በባህል ልማት ፖሊሲ እና ሌሎች የአሠራር መመሪያዎች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፣

 

አገራችን የደረሰችበት የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለተካዊ ዕድገት እና የዘርፉ ፍላጎት ጋር ተጣጥሞ የተለያዩ አገራት ተሞክሮ በመቀመር የተሻሻለው የባህል ፖሊሲ ፣ የባህል ምንነትና ሀገራዊ ፋይዳው፣ የባህል ኢንዱስትሪ ምንነትና ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ፣ በአሉታዊ መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በዜጎች ላይ እያስከተሉት ያለው አሉታዊ ገጽታዎች የተደረገ ጥናት ውጤት እና የመከላከያ ስትራቴጂ  ሰነዶች ላይ እና የባህል ስታትስቲካዊ መረጃ ማሰባሰቢያ ቅጽ ዙሪያ ከጥቅምት 17-21 ቀን 2010ዓ.ም. ድረስ በወላይታ ሶዶ ወላይታ የባህል አደራሽ /Wolaytta Gutaraa/ ሲካሄድ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡

 

ሥልጠናውን በጋራ ያዘጋጁት፤ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከደቡብ ብ/ብ/ሕ/ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ሲሆን፣ በክልሉ ቢሮ ሥር የሚገኙ ዞኖች እስከ ወረዳዎች ድረስ ያሉ የባህልና ቱሪዝም መዋቅር ኃላፊዎችና ፈፃሚ ባለሙያዎች ማለትም ከ56ቱ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የመጡ ከ300 በላይ ተሳታፊዎች በስልጠናው ተካፍለዋል፡፡

የስልጠናው መክፈቻ በቦታው  ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችው መልዕክት ያስተላለፉት አቶ አቡቶ አኒቶ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የባህል ልማትና ጥናት ዋና ሥራ ሂደት ባለቤት እንዲሁም ክቡራን ሚኒስትሮችን በመወከል መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ደስታ ካሣ የባህል ኢንዱስትሪ ልማትና ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡

 

ስልጠናው የባህል ዘርፉ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር ከመስሪያ ቤቱ የተውጣጡ ባለሙያዎች ተመቻችቶ በስድስት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ተከፋፍሎ ትምህርታዊ ገለፃዎች የተሰጡ ሲሆን፣ በተቀመጠው መርሀ-ግብር መሠረት በቀዳሚነት በተሻሻለው የባህል ልማት ፖሊሲ የማስተዋወቁ ስራ በአገሪቱ ባሉ 805 ወረዳዎች እንደሚካሄድ እቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ መሆኑን በማብራራት፤ የፖሊሲው መቀረጽ ከዓለም አቀፍ ዕይታ እና አገሪቱ ያለችበት የዕድገት ደረጃ ጋር ተጣጥሞ መሻሻሉን፣ አስፈላጊነቱን፣ ራዕዩን፣ መርሆዎቸን፣ ዓላማዎቹን እንዲሁም የፖሊሲው ዋና ዋና ጉዳዮችና ስትራቴጂዎቹን፣ የፖሊሲው አተገባበርን አቅጣጫ የሚያመላክቱ ጠቋሚ መረጃዎች ከነማጣቀሻዎቹ በአቶ ደስታ ካሣ  የተብራራበት ገለፃና  ውይይት ተደርጓል፡፡ 

 

ሁለተኛው  ርዕሰ ጉዳይ የባህል ምንነትና ሀገራዊ ፋይዳው በሚል ርዕስ በአቶ ይስማ ጽጌ የባህል ኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ ባለሙያ የቀረበ ሲሆን፤ በመቀጠል የቀረበው የባህል ኢንዱስትሪ ምንነትና ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ፣ የበርካታ ባህላዊ እሴቶች፣ የአገር በቀል ዕውቀቶች ባለቤት በመሆን ትታወቃለች፡፡ የአንድ አገር ዕድገት ሊመጣ የሚችለው በባህል ላይ ሢሠራ ነው፡፡  የባህል ኢንዱስትሪ  ሲባል መነሻው የባህሉ ባለቤት የሆነው የዚያ ህብረተሰብ ባህላዊ ሀብቱ፣ ቅርሱ ፣ ጥበቡ፣ ዕውቀቱና ፈጠራዎቹ መሆኑ፣ የፈጠራ ኢንዱስትሪ ደግሞ በግለሰብ ጥረት በክህሎቱና በችሎታው ላይ የተመሠረተ አዲስ የፈጠራ ግኝት የታከለበት ውጤት የሚታይበት መሆኑ ተገልጿል፡፡ የባህል ዘርፉ ለኢንዱስትሪው ልማትና ዕድገት ያልተቆጠበ ጥረት ይሠራል፡፡ አገራችን የብዝሃ ባህል ባለቤት በመሆኗ የባህል ኢንዱስትሪውን ልማት በአራቱም የሙያ ዘርፎች፡- በእደ ጥበባት፣ በትውን ጥበባት፣ በእይታዊ ጥበባት፣ በስነ-ጽሁፍ ጥበብ መስክ ያሉ አቅሞችን በማሰባሰብ ለአገራዊ ኢኮኖሚ የሚኖረውን ድርሻ በማሳደግ የህብረተሰብ ተጠቃሚነት የሚረጋገጥበት ስትራቴጂ ተቀይሷል፡፡ በተለይ በዓለም ገበያ የባህል ኢንዱስትሪው  አምስት በመቶ የኢኮኖሚውን ድርሻ የሚያንቀሳቅስ በመሆኑ ይህ ዘርፍ /የባህል መገለጫዎችን፣ የባህላዊ አገልግሎቶችንና ባህላዊ ዕቃዎችን የሚያካትት በመሆኑ በእነዚህ  በርካታ የሥራ ዕድል በመፍጠር ዘርፉ ለአገራዊ ኢኮኖሚው የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ካለበት ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ እንደሚቻል በአቶ ደስታ ካሣ ገለፃ ተደርጓል፡፡ በተሳታፊዎችም ወይይት ተደርጓል፡፡

 

 

በአሉታዊ መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በመላው አገራችን ባሉ ከተሞችም ሆነ የገጠር ሕብረተሰብ ላይ እያስከተሉት ያለው አሉታዊ ገጽታዎች ስጋትን ለመቀቋቋም/ ለመከላከልና ለችግሩ መንስኤ የሆኑ ማህበራዊ ባህላዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን እንዲሁም በዚህ ዙሪያ እንደ ሀገር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን በመገምገም በሀገሪቱ የሚገኙ የዘጠኙንም ክልሎች እና የሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ጋር በመነጋገር ችግሩ ጎልቶ ይታይባቸዋል ተብለው የተመረጡ 21 የከተማ አስተዳደር ቦታዎች የተደረገ ጥናት ውጤት ላይ የታየው ግኝት ወጣቶች ሁሉን ነገር ለማወቅ ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ለሀገር በቀልም  ሆነ ለመጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች (ለአደንዛዥ እጾች፤ ለትንባሆ፣ ለአልኮል መጠጥና ለልዩ ልዩ ሱሶች) የመጋለጥ ዕድል የሰፋ እንደሆነ በአቶ ግዛቸው ኪዳኔ የቋንቋና የጋራ ባህል እሴቶች ከፍተኛ ባለሙያ ገለፃ ተደርጓል፡፡

 

በተሳታፊዎች ውይይትም የችግሩ ማጠንጠኛ ድህነት ነው፡፡ የጥናቱ ወሰን የጠበበና የተከናበት ጊዜ 2006ዓ.ም. መሆኑ ወቅታዊነት  እንዲኖረው ቢደረግ ጥሩ  ነው፡፡ በአደንዛዥ ዕፅ ምክንያት ልጅ አባቱን የሚገድልበት፣ ባንዳንድ አካባቢዎች የግጭት መነሻ፣ ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ቤት በእርግዝና እየወጡ ያሉበት ሁኔታ መኖሩ ተጠቁሟል፡፡ እንደሀገር ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

 

እንዲሁም የባህል ዘርፍ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታና ከሀገራዊ ምርት የሚኖረውን ድርሻ ለማወቅ የተዘጋጀው የባህል መረጃ ማሰባሰቢያ ቀፃ ቅፅ እና የአሠራር ማኑዋል እንዴት ሥራ ላይ  እንደሚውል ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ በተለይ ቅጾቹ በዘርፉ  የተለዩ 63 የሙያ ዓይነቶች የተዘጋጁ ሲሆን፣ እንዴት የመረጃ ምንጮችን በማግኘት በክልሎች፣ በከተማ አስተዳደሮች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ደረጃ እንደሚሰበሰብ ሁሉም አካላት በባህልና ቱሪዝም ቢሮ መዋቅር የሚገኙ ተገቢው ባለሙያ ተመድቦ መረጃው በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ተሰብስቦ እንዲጠናቀቅና ለሚመለከተው አካል እንዲቀርብ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡

 

በመቀጠል ከላይ በቀረበው  የአሉታዊ መጤ ባህሎች እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከልና  ለመቆጣጠር እንደሀገር የተዘጋጀው ብሔራዊ ስትራቴጂ በአቶ ዓለማየሁ ጌታቸው የቋንቋና የጋራ ባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡    

 

በተለይ ስትራቴጀው  ለችግሩ መፍትሔ ይሆናሉ ብሎ ያስቀመጠው በገጠርም ሆነ በከተማ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመቃኘት ለመተግበር  የሚያስችሉ በአምስት አምዶች የተመሠረቱ ዋና ዋና መንገዶችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ በተለይም የችግሩን አሳሳቢነትን ከግምት በማስገባት ለመቀነስ የሚያስችሉ ስልቶች ተቀይሰዋል፡፡ እነዚህም ቅድመ መከላከል /prevention/፣ በመጠበቅ/protection/፣ የአቅርቦት ቅነሳ /Supply reduction/፣ የመልሶ ማቋቋም /Treatment and Rehabilitation/ ላይ የተኮረ የትግበራ መርሐግብር እና ጥናትና ምርምር/Research/ ማካሄድ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

 

በመጨረሻም በክልሉ የሚገኙ ወጣቶችና ሴቶች ማህበራት አደረጃጀቶች በምክር አገልግሎት ችግሩን ይቀርፋሉ ተብሎ ስለሚታሰብ የወጣቶች ካውንሲሊንግ አገልግሎት መጠናከር ይኖርበታል፡፡ ዘርፉን ለማሳደግና ውጤታማ ለማድረግ የእያንዳንዳችን ቆራጥነት /Commitment/ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ በአምስት ቀን በቆይታችን ያገኘውን ግንዛቤ ወደ ተግባር ለመለወጥ ሁላችንም ቀጣይ ሥራችን ምን መሆን እንዳለበት በዕቅዳችን አካተን የምንሠራበት ስንቅ ይሆነናል፡፡ በክልላችን የሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ተቀናጅተንና አቅማችንን እየገነባን የምንሠራበት ሁኔታ እንፈጥራለን" በማለት አቶ አቡቶ አኒቶ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የባህል ልማትና ጥናት ዋና ሥራ ሂደት ባለቤት የስልጠናው መድረክ በይፋ ተዘግቷል፡፡


News and Updates News and Updates