ዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን በደቡብ ብ/ብ/ሰቦችና ህዝቦች ክልል በዲላ ከተማ ተከበረ

ዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን
በደቡብ ብ/ብ/ሰቦችና ህዝቦች ክልል
በዲላ ከተማ ተከበረ
 
 

፳፩ኛው ዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን በሐገራችን ለ፰ኛ ጊዜ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ዲላ ከተማ ህዳር ፲፭ና ፲፮ በህብረ-ብሔራዊነት የደመቁ የመቻቻል ዕሴቶቻችን ለዘላቂ ሰላማችን በሚል መሪ ቃል በህዝባዊ ንቅናቄ ተከበረ፡፡የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና ባህል ዕሴቶች ዳይሬክቶሬት፣ከዲላ ዩኒቨርሲቲ፣ከደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ከዲላ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር በጋራ መሆኑን አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው የቋንቋና ባህል ዕሴቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ገልፀዋል፡፡

ህዳር ፲፭ ቀን ማለዳ በዲላይት ሆቴል ፊት ለፊት  የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መዋቅር ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላትና የሚዲያ ባለሙያዎች በመሰባሰብ የደቡብ ክልል ፖሊስ ማርች ባንድ ለኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ረመዳን አሸናፊና እንግዶች የክብር አቀባበል ሰላምታ በመስጠት ህዝባዊ ንቅናቄውን በደማቅ ሃገራዊ ጣዕመ-ዜማ እየመራ ሶስት ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ የተደረገ ሲሆን በዲላ ከተማ መናኸሪያ በተዘጋጀ ህዝባዊ መድረክ መነባንብና በሃገር ሽማግሌዎች ምርቃት የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ተደርጎአል፡፡

የጌዴዖ ዞን አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ የደ/ብ/ብ/ሕ/መ/ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ የመክፈቻ ንግግር አድርገው የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ረመዳን አሸናፊ ንግግር እንዲያደርጉ ጋብዘዋል፡፡

ክቡር አቶ ረመዳንም በንግግራቸው በዓሉ በመላው አገሪቱ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በሲምፖዚየምና በህዝባዊ ንቅናቄ የሚከበር ነው፤ ካሉ በኋላ መቻቻል ከሌለ ሠላም የለም  ሠላም ከሌለ ልማትና ዕድገት ሊኖሩ አይችሉም ፤ ስለዚህም ቅድመ- አያቶቻችን ያቆዩልንን ተከባብሮ አብሮ የመኖር ባህል ሳይሸረሸር እንዲቀጥል ሌት ተቀን ሁላችንም ልንሰራ ይገባል፡፡

ብዝሃነትን በመቀበል አንድነታችን በማጠናከር በማንግባባቸው ጉዳዮቻችን ዙሪያ በሰከነ ትዕግሥትና አርቆ በማሰብ መነጋገርና ሠላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት እንደሚቻል አምነን በተደራጀ መልኩ መሥራት እንዳለብን አበክሬ እየገለፅሁ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጭምር አሳስባለሁ ብለዋል፡፡

በመቀጠልም ባህላዊ ጨዋታ በዞኑ ያገር ሽማግሌዎችና በዲላ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል  አባላት ኢትዮጵያንና ህብረ-ብሄራዊነትን የሚያጎሉ ሙዚቃዊ ድራማ ለታዳሚው ህዝብ አቅርበዋል፡፡

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ለዚህ ዝግጅት መሳካት ላደረገው ጥረትና እንቅስቃሴው የሚመሰገን ነው፡፡ ነገር ግን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራው ቀጣይነት እንዲኖረው ዩኒቨርሲቲው በዚህ መነቃቃት መበረታታት አለበት፤ የሚል አስተያየት ከታዳምያኑ ተሠንዝሯል፡፡

ከሰዓት በኋላ በአካባቢው አጠራር ቱም ቲቻ በተባለው ሠንሰለታማ ተራራ ዙሪያ ገባ በተደረገው ጉብኝት የዲላን ተፈጥሯዊ የመልክዐ ምድር አቀማመጥ በማየት መርካት ወይ መደሰት ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮ በዝምታና በአርምሞ የምታስተላልፈው መልዕክት እንዳለ መረዳት አይከብድም

በሁለተኛው ቀን በዩኒቨርሲቲው አዳራሽ በተዘጋጀ ሲምፖዚየም ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቃል-ኪዳን የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግር በማድረግ ክቡር ሚኒስትሩ ጉባኤውን እንዲከፍቱ ጋብዘው በፌደራሊዝምና በመቻቻል ዙሪያ ሁለት ምሁራንን ጋብዘው ዶ/ር አሰፋ ፍስሃና ዶ/ር ዳኛቸው ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፎች ላይ በመመስረት ለተነሱ ሃሳቦችና ጥያቄዎች አወያዩ ዶ/ር ቃል-ኪዳን ለምሳሌ አሉ ባደረግነው ጉብኝት ላይ አንዳንዱ ሰው ከሲምፖዚየሙ ጋር ምን አገናኘው?   ምን ዓየን ? ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፤ የተፈጥሮን ፊደል የማያነብ፤አካባቢውን ቶሎ የማይረዳ፤ የጉብኝቱ ዓላማ ግን አሉ ዶ/ሩ ዕፅዋቱና አትክልቱ ከእንስሳቱና ከነፍሳቱ ጋር ተቻችለው መኖር እንደቻሉ እንድናይ  ነው፡፡

ዕፅዋቱ አንዱ ላንዱ ጥላ፣ ከለላ፣ ቤቱ፣ ውበቱ ሆኖ እንጂ በዓይነት በመጠን በመደብ ሲጣሉ አናይም፤ አንዱ ሌላውን ሲያጠፋ፣ ሲያደርቅ አልታየምና በጌዴዖ ምድር ዙሪያ እስከ ዛሬ ለምለምና አረንጓዴ እንጂ መጠውለግ እንኳ አይታይባቸውም፡፡ እኛስ ከዕፅዋቱ ምን እንማራለን? ሲሉ የጉብኝቱን ዓላማ በጥያቄ መልክ በማቅረብ ለዛ ባለው አነጋገር ገልፀውታል፡፡


ዜናዎች ዜናዎች