ባለ ፍል ውሃው ቤተ መንግስት ኤረር......
በ19 60 ዓ.ም በቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ እንደተገነባ የሚነገርለት ከአዲስ አበባ 602 ኪ.ሜ ርቀት በሱማሌ ክልላዊ መንግስት በኤረር ወረዳ የሚገኘው የኤረር ቤተ መንግስት ሶስት ህንፃዎች ያሉት ሲሆን የንጉሱን መዝናኛ፣ ምኝታ ቤት፣የአንበሳ ቤት፣የፍል ውሃ መታጠቢያ ክፍሎች ፣መጋዝኖች እና የሰራተኞች መኖሪያ ቤት የሚያካትት ነው።
የኤረር ቤተ መንግስት ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ በሀገሪቱ ካስገነቧቸው ቤተ መንግስቶች ለየት ያለ ነው። ንጉሱም በየ 3 ወር ኤረር ድረስ በባቡር በመምጣት ወደ ቤተ መንግሥቱ በንጉሱ መኪኖች እንደሚገቡ የአከባቢው ሽማግሌዎች ይናገራሉ።
ቤተ መንግሥቱ በውሃ የሚሰራ አነስተኛ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ የነበረው ሲሆን በዙርያውም ሰባት አይነት የውሃ አይነቶች ይገኙበታል። ከእነዚህ ውስጥ ፍል ውሃ እና ጥቁር ውሃ/የሚረጋ ውሃ/ ይገኙበታል።
የኤረር ቤተ መንግስት ልዩ ስጦታ የሆነው ፍል ውሃ በሀገራችን ካሉ ፍል ውሃዎች የሚለይበት ለሁሉም የሰውነት ክፍሎች ማለትም ከአንገት በላይ/እስቲም/፣ከጉልበት በታች፣ከወገብ በታች እንዲሁም ሙሉ የሰውነት ክፍል የሚታጠቡበት ለየብቻ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች ያሉት በመሆኑ ነው። በአሁኑ ጊዜ ፍል ውሃው በጥሩ ሁኔታ በነፃ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ፍል ውሃውን የአከባቢው ማህበረሰብ እና ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ለመድሀኒትነት ይጠቀሙበታል።
የኤረር ቤተ መንግስት በ2008 ዓ.ም በ4 ሚሊዮን ብር እድሳት ቢደረግለትም ቅርሱን የማስተዋወቅ ስራ ስላልተሰራለት ቤተ መንግስቱን ጎብኝዎች እንደማይጎበኙት የአከባቢው ነዎሪዎች ይናገራሉ።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመሆን በቀጣይ መስከረም ወር በክልሉ የሚከበረውን የዓለም የቱሪዝም ቀን በማስመልከት መዳረሻዎችን ከመገናኛ ብዙኅን ጋር በመጎብኘት የሚገኝ ሲሆን የኤረር ቤተ መንግስት አንዱ በመሆኑ መዳረሻው ያለበትን ችግር በመለየት ችግሮችን በመቅረፍ የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ አስታውቋል። ዘንድሮ በክልሉ የሚከበረው የዓለም የቱሪዝም ቀን ክልሉ ያሉትን የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዎወቅ እንደሚረዳም ተነግሯል።
የሱማሌ ክልላዊ መንግስት በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎቹ የሚገኙበት ክልል ሲሆን በቀጣይ መዳረሻዎቹ በተገቢው ለምተው የማስተዋወቅ ስራ ከተሰራባቸው ሱማሌ ክልል ሌላኛዎ የምስራቅ ኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻ የምትሆንበት ቀን እሩቅ አይሆንም።
ዜናዎች
- የእንጦጦ ፓርክ በይፋ ተመረቀ
- ቱሪዝም ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የቱሪዝም መለያ ብራንድ የማስተዋወቅ ስልጠና ሰጠ፡፡
- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰርከስ ጥምረት ተመሰረተ
- የጎብኝዎች የደህንነት መጠበቂያ ፕሮቶኮል በተመለከተ ለሼፍ ማህበራት ስልጠና ተሰጠ።
- በሀገራችን የመጀመሪያው የማደጎ ዛፍ ተከላ ፕሮጀክት በላሊበላ ተጀመረ
- በአይነቱ ልዩ የሆነ የእጽዋት ዓለም ፕሮጀክት በቅዱስ ላሊበላ የቱሪስት መዳረሻ ይፋ ሆነ፡፡
- የብርቅዬ ባህላዊ የመድኃኒት ዕጽዋት ችግኞች ተከላ ተካሄደ፡፡
- የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ዘርፍ አመታዊ የሴክተር ጉባኤ እየተካሄደ ነው፡፡
- ‹‹የኢትዮጵያ ቱሪዝም አጀንዳ!!›› በሚል የተዘጋጀው የቀጣይ አስር ዓመቱ የቱሪዝም ዘርፍ ዕቅድ ለፌደራል ባለድርሻ አካላት ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል፡፡