“የገዳ-ሥርዓት”በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበበት 1ኛ ዓመት እየተከበረ ነው፡፡

“የገዳ-ሥርዓት”በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበበት 1ኛ ዓመት እየተከበረ ነው፡፡

ህዳር 23/2010 ዓ.ም የኦሮሞ ብሔር እንደሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ለህልውናው ሲል በሚያከናውነው ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችና ማኅበራዊ ግንኙነቶች እንዲሁም ከአካባቢውና ከተፈጥሮ ጋር በሚያደርጋቸው መስተጋብሮች የፈጠራቸው፣ አሁንም እየፈጠራቸው የሚገኙና የማንነቱ መገለጫ የሆኑ አያሌ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት ነው፡፡ ከነዚህ ቅርሶች በግምባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የገዳ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ሲሆን ይህ ሀገረሰባዊ የአስተዳደር ተጠቃሽ ነው፡፡

ባለፈው ዓመት በመዲናችን በአዲስ አበባ ከህዳር 19 እስከ 23 ቀን 2009 ዓ.ም በተካሄደው  11ኛ የዩኔስኮ  ጉባዔ ለውሳኔ ከቀረቡት 37 ባሕላዊ ቅርሶች መካከል የኦሮሞ ብሔር ባህላዊ አገር በቀል የዲሞክራሲ ሥርዓት የሆነው “የገዳ-ሥርዓት” በዓለም የሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት መመዝገቡ የሚታወስ ነው፡፡

ቅርሱ የተመዘገበበትን 1ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከህዳር 22-23 2010 ዓ.ም ድረስ በሚዘልቅ መርሃ ግብር እየተከበረ ይገናል፡፡ ህዳር 22 ቀን 2010 ዓ.ም በኦሮሞ የባህል፤ ማዕከል አዳራሽ በተጀመረው ክብረ በዓል ላይ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳዳር ክቡር አቶ ለማ መገርሳ፣ የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም፣ የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ  ወ/ሮ ሎሚ በዶ እንዲሁም የገዳ አባቶች እና የሃገር ሽማግሌዎች በክብር የታደሙበት ነበር፡፡ በገዳ አባቶች ቡራኬ የተጀመረው መድረኩ በክብር እንግዳዋ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ 

በንግግራቸው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ህዝቦቿ ብዙ ሆነው እንደ አንድ አንድ ሆነው እንደ ብዙ የኖሩባት ለዘመናት ድንበሯን ከወራሪ ጠላት በጋራ አስከብረው የኖሩባት እነሱ በሰሩት ገድል ዛሬ ለምንገኝ ልጆቿ ብቻ ሳይሆን ለመላ ጥቁር ህዝቦች የኩራት ምንጭ የሆኑ ታሪካዊ ድሎችን አስመዝግበው ሁላችንም በኩራት አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ ያደረጉ ልጆች መኖሪያ፣ ያኩሪ ታሪክና የባህል አምባ መገኛ ናት፤ ለዚህ ፍቅርና መተሳሰብ ጀግንነትና ድል አድራጊነት መሰረቱ ከቀደምት አባቶቻችን የወረስናቸውና በጽኑ መሰረት ላይ የተተከሉ አኩሪ ባህላዊ እሴቶቻችን ናቸው፡፡

ቀደምት አባቶቻችን እና እናቶቻችን ከነሱ በፊት ከነበሩት ጠቢባን ወገኖቻችን ተረክበው ለዚህ ትውልድ ካደረሷቸው አስደናቂና ለኩራታችን ምንጭ ከሆኑ ባህላዊ እሴቶች አንዱና ዋነኛው የኦሮሞ ገዳ ስርዓት ነው፡፡ ዛሬ ላይ የዲሞክራሲ  አድራጊ ፈጣሪ ተደርገው የሚቆጠሩ ሀገሮች በዓለም ካርታ እንኳን የት እንደነበሩ ሳይታወቅ የኛዎቹ የኦሮሞ አባቶቻችን እና እናቶቻችን የዲሞክራሲ ስርዓት ፈጥረውና ከነሙሉ ለዛው ይዘው ቆይተውናል፡፡ ይህን ስርዓት በዘመን ውጣ ውረድ ሳይበረዝና ሳይከለስ አሁን ለላነው ትውልድ ብክብርና በኩራት ተላልፎልናል፡፡

ቅርሱ ከኛም አልፎ ለዓለም ጠቃሚ መሆኑ ስለተረጋገጠ የዓለም ቅርስ ሆኖ ለመመዝገብ በቅቷል፡፡ የገዳ ስርዓት በዓለም ቅርስነት ሊመዘገብ የቻለው የሚገባው፣ የሚመጥንና የሚመዝን ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ ይህ ሊያኮራን ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ ኩራት እራት አይሆንም እንደሚባለው ቅርሱን በማስመዝገብ ብቻ ረክተንና ኮርተን መቀመጥ የለብንም፡፡ ይልቁንም ይህንን የኦሮሞ እናቶችና አባቶቻችን ያስቀመጡልንን ባህላዊ ስርዓት ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ፋይዳው እንዲጎለብት አቅደንና አልመን መስራት ይገባናል፡፡ የገዳ ስርዓት ቁሳዊ ቅርሶችና ሌሎች ትውፊታዊ ቅርሶች ከትውልድ ወደ ትውልድ በሙዚየምና በባህል ማዕከላት በምስልና በድምፅ ተቀምጠው እንዲጠበቁ በማድረግ መጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ እንዲያስገኙ ማድረግ ይገባል፡፡

ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር ለገፅታ ግንባታና ለእኛነታችን መገለጫ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ይህንን የማይዳሰስ መስህብ ለአገራችን ህዝቦችም ሆነ ለዓለም ለማስተዋወቅ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በታቀደና መንገድ እንደ አንድ ቁልፍ ፕሮጀክት ይዘን መስራት ይኖርብናል፡፡

በቀጣይም አገራችንን ለመገንባት በምናደርገው ጥረት እንዚህን ወሳኝ እሴቶች እንደ አመሀ በመያዝ ልንጠቀምባቸው ይገባናል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች  የማንነት መገለጫ የሆኑ እሴቶቻቸው እንዲጠኑ፣ እንዲበለፅጉና ተጠብቀው ለቀጣይ ትውልድ እንዲሸጋገሩ የማድረግ ተልዕኮ ወስዶ የሚሰራ በመሆኑ የገዳን ስርዓትን ጨምሮ ሌሎች በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ መስህቦቻችንን የመጠበቅና የመንከባከብ ስራ ይሰራል፡፡  በመሆኑም በሁሉም ክልሎች የሚገኙ መስህቦችን ለማጥናትና እንዲጠበቁ ለማድረግ ስራዎችን እየሰራ በመሆኑ ሁሉም አካላት የስራው አካል በመሆን እንዲንቀሳቀስ ጥሪያቸውን በማስተላለፍ የገዳ ስርዓትን ጨምሮ የኦሮሞ ህዝብ ባህላዊ ሀብቶችን ለመጠበቅ በሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዘግጁ መሆኑን በመግለፅ መድረኩን በይፋ አስጀምረዋል፡፡

በመቀጠል በክብረ በዓሉ መርሃ ግብር መሰረት ቀኑን በማስመልከት የተዘጋጁ ወረቆች የቀረቡ ሲሆን የገዳ ስርዓት ታሪካዊ አመጣጥ፣ ባህላዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ማህበራዊ እና ስለ ፖለቲካዊ ፋይዳውና አወቃቀሩ፣ ስለ ቅርሱ በዓለም አመዘጋገብ፣ በቀጣይ ቅርሱን ለመጠበቅ፣ ለማስተዋወቅ፣ እና ተፈጠሯዊ ይዘቱን ሳይለቅ ለማስቀጠል ምን መደረግ አለበት በሚሉ ርዕሰ ጉዳች  ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸው በክቡር በአቶ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ማጠቃለያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ክቡር ርዕሰ መስተዳደሩ በማጠቃለያቸው  ይህን ነባር የኦሮሞ ህዝብ መገለጫ የሆነውን የገዳ ስርዓ-ይበልጥ ለማስተዋቅ የመስህቡ ባለቤቶች እኛው እራሳችን በደንብ በማወቅና አማባሳደር በመሆን ልናስተዋውቅ ይገባል ብለዋል፡፡ አከባበሩ ዛሬም በልዩ ልዩ መርሃ ግብር እንደሚቀጥል በመግለፅ መድረኩ ተጠናቋል፡፡

 


ዜናዎች ዜናዎች