የ2008 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ በአገራችን ለ6ኛ ጊዜ በድሬዳዋ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ፡፡

የ2008 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ በአገራችን ለ6ኛ ጊዜ “በብዝሃነት የፈጠርናቸው የመቻቻል እሴቶች ለልማታችን!” በሚል መሪ ቃል በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሲንፖዚየም፣ በጉብኝት እንዲሁም በተለያዩ የንቅናቄ ተግባራት ከህዳር 6 /2008ዓ.ም እስከ ህዳር 9/ 2008 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ ተከበረ፡፡

Newsየዓለም መቻቻል ቀን አከባበር ታሪካዊ ዳራ የሚጀምረው እ.ኤ.አ በ1995 የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት November 16 ዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን ሆኖ እንዲከበር ለአባል አገራቱ ውሳኔውን ባስተላለፈበት ወቅት እንደነበር ይታወሳል፡፡

አገራችንም የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት አባል ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ቀኑን በድምቀት ስታከብር ቆይታለች፡፡ የመቻቻል ቀን የሚከበርበት ዋና ዓላማ በዓለም ላይ የሚገኙ ህዝቦች አንዱን ከሌላው በዘር፣ በቀለምና በሃይማኖት ሳይነጣጠሉ በመተሳሰብና በአብሮነት እንዲኖሩ አላማ በማድረግ ነው፡፡

በፕሮግራሙ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልጀባር አብዱሰመድ እንደገለጹት የአገራችን ህዝቦች ለዘመናት ይዘውት የኖሩትን የመቻቻል ባህል በማጠናከር በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ እውን ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡    

 

በፕሮግራሙ ላይ በመቻቻልና ተያያዥነት ባላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ዙር ትኩረት ያደረጉ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን ከነዚህም መካከል “ሐይማኖትና መቻቻል”፤ “የጋራ የባህል እሴቶች ሚና ‘ለጋርዮሻዊ ብሔራዊ ልማት’ ማህበረሰብ የእርስ በእርስ ማህበረ- ተራክቦ ማሳያነት”፤ “ሀገር በቀል እውቀትና አብሮነት”፤ “መቻቻልን ለመስበክ” “ብዝሀነትና መቻቻል” እንዲሁም በአገራችን ስላለው የመቻቻል ባህል ታሪካዊ ዳራ አሁን ያለበት ደረጃ፣ እያበረከተ ያለው አገራዊ ፋይዳ ላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል፡፡

በምድር ባቡር ታሪክ ለአገራችን ፈር ቀዳጅና ከቀደምት የመሰረተ ልማት አውታሮች ግንባር ቀደም የሆነው (በድሬዳዋ ከተማ የሚገኘው) ታሪካዊው የኢትዮጵያ ጅቡቲ የባቡር ሀዲድ እና በዘመናዊ መንገድ በመገንባት ላይ ያለው አዲሱ የባቡር ፕሮጀክት በተሳታፊዎች ተጎብኝተዋል፡፡


News and Updates News and Updates