“የገዳ-ሥርዓት”በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ /UNESCO/ በዓለም ቅርስነት ተመዘገበ.

News

በመዲናችን በአዲስ አበባ ከህዳር 19 እስከ 23 ቀን 2009 ዓ.ም በመካሔድ ላይ ባለው  11ኛ የዩኔስኮ  ጉባዔ ለውሳኔ ከቀረቡት 37 (ሠላሳ  ሰባት) ባሕላዊ ቅርሶች መካከል የኦሮሞ ብሔር ባህላዊ አገር በቀል የዲሞክራሲ ሥርዓት የሆነው “የገዳ-ሥርዓት” በዓለም የሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት “የገዳ-ሥርዓት” የ2ዐዐ3ቱን የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ዓለም አቀፍ ሰምምነት አምስቱንም የመመዘኛ መስፈርቶች አሟልቶ በመገኘቱ አባል አገሮች ውይይት ካደረጉበት በኋላ ህዳር 21 ቀን 2ዐዐ9 ዓ.ም. በፋይል ቁጥር /01164/ ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡

በየነ-መንግሥታዊ ኮሚቴው በዚሁ ጉባዔ አምስተኛ ቀን ውሎው  የ“ገዳ-ሥርዓት”ን ጨምሮ የ26 ሃገራትን ባህላዊ እሴቶች በሰው ልጆች የማይዳሰሱ ወካይ ቅርሶች ማህደር (Representative List of Intangible Cultural Heritage of Humanity) ውስጥ ማካተቱን አስታውቋል፡፡

ስድስት አባላት ያሉትን የኢትዮጵየ ልዑካን ቡድን የሚመሩት ባህላዊ ቅርሶችን በሚመለከተው የ”ዩኔስኮ” አካል በይነ መንግሥታዊው ኮማቴ 11ኛ ጉባዔ በከተማችን በአዲስ አበባ የተካፈሉት የፌዴራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ መዓዛ ገ/መድህን ናቸው፡፡

የልዑካን ቡድኑ አባላት የ“ገዳ-ሥርዓት” የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አምስቱንም የመላኪያ መስፈርቶች የሚያሟላ የባህል እሴት ያለው መሆኑን በመድረኩ በሚገባ ተከራክሮ አሳምኖ ኮሚቴውም ተቀብሎ መመዝገቡ ታውቋል፡፡

ይኸው የልዑካን ቡድን የ“ገዳ-ሥርዓት” በወካይ ቅርስነት በዓለም ባህላዊ የቅርስ ማህደር ውስጥ በመካተቱ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደሰታ ለጉባዔው በንግግር ገልጸው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት፣ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተለይም የቅርሱ ባለቤት ለሆነው የኦሮሞ ሕዝብ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፏል፡፡

News

News


ዜናዎች ዜናዎች