብነት በአክሱም ከተማ የሚገኙ የነገሥታት የመቃብር ሥፍራዎችና ሐውልቶች  ሕያው ተምሳሌቶች ናቸው፡፡  በመቀጠል በመካከለኛው ክፍሌ ዘመን ከሐይማኖታዊ ሥልጣኔዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ በላሊበላ ታላላቅ ውቅር አብያተክርስቲያናት መታነፃቸው በተለይም ከመሬት በላይ ባለ ንጣፍ ድንጋይ ወደ ታች ተፈልፍለው ታነፀው የወጡ የምድር ውስጥ ሕንፃዎች የደመቁበት ነው፤ ይህም ለእምነቱ መታሳቢያነት ብቻ  ሳይሆን የሕንፃ ጥበብን ያሳየ ነው፡፡ የአንድ ሺህ ዓመታት በላይ  ዕድሜን ያስቆጠረው  የሐረር ጀጎል ግንብ ኢትዮጵያን ከጥንታዊ እስላማዊ ከተሞች አንዱ ሲያደርጋት፣ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ የታነፀውና በኢትዮጵያ  የጥንታዊ  ከተሞች ታሪክና ዕድገት ፈር ቀዳጅ የጎንደር ነገሥታት ግብረ ህንፃ ተመሳሳይ ታሪክን የሚዘክር ነው፡፡ ሌላው የኮንሶ ባህላዊ መልካምድርና የአፈር እቀባ፣ የእርሻ አስተራረስ ዘዴ፣ እንዲሁም በአገሪቱ መካከለኛ ከፍል የሚገኘው የጢያ ትክል ድንጋዮች፣ የታችኛው ኦሞ እና የመካከለኛ አዋሽ ፓሊዮአንትሮፖሎጂካል ሥፍራዎች፣ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ 12 የባህላዊ፣ ታሪካዊ ተፈጥሯዊ ቅርሶች፣  12 የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች እና 4 ከበባዊ ብዝሃሕይወት ጥበቃ ቦታዎች ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በተነፃፃሪነት ቁጥራቸው በርከት ያሉ ብሔራዊ ፓርኮች ያላት በመሆኑ ጉብኝት ለሚፈልጉ ቱሪስቶች ደስታን የሚፈጥሩ የጥብቅ ብዝሃሕይወት እና የዱር እንስሳት መኖሪያ ቦታዎች  እንደየሥነምህዳራዊ በያሉበት ለማየት ብሎም ለጉዞና የጀብደኝነት ቱሪዝም  መልካም አጋጣሚን የፈጠረ ነው፡፡ 

ኢትዮጵያ ብዝሃነትን የተቀበለችና ከ80 በላይ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች ሕዝቦች ሀገር ናት፡፡ ሕዝቦቿም የየራሳቸው የሆነ ማንነት የሚገለጽበት ባህል፣ ታሪክ፣  ቋንቋ፣ ስነቃል፣ ወግ፣ ዕምነቶች፣ የባህል ዕሴቶችና ሥነጥበብ  ሀብቶች አሏቸው፡፡ በዚህ ብዝሃነት ውስጥ ባንድነት በመቻቻልና በመከባበር በስላም የሚኖሩ ናቸው፡፡ በአንፃሩም ለእንግዶቻችንና ቱሪስቶቻችን አቀባበል ልምድ በሕዝቦቻችን መካከል  ሲወርድስዋረድ የመጣ ድንቅና ውብ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል አለን፡፡

በመጨረሻም ውድ አንባቢያን  እነዚህን የኋላ ታሪኳቹዋን ለመናገር በመብቃቴ ላቅ ያለ ኩራት ይሰማኛል፡፡  ኢትዮጵያ ገና ብዙ ያልተነኩ የባህልና ቱሪዝም ሀብቶች ያሏት በመሆኑ ለማየት ዕድሉ ያልገጠማችሁ በውጭ አገር የምትኖሩ ዜጎቻችን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጎብኙዋት፡፡ መዋዕለ ንዋያችሁንም በማሰባሰብ ኢንቨስት እንድታደርጉ በታላቅ አክብሮት ጋብዤያቸዋለሁ፡፡ 

ስለሆነም የሁላችንም መገኛ የሆነችዋ ኢትዮጵያ  የደመቀችና የለመለመች ምድር እንድትሆነን ሀብቶቻችን በጋራ በማልማትና በመጠበቅ ኢኮኖሚያዊ የጋራ ተጠቃሚነትን እናስፋፋ እንላለን፡፡!!

በብዙ ማይልስ ርቀት ላይ ያላችሁ ሁሉ የምትፈልጉትን ድጋፍ፣ ተጨማሪ ማበረታቻዎች እና ሰፊ ሽፋን ያለው አገልግሎት ማግኘት የምትችሉበትን ሁኔታ የማመቻቸት ኃላፊነት ለሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን የተሰጠው ተግባር መሆኑን መግለጽ እወቃለሁ፡፡

ወደዚህች ብዝሃነትን በምታስተደናግደዋ ብቸኛዋ የሰው ዘር መገኛ፣ የቡና መገኛ፣ ከአፍሪካ የራሷ ፊደል ያላትና የአፍሪካ ህብረት መዲና አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጣችሁ፡፡

ክብርት ዶ/ር ሂሩት ወ/ማርያም
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር