የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ካሳው በሙዳይ በጎ አድራጎት ተገኝተው የትንሳኤ ማዕድ ማጋራት ፕሮግራም ጎበኙ፡፡

በዛሬው ዕለት የትንሳኤ በዓል ሲከበር የሀዋሳው ኦሲስ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለቤት አቶ ብርሃን ተድላ ኮተቤ አካባቢ በሚገኘው ሙዳይ የበጎ አድራጎት ድርጅት ምሳ አብልተዋል፡፡ አቶ ብርሃን በዝግጅቱ ላይ እንደተናገሩት ወ/ሮ ሙዳይ ከአስራ ሶስት አመታት በላይ ለድሆች ያለመታከት እያደረገችው ያለችው ነገር እኛ ለአንድ ቀን ከምናደርገው ጋር ፈፅሞ የሚነፃፀር አይደለም ብለዋል፡፡ ዛሬ በዓሉን አስመልክቶ ከተደረገው የማዕድ ማጋራት ባለፈም ድርጅቱ በርካታ ችግሮች ያሉበት እንደመሆኑ ተጨማሪ ድጋፎችን ለማድረግ መታሰበቡን ተናግረዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ህፃናቱ የመኝታ ችግር ያለባውቸውና በአንድ ክፍል ውስጥ በብዛት መሬት ላይ አንጥፈው የሚተኙ በመሆኑ አቶ ብርሃን በግላቸው አስር ተደራራቢ አልጋዎችን ለማሰራት ቃል ገብተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሆቴል አሰሪዎች ማህበርም በተመሳሳይ ሌሎች አስር አልጋዎችን ለማሰራት ቃል የገባ ሲሆን የኢትዮጵያ አስጎብኝዎች ማህበርም እንዲሁ አስራ ሶስት ተደራራቢ አልጋዎችን ለማሰራት ቃል ገብተዋል፡፡


በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ክብርት ዶ/ር ሂሩት ካሳው የድርጅቱ መስራች የሆነችውን ወ/ሮ ሙዳይ እያደረገች ላለው በጎ ተግባር ካመሰገኑ በኋላ እሳቸውም ወደፊት ለድርጅቱ አስፈላጊ ድጋፎችን በማስተባበር እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡
እቴቴ ወተት በበኩሉ ለህፃናቱ በሳምንት ሁለት ጊዜ ወተት በነፃ ለማቅረብ ቃል ገብቷል፡፡ ወደፊት በርካታ የሆቴል ባለሀብቶችና አስጎብኝ ድርጅችን በማስተባባር ከዚህም በላይ ቋሚ ድጋፎችን ለማድረግ ጥረቶች መጀመራቸውን አቶ ብርሃን ገልፀዋል፡፡


ሙዳይ የበጎ አድራጎት ድርጅት ስራውን ለማከናውን የሚያስችለው በቂ ቦታ ስለሌለው ካሁን በፊት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቦታ ጥያቄ አቅርቦ አምስት ሽህ ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጠው ተወስኖ የነበረ ቢሆንም እስካሁን አለመፈፀሙን ወ/ሮ ሙዳይ ገልፀው ከተማ አስተዳደሩም ሆነ ክቡር ከንቲባው ይህ ጉዳይ እዲፈፀም እንዲረዷቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል ጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ፊት ላይ ለተሰለፉ ሙያተኞችና ድጋፍ ለሚፈልጉ ወገኖች የማዕድ ማጋራት ፕሮግራም በማካሄድ ምሳ በነፃ አብልተዋል፡፡ የሆቴሉ ባለቤት አቶ ቢኒያም ብስራት እንዳሉት በአራት የተለያዩ ቦታዎች 120 የጁፒተር ሆቴል ልዩ አገልግሎችን በማዕድነት አቅርበዋል፡፡


ዜናዎች ዜናዎች