የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ከሚደርስበት ከባድ ተፅዕኖ በሚወጣበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽ የመጀመሪያ ሰለባ የሆነው የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ወደፊት ማንሰራራት እንዲችል በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች መጀመራውን የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ / ቡዜና አልከድር በዛሬው ዕለት በጉዳዩ ላይ በተሰጠ መግለጫ ገልፀዋል፡፡
በመግለጫው ላይ ሆቴሎች በአሁኑ ሰአት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ስራ በማቆም ላይ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን ይህንን ሁኔታ ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ ለማድረግ ሆቴሎች ለለይቶ ማቆያ እና መከታታያ ማዕከልነት እንዲውሉ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪ ግን በቤት ውስጥ የሚሰሩ የሰነድ ዝግጅቶች፣ የድረ-ገፅ ስልጠናዎች፣ የማስታዋወቂያና የገበያ አማራጮች ልየታና የአቅም ግንባታ ስራዎች እንደሚሰሩ መግለጫውን የሰጡት የስራ ሃላፊዎች አብራተዋል፡፡

የመግለጫዉ ዋና ዋና ሀሳቦች፡-

1. መላዉ የሀገራችን ህዝቦች -
በአሁኑ ሰዓት አለምን በሙሉ በመፈተን ላይ የሚገኘዉን የኮሮና ቫይረስ በሚመለከት ሁላችንም በፌደራል መንግስት፣ በጤና ሚኒስቴር እና በአለም የጤና ድርጅት/WHO/ በኩል እየተሰጡ ያሉ የጥንቃቄ መመሪያዎችን እንድናከብርና በጥብቅ ዲሲፕሊን እንድንፈፅም እንዲሁም በዚህ አንገብጋቢ የጋራ ጉዳይ ላይ ታላቅ ርብርብ በማድረግ ራሳችንን እና ህዝባችን ከአስከፊ ሁኔታ በመጠበቅ ወቅቱን እንድንሻገር ጥሪ ለማቅረብ እንወዳለን፡፡

2. በአሁኑ ሰዓት የኮሮና ወረርሽኝ በመላዉ አለም በሚባል ደረጃ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡ ይህ ቫይረስ በዋናነት በዋጋ ሊተመን የማይችለዉን ዉዱን የሰዉ ልጅ ህይወት በመቅጠፍ እና የሰዉን ልጅ ማንኛዉንም አይነት ጉዞ በመግታት ላይ ይገኛል፡፡ እስካሁን በታወቀዉ ይህ ችግር በከፍተኛ ደረጃ የተጋረጠባቸዉ ሀገራትም ለሀገራችን ኢትዮጵያ ዋና ቱሪስት ምንጭ /Core Markets/ የሆኑ ለምሳሌ አሜሪካ፣ ጣሊያን፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን ... በማጥቃት ላይ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ሀገራችንን በብዙ ቁጥር የሚጎበኙ ቱሪስቶች የዕድሜ ክልል ዉስጥ የሚገኙ ሰዎችን እየጎዳ ያለ መሆኑ ችግሩን ይበልጥ የባሰ እና የቱሪዝም ዘርፉን ችግር በጊዜያዊነት ብቻ ሳይሆን ረዘም ላለ ጊዜ ሊፈታተነዉ ይችላል፡፡
ስለሆነም በየክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም ተቋማት እና ብሄራዊ አስጎብኝ ድርጅቶች ይህን ተገንዝበዉ ጥናትን መሰረት በማድረግ በመላዉ ሀገራችን የሚገኙ በርካታ መስህቦችንና ልዩ ልዩ አዳዲስ አማራጭ የጉብኝት ፓኬጆችን በመቅረፅ ጊዜዉ ሲፈቅድ ወደ ነባር ገበያችን እና ሌሎች አዳዲስ የገበያ አማራጮች መግባት በምንችልበት ደረጃ ስራዎችን እንድታከናዉኑ እንገልፃለን፡፡

3. የቱሪዝም ፕሮሞሽን እና የሀገር ገፅታ ግንባታ ስራ የብዙ አካላትን የተቀናጀና የተደራጀ ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ መላዉ ህዝብ፣ በተለይም የቱሪዝሙ ማህበረሰብና ተቋማት እንዲሁም በዉጭ ሀገር የሚገኙ ትዉልደ ኢትዮጵያን የኢንተርኔት እና የማህበራዊ ድህረ-ገፆችን በመጠቀም ከኮሮና መረጃዎች መቀያየር በተጨማሪ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢ የሚገኙ ፀጋዎችን በፎቶ፣ በምስልና በድምፅ መረጃ የምንሰጥበት፣ ቨርቺዋል ቪዲዮዎችን የምናስተዋዉቅበት እና ላለፉት ሳምንታት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የነበራቸዉን ጉዞ የሰረዙ ቱሪስቶች ወደፊት እንዲመጡ የምናስታዉስበት ሊሆን ይገባል፡፡

4. መንግስት ሀገራችን ያላትን ዕምቅ የቱሪዝም አቅም በመረዳት ማሳያ ሊሆኑ የሚችሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት እና ማህበረሰቡን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆን በዘርፉ የተሰማሩ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ኢንቨስትመንት ያለዉን ፋይዳም በአግባቡ ይረዳል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ የቱሪዝም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ከገጠማቸዉ ፈተና እንዲወጡ አቅም በፈቀደ መጠን የማገዝ ጥረቶች እየተከናወኑ ያሉ ሲሆን የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በተለይም ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶችና አስጎብኝ ድርጅቶች በተቋማችሁ እየሰሩ የሚገኙ ዜጎችን እንድትደግፉ እና ችግሩን በጋራ በመሆን መወጣት እንዳለብን መዘንጋት የለበትም፡፡

5. ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰፊ ታሪክ፣ ባህል፣ የተፈጥሮ መስህብ ሀብቶች ባለቤት እና የቀደምት የሰዉ ዘር መገኛ በአጠቃላይ ምድረ-ቀደምት ስትሆን ከሌሎች ሀገራት በተለየ ሁኔታም የበርካታ ሀይማኖቶች፣ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ቋንቋዎች መገኛ እና ለአለም ህዝብ የብዝሃነት፣ የፍቅር፣ የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህል ተምሳሌት እና ከሀገሬዉ ባለፈ የበርካታ የዉጭ ሀገር ቱሪስቶች የጉብኝት ማዕከል ነች፡፡ በአዲስ አበባ እና በዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻዎች የምትገኙ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም ከዚህ ቀደም ለጉብኝት የመጡና ወደ ሀገራቸዉ በመመለስ ላይ ያሉ እንግዶችንም ይሁን በሀገራችን የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተሳተፉ ያሉ የዉጭ ሀገር ዜጎች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በኢትዮጵያዊነት የእንግዳ አቀባበል ባህል መሰረት እንድትቀበሏቸዉ እና እንድትንከባከቧቸዉ አደራ ለማለት እንፈልጋለን፡፡

6. ሀገራችን የበርካታ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ባለቤት ብትሆንም ቅርሶቻችን በተለያየ ምክኒያት ጥገና እና ጥበቃ የሚሹ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ይህ ወቅት ከጎብኝዎች ንክኪ ነፃ በመሆኑ በየደረጃዉ የምትገኙ የመንግስት አካላት ከበሽታዉ ተጋላጭነት ነፃ የሆኑ አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም የቅርስ እንክብካቤ እና ጥበቃ ስራዎችን በማከናዎን ችግሩን ከመከላከልና ከመቋቋም በተጓዳኝ ቅርሶቻችን በአግባቡ በመጠበቅ ወደፊት ለጎብኝዎች ይበልጥ ማራኪና ምቹ ሆነዉ እንዲጠብቁ ማድረግ ይኖርባችኋል፡፡

7. ይህ ወቅት በርካታ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ከስራ ዉጭ እንዲሆኑ እና በየቤታቸዉ እንዲቀመጡ የሚጠይቅ እና በዚሁ መሰረት መፈፀም ያለበት ነዉ፡፡ ነገር ግን በቱሪስት መዳረሻዎች አካባቢ ግለሰቦች ከሰዉ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ሳይኖራቸዉ የሚከዉኗቸዉ ለምሳሌ የዕደ-ጥበብ እና የፈጠራ ስራዎች ለገበያ በሚቀርቡበት ጥራት የማምረት ተግባር ቢኖርም በቀጣይ ለቱሪስቶች የሚቀርቡ የስጦታ ዕቃዎች እና የገፀ-በረከት ምርቶችን በሚፈለገዉ ደረጃ ለገበያ ለማቅረብ አዉንታዊ ተፅዕኖ ያለዉ ሲሆን አምራቾችንም ለአደጋ የሚያጋልጥ አይሆንም፡፡
8. እንግዶች ከዉጭ ሀገር በቦሌ አለምዓቀፍ አየር ማረፊያ በኩል ወደ ሀገራችን ሲገቡ ከዚህ ቀደም ተዘጋጅተዉ ከነበሩ ስካይ ላይት እና ግዮን ሆቴሎች በተጨማሪ በአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች በኩል በተለዩ ተጨማሪ ሆቴሎችም እንደየአቅማቸው ተመጣኝ በሆነ ወጪ እንዲቆዩ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
9. በመጨረሻም ችግሩ ቀድሞ የደረሰባቸዉን ወገኖቻችን ፈጣሪ ምህረት እንዲሰጣቸዉ እየለመን ሁላችንም ራሳችንን እና ወገኖቻችንን እንድንጠብቅ እንዲሁም በተቻለ መጠን ከዚህ ቀደም ጊዜ አግኝተን ብንሰራቸዉ የምንላቸዉና ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የማይጠይቁ ልዩ ልዩ ተግባራትን ለምሳሌ፡-
-
ለስራና ህይወታችን አስፈላጊ የሆኑ ንባቦችን
- የመመሪያ ዝግጅት እና ልዩ ልዩ ጥናቶችን
- የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባህላችን ... በማከናዎን እንድንቆይና ከችግሩ መዉጣት የሚያስችል ዕቅድ /Recovery Plan/ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

----------------------እናመሰግናለን--------------------


News and Updates News and Updates