ብሔራዊ የሚዲያ እና የኪነ-ጥበባት ግብረ-ሃይል ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ልዩ ልዩ ተግባራት ማከናወን ጀመረ።

ኪነ ጥበብና ሚዲያን አቀናጅቶ በመጠቀም ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ስርጭትን ለመቀነስ እና በወረርሽኙ ምክንያትም የሚከሰቱ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለማህበረሰቡ ለማቅረብ ዓላማ ይዞ የተመሰረተው ግብረ ሃይሉ ወደ ስራ ገብቷል፡፡
በዚህም የተለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን በማዘጋጀትና በማቅረብ ህዝቡ እየተዝናና እራሱን፣ ቤተሰቡን እና ሀገሩን ከቫይረሱ እንዲጠብቅ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው።
እንቅስቃሴውን ውጤታማ ለማድረግ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ተቋማትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ፈጠራ የታከለበት፤ ሙያዊ ስነ ምግባርን የተከተለ፣ የቅርፅ፣ የአቀራረብ፣ የይዘት እና ግዝፈት ደረጃቸውን የጠበቁ የተለያዩ የኪነ ጥበብ ስራዎችን በሚዲያ እንዲቀርቡ ዝግጅት አድርጓል፡፡ ግብረ ሀይሉ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከኪነጥበብ ዘርፍ ሙያ ማህበራት፣ ከጤና ሚኒስቴርና ከሚዲያ አካላት በተውጣጡ ሃላፊዎች የተቋቋመ ሲሆን በሥሩም ሦስት ንኡሳን ኮሚቴዎች ተቋቁሟል፡፡
የዕይታዊ ጥበባት ንኡስ ኮሚቴ ፣ የ ትውን/ትዕይንታዊ ጥበባት ንኡስ ኮሚቴ እና የጽሑፍ ጥበባት ንኡስ ኮሚቴ ሲሆኑ በዕይታዊ ጥበባት ዶክመንተሪዎች፣ አጭጭር ፊልሞች፣ ድራማዎች፣ ማስታወቂያዎች፣ ኢንተርቪዎች፣ ስዕሎች ፣ ካርቱን ስዕሎች፣ የሙዚቃ ቪዲዮዎች፣ ግራፊክስ፣ ዲዛይን፣ ፋሽን እና ሞዴል ትዕይንቶች በትውን/ትዕይንታዊ ጥበባት ቴአትር፣ ኮሜዲ፣ ሙዚቃ፣ የሰርከስ እና ስፖርት፣ ዳንስ እና ውዝዋዜ እንዲሁም በጽሑፍ ጥበባት ስር ድርሰት፣ ግጥሞች፣ አጫጭር ወጎች፣ ልብ ወለዶች፣ ጥያቄና መልስ ውድድሮች፣ መጣጥፎች ይሰራሉ።
በግብረ ሃይሉ እስካሁን የገጣሚ ታገል ሰይፉ የሬዲዩ መልእክት፣ የፋሽን ዲዛይነሮች ስራዎችና የኮመዲያን ሥራዎች ቀርበዋል፡፡
የፊልምና ድራማ ስፖት፣ ግጥም፣ የሰርከስ፣ ሙዚቃ፣ዳንስ.. ዝግጅቶች በሂደት ላይ ናቸው።

News and Updates News and Updates