የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከአስጎብኝ ባለሙያዎች ጋር በኮቪድ ፕሮቶኮል እና የአስጎብኝ ባለሙያዎችን የተመለከተ ረቂቅ መመሪያ ዙሪያ ምክክር አደረገ

ጥቅምት 05/2013 ዓም
አዲስ አበባ ፤
በኮቪድ 19 ቫይረስ ምክንያት በሀገራችን ተቋርጦ የነበረውን የቱሪዝም አገልግሎት እንደገና ለማስጀመር ለአስጎብኝ ባለሙያዎች የኮቪድ ፕሮቶኮል ሰነድ ቀርቦ ምክክር ተካሂዷል። ከተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ ጋር በማጣጣም የተዘጋጀውን የኮቪድ ፕሮቶኮል አስጎብኝ ባለሙያዎች በማስጎብኘት አገልግሎት ወቅት ሊከተሉት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
በዕለቱ ተገኝተው ስልጠናውን የሰጡት የዓለም አቅፍ ቱሪዝም ፋሲሊቴሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደርበው፡- " የፕሮቶኮሉ ዓላማ የራሳችንን እና የቱሪስቱን ደህንነት በመጠበቅ የቱሪስት አገልግሎት ስራውን ማስጀመር ነው፡፡" በማለት ተናግረዋል።
የሀገራችንን ገፅታ እንደገና በመገንባት የተዳከመውን የቱሪስት አገልግሎት ማስጀመሪያ ጊዜው አሁን ስለሆነ፤ በዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የኮቪድ ፕሮቶኮል ላይ በተቀመጠው መሰረት አገልግሎቱን ማሳለጥ እንደሚገባ በመድረኩ ተገልጿል ።
በሌላ በኩል የአስጎብኝ ባለሙያዎችን የተመለከተ ረቂቅ መመሪያ ላይ ከአስጎብኝ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ ረቂቅ መመሪያው ግብዓት የሚሰበሰብበት እንጅ ያለቀለት ባለመሆኑ ከአስጎብኝ ባለሙያዎች ሀሳብ፣ አስተያዬት እና ጥያቄ የተነሳበት ሲሆን በአቶ ዳንኤል ዓባይነህ ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡


ዜናዎች ዜናዎች