የቱሪዝም ቀን በክልሎች መከበሩ ለአገር ውስጥ ቱሪዝም እድገት ፋይዳው የጎላ ነው ተባለ

 

የቱሪዝም ቀን በክልሎች መከበሩ ለአገር ውስጥ ቱሪዝም እድገትና ለዜጎች እርስ በእርስ ትስስር የጎላ ፋይዳ እንዳለው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዶክተር ሂሩት ወልደ ማርያም ገለጹ።

ሚኒስትሯ  የኦሮሚያ ክልል የሚከበረውን የዓለም የቱሪዝም ቀንን ትናንት ምሽት በአዳማ በይፋ ከፍተዋል።

በአዲስ አበባ ብቻ  ሲከበር የነበረው የዓለም ቱሪዝም ቀን ከአሥር ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር እየተከበረ ነው፡፡

ዘንድሮም በበርካታ ተፈጥሮዊ፣ታሪካዊና  ባህላዊ  የቱሪስት ሃብቶች  ባለቤት በሆነችው  በኦሮሚያ ክልል መከበሩ  የክልሉ  ቱሪዝም ሐብትና  ቱሪዝም ለልማት ያለው ፋይዳ  ለማስገንዘብ ያግዛል ሲሉ የበዓሉ ታዳሚዎች ገልፀዋል።

የቱሪዝም ዘርፍ ለዘላቂ ልማት ከሚሰጠው ፋይዳ በተጨማሪ በሥራ እድል ፈጠራ የዜጎችን ተጠቃሚነት በማሳደግ የባህል ብዝሃነትን  በማበረታታትና የዜጎችን የእርስ በእርስ ትስስር በማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጾኦ እንዳለው ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የነበረው ይኸው በዓል በክልሎች አስተናጋጅነት መከበሩ ለአገር ውስጥ ቱሪዝም እድገትና ለህዝቦች የእርስ በእርስ ትስስር መጎልበት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ነው ያሉት።

ከኬሚካልና ከነዳጅ  ቀጥሎ  ሦስተኛው የውጪ ንግድ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ አገሪቱ ካላት እምቅ የቱሪስት መስህብና ሃብት  አንጻር ተጠቃሚነቷ ዝቅተኛ በመሆኑ ለዘርፉ ልማት መጎልበት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የኦሮሚያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሎሚ በህደ በበኩላቸው በክልሉ ያሉ ተፈጥሯዊ የመስህብ ሃብቶች በመጠበቅ፣ በማስተዋወቅና በማልማት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም ባሳለፍነው ዓመት በዩኒስኮ የዓለም ወካይ ቅርስነት የተመዘገበው የገዳ ሥርዓት በማበረታታት የመሠረተ ልማት ዝርጋታን  የአገልግሎት ጥራትን በማሳደግ ረገድ ቢሮው በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን አውስተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ 38 በአገራችን ደግሞ 30 ጊዜ የሚከበረው "ቱሪዝም ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ቃል ለአንድ ሳምንት የሚቆየው ይኸው በዓል በክልሉ የሚገኙ ልዩ ልዩ የመስህብ ሃብቶች በመጎብኘት ይከበራል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2015/16 ኢትዮጵያን ከጎበኙ ዘጠኝ መቶ የውጭ አገር ጎብዎች ዜጎች  3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን  ከሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ምንጭ፡- ኢዜአ


News and Updates News and Updates