የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ዘርፍ አመታዊ የሴክተር ጉባኤ እየተካሄደ ነው፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ክብርት ዶ/ር ሂሩት ካሳው ባስተላለፉት መልዕክት ወቅቱ አገራችን የሚያጋጥሟትን ዙሪያመለስ ፈተናዎች እየተጋፈጠች የህዝቦቿን ብልፅግና ዕውን ለማድረግ ከመቸውም ጊዜ በላይ ርብርብ የምታደርግበት ነው ያሉ ሲሆን በዚህ ሂደት የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ዘርፉ የሀገር ብልፅግናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና ከሚጫወቱ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስና ሚናውንም እየተወጣ የሚገኝ፤ በመንግስትም የተለዬ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አንስተዋል፡፡ ዘርፉ ለሀገራችን ብልፅግና ያለውን የማይተካ ሚና ጠንቅቆ የተረዳው መንግስት በቅርሶች ጥበቃና ልማት፣ በቋንቋ ልማት፣ በኪነጥበብና ስነጥበብ ኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ በአዳዲስና ነባር መስህብና መዳረሻዎች ልማት፣ በመስተንግዶ ተቋማት ልማት፣ በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ልማት፣ በሰው ሃብት ልማትና በመሰል ቁልፍ ጉዳዮች ዙሪያ ሊዳሰሱና ሊጨበጡ የሚችሉ ተስፋን የሚያለመልሙ ሥራዎችን በመስራት ላይ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡ ይህ ደግሞ በተለይም በዚህ ዘርፍ ውስጥ ኃላፊነት ይዘን ለምንሰራ አካላት በየአቅጣጫው የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች በልዩ መሰጠትና በትጋት በማሸነፍ የየራሳችንን አሻራዎች እንድናስቀምጥ የሚያበረታታና እድል የሚሰጥ በመሆኑና ይህንንም በተጨባጭ እየተመለከትን በመሆኑ ኩራትንና መነሳሳትን ይፈጥርልናል ብለዋል፡፡


ክብርት ሚኒስትሯ የጠራ ዕቅድ ማቀድ የስራዎቻችን ግማሽ መፈፀም ነው ካሉ በኋላ ባሳለፍነው የ2012 በጀት ዘመን የሴክተሩን ዓመታዊ ዕቅድ በተቻለ መጠን በሁሉም ባለድርሻ ተሳትፎ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ የተገባ ቢሆንም የተከሰተው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ዕቅዶቹ በታሰበው መልኩ መሳካት እንዳይችሉ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡ ወረርሽኙ ከዚህ ሴክተር የበለጠ ጉዳት ያደረሰበት አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት ዘርፎች የኮቪድ-19 ማገገሚያ ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱንና አመራሮች ለማገገሚያ ስትራቴጂዎቹ ዕውን መሆን ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡

በዚህ ፈታኝ ጊዜ ውስጥ ከተከናወኑ ወሳኝ ተግባራት ውስጥ አንዱ የቀጣይ አስር ዓመታት(ከ2013 እስከ 2022) በጀት ዘመን የሚተገበር የሴክተር ልማት ዕቅድ መዘጋጀት ነው ያሉት ሚኒስትሯ የ2013 በጀት ዘመን ዕቅድም ከአስር ዓመቱ ዕቅድ የሚቀዳ እንደመሆኑ በተለይ ለቀጣይ አስር ዓመታት ጉዞአችን እንዲመች አሳሪ የሆኑ ከአሰራር፣ ከአደረጃጀትና ከሰው ሃብት የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ግንባታ ጋር የተያያዙ ፖሊሲዎችን እንዲሁም መሰል የህግ ማዕቀፋትን ለምናጎለብትበት ሥራ ልዩ ትኩረት በመስጠት የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ባስተላለፉት መልዕክት በዚህ የታሪክ አጋጣሚ የዘርፉ አመራር ሆነን የምንገኝ አካላት በንፁህ ልቡና፣ በአገራዊ ፍቅርና በትጋት ዕቅዶቻችንን ተፈጻሚ በማድረግ ህዝባችንን ብሎም አገራችንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ አንስራ ብለዋል፡፡
በመቀጠልም የ2012 በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ከ2013 በጀት ዓመት እቅድ ጋር በተከታታይ ለውይይት በመቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡