የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን
አጭር ታሪካዊ ዳራ
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ሥራ በ1936 ዓ.ም. የመሳፍንትና የመኳንንቱን የወግና የክብር አልባሳት በቤተ መፃህፍት ሕንፃ ውስጥ ለኤግዚቪሽን በማቅረብ በቅርስ እንክብካቤ ላይ የመጀመሪያ ግንዛቤ አስገኘ፡፡
በዚሁ ግንዛቤ መነሻነት በ1945 ዓ.ም. ከፈረንሣይ መንግሥት ጋር የሁለትዮሽ የባህል ስምምነት ተፈርሞ በወቅቱ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከናወኑ የአርኪዎሎጂ ጥናትና ምርምሮች በርካታ ቅርሶች በመገኘታቸው ሕዝቡ ታሪኩንና ማንነቱን በውል የሚረዳበት የአርኪዎሎጂ ሙዚየም በአሁኑ የባንክ ክበብ ተቀቋመ፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ሥራ ይበልጥ ትኩረት በማግኘቱ በ1958 ዓ.ም. ተጠሪነቱ ለጽሕፈት ሚኒስቴር ሆኖ የታሪካዊ ቅርሶች አስተዳደር በመባል፣ በ1967 ዓ.ም. በባህል፣ የስፖርትና ወጣቶች ሚኒስቴር ስር ሆኖ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ መምሪያ በመሆን፣ በ1987 ዓ.ም. በባህልና ማስታወቂያ ሚኒስቴር ስር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ድርጅት ተብሎ ሲሠራ ቆይቶ ድርጅቱ እያደገ በመምጣቱ በ1992 ዓ.ም. ወደ ባለሥልጣን ደረጃ ከፍ ብሎ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ስር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ሆኖ እየሠራ ይገኛል፡፡
የባለሥልጣኑ ራዕይ'ተልዕኮ 'ዕሴቶችና ዓላማ
ራዕይ
ቅርሶች ተጠብቀው በሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ዘላቂነት ያለው አስተዋፅኦ ኖሯቸው ማየት፡፡
ተልዕኮ
የሀገሪቱን ቅርሶች አጥንቶ፣ አሰሳስቦ፣ አደራጅቶና ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለÒ ለጥናትና ምርምር አገልግሎት እንዲውሉና ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እገዛ እንዲያደርጉ ማስቻል፡፡
ዓላማ
ቅርሶችን ማግኘት፣ ማሰባሰብ፣ ከአደጋ ጠብቆ የታሪክ ምስክርነታቸውንና እሴቶቻቸውን (values) መዝግቦና አጥንቶ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ፣ ለዘላቂ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት አስተዋፅኦ የሚያደርጉበትና የሚውሉበትን መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡
ዕሴቶች
ቅርሶች የማንነታችን መገለጫ መተኪያ የሌላቸው የሕዝብ ሀብቶች፣ የልማትና የእድገት መሠረቶች፣ የዕውቀት ምንጮችና ክቡር ናቸው፡፡