መንግስት ለባህል ህክምና ባለሙያዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

በርካታ ዓመታትን በባህል ህክምና ላይ ያሳለፉ ባለሙያዎች ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት በሀገራችን እምቅ የሆነ የባህል ህክምና እውቀት ቢኖርም በቂ እውቅናና ድጋፍ ባለመኖሩ ዘርፉ የሚጠበቅበትን ያህል ጥቅም መስጠት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ከሀገራችን አልፎ ለሌላው ዓለም መትረፍ የሚችሉ ፈዋሽ ባህላዊ ዕውቀቶችን መጠቀም ሳይቻል ቀርቷል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ባህላዊ ህክምና ባለሙዎች ማህበር የተመሰረተ እና በጋራ ለመንቀሳቀስ ሙከራዎች እያደረገ የሚገኝ ቢሆንም ውጤት ማስመዝገብ አለመቻሉንም አንስተዋል፡፡ ባለሙያዎቹ እንደተናገሩት በአሁኑ ጊዜ ከጎረቤት ሀገሮች ጀምሮ ከሀገራችን የባህል ህክምና እውቀትን በመቅሰም የሚጠቀሙ በርካታ አገሮች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ አሁንም በባህል ህክምና የሚደረጉ ጥረቶችን መደገፍና ማዘመን ከተቻለ ሀገራችን አሁን በየዘመናቱ እየተነሱ በሰው ልጆች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ በሽታዎችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ህመሞችን የመፈወስ እድል መፍጠር እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡
ውይይቱን የመሩት የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ክብርት / ሂሩት ካሳው በበኩላቸው የባህል ህክምናን ጨምሮ በሀገራችን ያሉ ልዩ ልዩ ሀገር በቀል እውቀቶች በተቀናጀ መልኩ መልማት እንዳለባቸው ታምኖበት መንግስት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተለይ የሀገራችንን ጥንታዊ የፈውስ ጥበብን የያዙ መፅሀፍት ዛሬ ሰለጠኑ በሚባሉት ሀገራት ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ስለሆነም ባህላዊ ህክምናን በተቀናጀ መልኩ ለመደገፍና አሻሽሎ ለመጠቀም መንግስት የዘርፉ ተዋንያን ከሆኑ በተለይም ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቋማት፤ ከጤና ሚኒስቴር እና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ተቀናጅተው በዘላቂነት እንዲሰሩ አቅጣጫ ማስቀመጡን አብራተዋል፡፡
ይህንኑ ለማስቀጠል እንዲቻል በባህል ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ የሚመራ ከዘርፉ ሙያኞችና ከተጠቀሱት ተቋማት የተውጣጡ ሰዎችን የያዘ ቡድን እንዲቋቋም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡


News and Updates News and Updates