29ኛው የዓለም ቱሪዝም ቀን አከባበር በአዲስ አበባ

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት /UNWTO/ በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን የሚከበረውን የዓለም ቱሪዝም ቀን /WTD/ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ37ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ29ኛ ጊዜ ”ቱሪዝም ለሁሉም - ዓለም አቀፍ ተደራሽነትን ማረጋገጥ” በሚል መሪ ቃል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በመዲናዋ በድምቀት ይከበራል፡፡

በበዓሉ ከ150 ሺህ ሕዝብ በላይ እንደሚጎበኘው የሚጠበቀውና በኤግዚቢሽን ማዕከል የሚካሄደው ዐውደ ርዕይ፣ ጥናቶች የሚቀርቡበት ሲምፖዚየም እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄዱ የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች ይፋ የሚሆኑበት መሆኑን በወጣው መርኃ ግብር ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዓሉ ከመስከረም 10-15/2009 ዓ.ም. ጀምሮ በወረዳና በክፍለ ከተማ ደረጃ ሲከበር የሚቆይ ሲሆን፣ ከብሔራዊ ክልል፣ የከተማ አስተዳደሮችና የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት መስከረም 15 ቀን 2009 ዓ.ም. 11፡00 ሰዓት በግዮን ሆቴል የበዓሉ መከበር ይፋ ይሆናል፡፡

በዓሉ የሚከበርባቸው ጊዜያት ኩነቶች ሲምፖዚየም፣ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በታሜልሶል የጥያቄና መልስ ውድድር፣ ሚስ ቱሪዝም አዲስ የምትመረጥበት የቁንጅናና የፋሽን ትርዒትና ውድድር ይገኝበታል፡፡ የከተማ አስተዳዳሩ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት እና የቤቶች ልማት እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻዎችና የአካባቢ ጉብኝት፣ የአካባቢ ጽዳት፣ የችግኝ እንክብካቤና በዝግጅቱ ሂደት ቢሮው ያከናወናቸው የከተማ ውስጥ ልማቶች መካከል የአዲስ አበባ ሙዚየም ዕድሳት፣ የቨርችዋል ቱር፣ ስእላዊ ቱሪስት ካርታ፣ የተከለሰ የጎብኚዎች መምሪያ መጽሐፍ የሚመረቁ ሲሆኑ፣ በስታዲዮም የሚካሄዱ ስፖርታዊ ውድድሮችም የበዓሉ አካል ይሆናሉ፡፡


ዜናዎች ዜናዎች