የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰርከስ ጥምረት ተመሰረተ

በሀገራችን በተበታተነ መልኩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሰርከስ ቡድን አባላት መስከረም 19/2013 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መሰብሰቢያ አዳራሽ ባካሄዱት የምስረታ ጠቅላላ ጉባዔ "የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰርከስ ጥምረት" በሚል ስያሜ የአንድነት ማህበር መሠረቱ፡፡
የጥምረቱ አባላት በእስካሁኑ እንቅስቃሴያቸው የሀገራችንን ባህልና መልካም ገፅታ በመላው ዓለም ሲያስተዋውቁ እንደቆዩና ዓለም አቀፍ ዝና ማግኘታቸውን በማስታወስ አሁንም በበለጠ በመሥራት ውጤት ለማስመዝገብ መዘጋጀታቸውን፣ ኢትዮጵያ በሰርከስ ጥበብ ተመራጭና ተፎካካሪ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ እንደምትሆን በማመን ተግቶ ለመስራት የአንድነት ማህበር የመሠረቱበት ወሳኝ ወቅት ላይ መሆናቸውንና በጋራ ራዕይ መንቀሳቀሱ በተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው መሆኑን ነው የተገለጸው፡፡
በተለይ የሰርከስ ጥበብ በአካላዊ እንቅስቃሴው ብቻ ሳይሆን አዕምሯዊ ዝግጁነትና ብቃት ጋር የሚያያዝ እንደመሆኑ ከመዝናኛ ስፖርት ጎን ለጎን እያደገ የመጣ፣ የግልና የቡድን እንቅስቃሴ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሰርከስ ጥበብ በወጣቶችና ሴቶች ወይም በሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለማዳ በሆኑ የቤትና የዱር እንስሳትም ጭምር እየተዘወተረና እየተስፋፋ የመጣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በመሆኑ የጥምረቱ መኖር እነዚህንም ተሞክሮች ለማስፋት ይጠቅማል፡፡
ስለሆነም በተበታተነ መልኩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሰርከስ ቡድን አባላት በመመሰረቱት የአንድነት ጥምረት ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው በቡድንም ሆነ በተናጠል የሚያደረጉ እንቅስቃሴዎች ለጋራ ልማት በማዋል በአርአያት ወደ ላቀ ደረጃ ለመሸጋገር መታሰቡን የመመስረቻ ሰነዱ ይጠቁማል፡፡
በጉባኤው የመመስረቻ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ከተደረገ በኋላ በማጽደቅ ጥምረቱን የሚመሩ ሰባት አባላት ያሉት አመራሮች በመምረጥ ያጠናቀቀ ሲሆን፣
በዚሁ መሠረት፡-
1. አቶ ተክሉ አሻግር ነበበ ፕሬዝዳንት
2. አቶ የኔነህ ተስፋዬ ም/ፕሬዚዳንት
3. ወ/ት ውዴ ዘለቀ ፀሃፊ
4. አቶ በሃይሉ ዮሴፍ የሂሳብ ሹም
5. አቶ አንዋር አሚን ገንዘብ ያዥ
6. አቶ ክብሮም በርሃ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ
7. አቶ ተስፋሁን መርጊያ የፕሮጀክት ሃላፊ በመሆን በጉባኤው ተመርጠዋል፡፡
የጥምረቱ ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ተክሉ አሻግር በዕለቱ ያስተላለፉት መልዕክት "ይህንን ማህበር የመሠረትነው በተቀናጀ መንገድ ለመንቀሳቀስ እንዲረዳን ነው፡፡ በሰርከስ ጥበብ እንቅስቃሴያችን የተባበረ አቅም፣ ትብብርና ድጋፍ ለማግኘት ይጠቅመናል ነው ያሉት፡፡ የአገራችንን ባህልና መልካም ገፅታ በመላው ዓለም እያስተዋወቅን ባለነው አቅምም ልምዳችንን አሳድገን ለበለጠ መንቀሳቀስ እንድንችል ያግዘናል" ብለዋል፡፡
አያይዘውም ፕሬዝዳንቱ የሰርከስ ጥበብ ዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭና ተፎካካሪ የኪነ -ጥበብ ዘርፍ እንዲሆን አጠናክረን እንሠራለን ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዘርፉን ሪፎርም በማድረግ በሀገር ውስጥ ሆነም በዓለም አቀፍ ደረጃ መልካም ዝናና ተሞክሮዎቻችንን እያሰፋን ስራዎቻችንን በማስፋፋት ለሰርከስ ጥበብ ዘርፉ የብልፅግና ጉዞ ስኬት እጅ ለእጅ ተያይዘን መንቀሳቀስ ይኖርብናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
በጥምረቱ የምስረታ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በመገኘት የተሳተፉት 5 ክልሎች እና 2 የከተማ አስተዳደሮች መሆናቸው ታውቋል፡፡

ዜናዎች ዜናዎች